አስረስ አለልኝ የተባለ የሀገር አቋራጭ አሽከርካሪ በ2010 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ በሁመራ መስመር አሸሬ መንገድ ላይ ኬላ ላይ የታጠቁ ሰዎች እንደያዙት ይገልፃል። አጋቾቹ ከ80 እስከ 100 ሺህ ብር እንደጠየቁና ያንንም ከሚያዉቃቸዉ ሰዎች አስልኮ መለቀቁን ይናገራል።
“አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች አዋጥተው ነው ገንዘቡ ተከፍሎ የተለቀቅኩት” የሚለዉ አስረስ ገንዘቡ ባይላክ ኖሮ የከፋ አደጋ ሊያጋጥመዉ እንደሚችል ይገጻል።
ይህን አጋጣሚ የአንድ አሸከርካሪ ብቻ አይደለም መሰል ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎችም ቁጥራቸዉ እየተባባሰ መምጣቱን የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር እና አሽከርካሪዎች ይገልፃሉ።
መቀመጫውን ባህር ዳር ያደረገው እና ከ170 በላይ አባላት ያሉት ጣና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሙያ ማህበር የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌደራል መንግስት እና ለክልሎች በላከው ደብዳቤ “በሀገሪቱ ተዟዙሮ ዘር ቀለም ብሔር ሳይለይ ግልጋሎት የሚሰጥ አሽከርካሪ ዛሬ በደረሰበት እየተሳደደ እየተዋረደ እየተበደለ እየተገደለ ይገኛል። አሽከርካሪዎች ነገሮች ይሻሻላሉ ብለው በተስፋ ቢንቀሳቀሱም ከእለት እለት በደሉ እየበረታ መሄዱ አሳሳቢ ሆኖ እያየን ነው” ሲል ገልጿል።
“በእኔ ምልከታ አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየትባባሰ ያለው የባለሙያዎቹን ጉዳትና ችግር የሚያገናዝብ፣ ጉዳታችን ጉዳታቸው እንደሆነ የሚያስቡ የህግ አካላት እና የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ እና መንግስት ለችግሩ ትኩረት ባለመስጠቱ ነው” የሚሉት ፈጡ ብርሃን የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ እና የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ናቸው።
የሀገር አቋራጭ ከባድ መኪና አሽከርካሪዉ አስረስ አለልኝ እንደሚለው ደግሞ “አሽከርካሪዎች ሰርተን የቤት ኪራይ ከፈልን ስንል በመንገድ ላይ ተዘርፈን የባሰ እዳ ውስጥ እንገባለን፤ ለቤተሰቦቼ የሆነ ገንዘብ አገኘሁ ስትል መኪናህን በመሳሪያ ይመቱትና መተዳደሪያህን ያሳጡሀል፤ ያንን ለማስተካከል ሌላ ወጪ ይጠብቅሀል”
ጣና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሙያ ማህበር “በኦሮሚያ ክልል ከፍቸ ጎሃፅዮን አባይ ድልድይ እንዲሁም ወለጋ መስመር ሙሉ ለሙሉ በሚባል፣ በአማራ ክልል ጎንደር አብርሃ ጅራ ዳንሻ ከጎንደር ሸህዲ ድረስ፣ ከጋይንት ደብረታቦር ገረገራ ያሉ ቦታዎች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከካር ኬላ አባይ ግድብ መንገድ፣ በአፋር ክልል ከሚሌ አዋሽ አርባ ድረስ ያሉ መንገዶች” ዋነኞቹ አሽከርካሪዎች በደል የሚደርስባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ገልጿል።
የማህበሩ ዋና ፀሐፊ “እነዚህ አካባቢዎች በማህበራችን አባላት ላይም ጉዳት የደረሰባቸው እና በስፋት የምንጓዝባቸው መንገዶች በመሆናቸው እንጂ ሌሎች ክልሎችና ቦታዎች ላይም ችግሩ አለ” ይላል።
መቀመጫው አዲስ አበባ የሆነ ስሙ እንዲጠቀስ ባልተፈለገ ሌላ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የግል ማህበር ዉስጥ ሰራተኛ የሆነ ግለሰብ እንደሚገልፀው ደግሞ የማህበሩ አሽከርካሪዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱት ወደ ኦሮሚያ ክልል ሲሆን በማህበሩ አባላት ላይ በመንገድ ላይ ሆነው እስካሁን የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ይገልፃል። ይሁን እንጂ “በሌሎች አሽከርካሪዎች ላይ ስለሚደርሱ ጉዳቶች እንሰማለን ምናልባትም የእኛ የእድል ጉዳይ ሊሆን ይችላል” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል።
