የካቲት 19 ፣ 2014

የአዳማ የሙዚቃ እንቅስቃሴ ከአጼ ገላውድዮስ እስከ ኡርጂ አዳማ ባንድ

City: Adamaባህል

ከሰማንያዎቹ መጀመርያ አንስቶ በሳክስፎንና በክላርኔት ተጫዋችነት ያገለገለው ለገሰ ገብረወልድም ለአዳማ ከተማ የባንድ ሙዚቃ መነሻው የአጼ ገላውድዮስ ኦርኬስትራ በመሆኑ ላይ ይስማማል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአዳማ የሙዚቃ እንቅስቃሴ ከአጼ ገላውድዮስ እስከ ኡርጂ አዳማ ባንድ
Camera Icon

ፎቶ፡ ከታዬ ሽብሩ ማህደር

የባቡር መሠረተ ልማትን ተንተርሳ ያደገችው አዳማ በርካታ የኪነ-ጥበብና የሚድያ ባለሙያዎችን አፍርታለች። ከእነዚህም መካከል ጋዜጠኛ ደረጄ ኃይሌ፣ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ተዋናይት ጀማነሽ ሰለሞን፣ ድምጻዊት ሃና ሸንቁጤ፣ ጋዜጠኛ ሰለሞን ክፍሌ፣ ደራሲ ኃይሉ ጸጋዬ፣ ሳክስፎን ተጫዋች ፉሲል አዲኛ፣ ተዋናይ በኃይሉ ማንያዘዋል፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ፣ ድምጻዊ ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። በሙዚቃው ዘርፍ በጎላ ተሳትፏቸው ከሚታወቁ የሙዚቃ ባንዶች መካከል ዋና ዋናዎቹን በዚህ ጽሑፍ እንመለከታለን።

አጼ ገላውድዮስ ኦርኬስትራ

ለከተማዋ የሙዚቃ ቡድኖች ታሪክ መሰረት የጣለው በአጼ ገላውድዮስ መርሃ-ሙያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ስር ይንቀሳቀስ የነበረው “የአጼ ገላውዲዮስ ኦርኬስትራ” ስለመሆኑ አዳማ ተወልዶ ያደገው ገጣሚ ነቢይ መኮንን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል። ታዬ ሽብሩ የኦርኬስትራው አባል እና ሊድ ጊታር ተጫዋች ነበር። በማኅበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳትፎ ያለው ታዬ ሃምሳ ዓመቱን ሊደፍን አንድ ዓመት የቀረውን የአጼ ገላውዲዮስ ኦርኬስትራ መረጃዎች እያጋራ ይገኛል።

ከሰማንያዎቹ መጀመርያ አንስቶ በሳክስፎንና በክላርኔት ተጫዋችነት ያገለገለው ለገሰ ገብረወልድም ለአዳማ ከተማ የባንድ ሙዚቃ መነሻው የአጼ ገላውድዮስ ኦርኬስትራ በመሆኑ ላይ ይስማማል። ስለ ተቋቋመበት አጋጣሚ ሲናገርም በወቅቱ የትምህርት ሚንስትር አማካኝነት እጣ ለወጣላቸው ትምህርት ቤቶች ኦርኬስትራ ለማቋቋም ሲታቀድ እንደተቋቋመ መስማቱን ያስታውሳል። የወቅቱ እድለኞች የደሴው ወ/ሮ ስህን እና የናዝሬቱ አጼ ገላውድዮስ ነበሩ። የራሱ የተሟላ መሳሪያ ኖሮት ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ ተማሪዎች አባልነት ብስራት ታመነ በተባለ ሙዚቀኛ እየተመራ በ1965 ዓ.ም. ሥራ ጀመረ። ፖሊስ ኦርኬስትራ ያገለገለው ሙዚቀኛ ብስራት ታመነ ሙዚቀኞችን የመምራትና የማሰራት ኃላፊነቱን ተወጥቷል። “በደርግ ዘመን መጀመሪያ በነበሩ የፖለቲካ አለመግባባቶች ምክንያት እንቅስቃሴው ቀዝቅዞ ከ1967 ዓ.ም. በኋላ ተዳከመ። ባንዱ በወቅቱ ከፍተኛ ኪነት ለሚባሉት መሠረት ጥሏል” ሲል ለገሰ ገ/ወልድ ይናገራል።

ይህ ኦርኬስትራ እንደ ድምጻዊ ጥላዬ ጨዋቃ እና / በወቅቱ / ይገልጻሉ እና ድምጻዊ እና ጋዜጠኛ ንጉሤ ወ/ማርያም ያሉ በሀገር ደረጃ በተለይም በእድገት በሕብረት የስራ እና የእውቀት ዘመቻ ላይ በዘመሯቸው መዝሙሮች የሚታወቁ ባለሞያዎችን አፍርተዋል።

በዘመነ ደረግ በተቋቋሙት የከፍተኛ ኪነቶች እንዲሁም በወቅቱ አስተዳደራዊ አጠራር የናዝሬት አውራጃ ላቋቋመው ባንድ ዋነኛ የባለሞያ ግብዓቱ የአጼ ገላውዲዮስ ኦርኬስትራ እንደነበር ሙዚቀኛ ታዬ ሽብሩ ይገልጻል።