“ከአንድ ቀን በፊት በጉሀ ፅዮን መንገድ ላይ አንድ አሽከርካሪ ተኩስ ተከፍቶበት ተሽከርካሪዉ ወደ ገደል ገብቶ እሱ ተርፏል፤ ነገር ግን ቦታውን የፀጥታ አካላት መጥተው ስላልተከታተሉት በነጋታው እዛው ቦታ ላይ ሌላ አሽከርካሪ ተኩስ ተከፍቶበት ተገድሏል። ይህ ነው ቸልተኛ መሆናቸውን የሚያመለክተው” ሲል የሙያ ማህበሩ ዋና ፀሀፊ የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ለአዲስ ዘይቤ በሰጠው ቃለ መጠይቅ አስረድቷል።
ጣና የአሽከርካሪዎች ማህበር በደረሰው መረጃዎች ብቻ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ10 የሚበልጡ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ተገድለዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ግድያ እና አፈና ለመበራከቱ ሌላኛው ማሳያ አሽከርካሪዎች እየታገቱ ከ15 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር እየተጠየቁ ገንዘብ እጅ በእጅ ተረካክበህ የምትለቀቅበት ሁኔታ መኖሩ ነው። በተጨማሪም ከ20 በላይ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ታግተው በእዚህ መንገድ ገንዘብ ሰጥተው የተለቀቁ እንዳሉ ማህበሩ ገልጿል።
አዲስ ዘይቤ ጉዳዩን በተመለከተ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጠየቀችበት ወቅት ስለችግሩ መረጃ እንደሌላቸው፣ የጣና ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሙያ ማህበር የፃፈው ደብዳቤም እንዳልደረሳቸውና ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ ከሚኒስቴሩ አንድ ሰራተኛ ችግሮቹ በስፋት በክልሎች የፀጥታ አካላት ቸልተኛነት የሚፈጠሩ መሆናቸውን አዲስ ዘይቤ መገንዘብ ችላለች።
እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሳሰሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያገለግሉ አሽከርካሪዎች የፕሮጀክቱ ስፍራ ላይ እስከሚደርሱ በፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት የሚታጀቡ መሆኑን የገለፁት ሰራተኛው “እንደዛም ሆኖ ታጣቂዎች መንገድ ላይ ከመሬት ስር የሚቀበሩ ፈንጂዎችን አጥምደው ጥቃት የሚያደርሱበት ሁኔታ አለ” ብለዋል።
የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪው አቶ ፈጡ እንደሚለው “አጃቢ የፀጥታ አካላት ባሉበት ራሱ በታጣቂዎች የሚገደሉ አሽከርካሪዎች አሉ፤ አሽከርካሪዎችን ለመጠበቅ ብለው የፀጥታ አካላትም ጭምር ይሞታሉ”
ችግሩን ያባባሰው የፖሊሶችና የፀጥታ አካላት ቸልተኛነት መሆኑ የሚገልፀው አስረስ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ላይ የፀጥታ አካላት እንደሚሳተፉበት ጭምር ያነሳል። አሽከርካሪው ለዚህ ማሳያ ሲጠቅስ “ጥቆማ የሚደርሳቸው የህግ አካላት ራሱ ይሄንማ በገንዘብ መጨረስ ነው የሚሻለው” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ ብሏል።
አሁን በአሽከርካሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የአሽከርካሪ ቤተሰቦችን ስጋት ውስጥ የከተተ እና የአሽከርካሪዎችን ደግሞ የመኖር ዋስትና ፈተና ላይ የጣለ ሁኔታ ነው ሲል አስረስ ገልጿል።
የበርካታ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የቤተሰብ ህይወት በአሽከርካሪው ገቢና ስራ ላይ የተመሰረተ ነው። አስረስ የግብርና ምርቶችን ከአንድ አካባቢ ወደሌላ በማድረስ የሚሰራ ሲሆን ቤተሰቦቹ እሱ በታገተበት ወቅት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደነበሩ ይገልፃል።
“አሽከርካሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድራሉ። እንደዚህ አይነት ጥቃቶች ሲደርሱበት ግን አይደለም ለቤተሰቡ ሊተርፍ የተጎዳ የመኪና አካል ለማሰራትና ከእገታ ለመለቀቅ ገንዘቡን ይጨርሳል” ሲል አስረስ ያስረዳል። በተጨማሪም አንድ አሽከርካሪ ሲጎዳ ቤተሰብ ይፈርሳል፤ ሙያው ውስጥ ያለን ሰዎች ብዙ የተበተኑ፣ ለጎዳና ህይወት የተዳረጉ እና ልጆችን ለማሳደግ ያልተገቡ ስራዎችን ለመስራት የተገደዱ ቤተሰቦችን እናውቃለን ሲልም የአደጋውን አስከፊነት ያስረዳል።
የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪው ከእዚህ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ሲያስረዳ ከ10 ዓመታት በፊት በአፋር ክልል ገዋኔ አካባቢ አሽከርካሪዎችን ስጋት ውስጥ የከተተ ሁኔታ ነበር። “በቀን የምዘረፍበትና በምሽት የማትንቀሳቀስበት ሁኔታ ነበር፤ በተቀራራቢ ጊዜ ውስጥ 4 አሽከርካሪዎች እዛ አካባቢ ሲገደሉ በአፋር ክልል መንገድ ላይ የነበሩ አሽከርካሪዎች መንግስት መፍትሔ ካልሰጠ አንንቀሳቀስም በማለታቸው የገዋኔ መንገድ ለ24 ሰዓታት በፀጥታ አካላት እንዲጠበቅ ተደርጎ ቀንም ሌሊትም በሰላም መስራት የተቻለብት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።”
ጣና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሙያ ማህበር “ከበደላችን ባለፈ መንግስትም ሆነ ሚድያዎች ለጉዳታችን ለበደላችን ለእንግልታችን ለሞታችን ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት የሚያሳዩት ቸልታ ለሙያችን ያላቸውን ክብር ዝቅ ያለ መሆኑን አመላካች ሆኖ አይተነዋል፤ በዚህም ቅሬታ ተሰምቶናል” ሲል በደብዳቤው ላይ ገልጿል።
መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የአሽከርካሪዎችን ደህንነት ቢከታተል ችግሩ የሚቀረፍ ነው የሚለው የማህበሩ ዋና ፀሐፊ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈፀምባቸውን አካባቢዎች ትኩረት ሰጥቶ መጠበቅ ያስፈልጋል ብሏል።
“እኛ አሽከርካሪዎች እየደረሰብን ያለውን ግፍ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ስራውን በመስራት ወንበዴዎችንና አጥፊዎች አጥፍቶ ቀጥቶ አሽከርካሪው ያለስጋት የሚሰራበትን ሂደት የመንግስት ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን ይገባል” የሚለው ደግሞ በማህበሩ ደብዳቤ ላይ ተገልጿል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በሩብ እና በግማሽ ዓመት ከፌደራል እና ከክልሎች የፀጥታ አካላት ጋር በአገልግሎቱ ዙሪያ ግምገማ የሚያካሄድ በመሆኑ ችግሩን በትኩረት እንደሚመረምር እና ማስተካከያዎችን የሚያደርግ መሆኑን አዲስ ዘይቤ መረዳት ችላለች።
አቶ ፈጡ ብርሃን “በእዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን አሽከርካሪ አግተው በስልክ ተደዋውለው ገንዘብ የሚቀበሉ ሰዎችን መቆጣጠር የሚከብድ አይመስለንም ትኩረት የመስጠትና ያለመስጠት ጉዳይ ነው። የእኛ እስትንፋስ አለመኖር የማይገዳቸው ነገር ግን ስራችን አቁመን መብታችንን እናስከብር ሲባል እኛን ለማውገዝ የሚንቀሳቀሱ አሉ፤ ለደህንነታችን ካላሰቡ ለስራው ማሰብ አይችሉም ብሎ “ሞቴን ካልተቃወምክ ለምን በሰላም መቆሜን ትቃወማለህ” ሲል ይጠይቃል።
ሌላኛው አሽከርካሪ አስረስ አለልኝ “ለሀገር ግልጋሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎችን ደህንነት መንግስት በትኩረት መጠበቅ አለበት። እንዴት የመድኅኒትና የምግብ እጥረት በሚከሰትበት ሀገር ከባድ መኪና ሲነድ ታያለህ፤ እነዚህን የሚያመላልሱት አሽከርካሪዎች እኮ ናቸው ጉዳት የሚደርስባቸው” ብሏል።