አዳማ ባንድ 

አዳማ ባንድ በ1981 ዓ.ም. የተመሠረተ ባንድ ነው። የሳክስፎን እና ክላርኔት ተጫዋቹ ለገሰ ሀብተወልድ ከመስራቾቹ መካከል አንዱ ነው። "ከጓደኛዬ ካሳዬ አበበ ጋር በ1981 ዓ.ም. ከምድር ጦር እንደተመለስኩ መሠረትነው። አቶ መንግስቴ አበበ ደግሞ በማስተባባር ይሰራ ነበር" ሲል ለገሰ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። የእነርሱን መምጣት ተከትሎ የሙዚቃ ሙያቸውን በሌላ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ባለሞያዎችም ወደ እነርሱ መምጣታቸውን ያስታውሳል። በባንዱ ውስጥ ሊድ ጊታር የሚጫወቱት ተፈሪ ነጋሽ እና ሳሙኤል ጣሰው (ሳንቾ) ናቸው። ወርቅአገኝ ሸዋንደግፍ ሳክስፎን፣ ክፍሉ ማሞ ድራም፣ ታደሰ ቤዝ ጊታር፣ ካሳዬ አበባ ድራም ተጫውተዋል። በድምጽ ድምጻዊት ዮዲት መኮንንን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈዋል። ከ1983 ዓ.ም. የመንግስት ለውጥ በኋላ ባንዱ ወደ “ኦዳ-ነቤ ባንድ” እንደተቀየረ ለገሰ ገብረወልድ ይናገራል።

ኦዳ-ነቤ ባንድ የተለያዩ የባህል ሙዚቃዎችን ከሰራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እንደፈረሰ በሰራበት አጭር ጊዜ ውስጥ ግን የተለያዩ በምስራቅ ሸዋ ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ባህሎች ላይ እንደሰራ ለገሰ ገብረወልድ ይናገራል።

ሳፊ ባንድ

ሶፊ ባንድ የተመሰረተው በ1984 ዓ.ም. ነው። መስራችና ባለቤቱ ሳፊ አላሚን ይባላል። የአጼ ገላውድዮስ ት/ቤት መምህር ነበር። ሙዚቃ አፍቃሪው፣ ማየት የተሳነው ሶፊ አላሚን በስሙ በጠራው ባንድ በርካታ ባለሙያዎችን አፍርቷል። ከእነዚህም መካከል አበበ ከፊኒ፣ ኤርሚያስ አስፋው፣ ሃድጉ ዘስላሴ፣ ሚኪያስ ቸርነት ይጠቀሳሉ። በሰማንያዎቹ አጋማሽ ስመጥር የነበረው ሶፊ ባንድ ከአዳማ አልፎ በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች እውቅና አትርፏል።

በአሁን ሰዓት ከሙዚቃ ህይወት ራሱን ያገለለው ሶፊ ኑሮውን አሜሪካን ሐገር አድርጎ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንደሚገኝ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ፔሊካን ባንድ

ፔሊካን ባንድ በሰማንያዎቹ አጋማሽ ከታዩት የሙዚቃ ባንዶች መካከል አንዱ ነው። የተመሰረተው በ1985 ዓ.ም. ነው። የባንዱ መስራች በሙያው አርኪዮሎጂስት የሆነና የሙዚቃ ፍቅር ያለው ታደሰ የሚባል ሰው ነው። ይህ ሰው ለትምህርት ከሄደበት ሶቪየት ሕብረት የሙዚቃ መሳሪያዎች አምጥቶ ባንዱን ማቋቋሙን ጊታሪስት ሚሊዮን ነጋሽ ይናገራል። ባንዱ በአዳማ ከተማ ከተቋም ድጋፍ ውጭ በግለሰብ ደረጃ በመንቀሳቀስ የመጀመሪያው ሙሉ ባንድ ሊባል የሚችል እንደነበረም ያስረዳል።

"በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው ታዋቂው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ በ80ዎቹ መጨረሻ ደንበላ አካባቢ የምሽት መዝናኛ ነበረው። በዚህ መዝናኛ ውስጥ የራሱን ባንድ አቋቁሞ ይሰራ ነበር" የሚለው በባንዱ በጊታር ተጫዋችነት የተሳተፈው ሚሊዮን ነጋሽ ነው። ሚልዮን ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ባንዱ ከሁለት ዓመታት በላይ ሊዘልቅ እንዳልቻለ ተናግሯል።

ኡርጂ አዳማ ባንድ

“ኡርጂ” የኦሮምኛ ቃል ነው። በአማርኛ ቋንቋ “ኮከብ” የሚል ትርጓሜ አለው። በ1998 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን ከዚህ ቀደም የተለያዩ ባንዶችን ባዋቀረው ለገሰ ገብረወልድ አነሳሽነት ስለመቋቋሙ የአሁኑ የባንዱ ኃላፊ ሚሊዮን ነጋሽ  ያስረዳል። በወቅቱ በነበረው የባህል ኃላፊ ደጀኑ እሸቱ እና በለገሰ ገብረወልድ ጥረት በ200 ሺህ ብር በጀት ተቋቋመ። በአዳማ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ስር የሚገኘው ባንዱ በስሩ የባህል፣ ዘመናዊ ቴአትር እንዲሁም የውዝዋዜ ቡድኖች አሉት።

"በ16 የሙዚቃ ባለሙያዎች ስራ የጀመረው ባንዱ በአሁን ወቅት 32 ባለሞያዎችን በቋሚ ቅጥር እንዲሁም ቁጥራቸው በተለያየ ጊዜ የሚለያይ 7 የነጻ አገልግሎት ባለሙያዎችን ይዞ ይገኛል" የሚለው የባንዱ ኃላፊ ሙዚቀኛ ሚሊዮን ነጋሽ ነው።

"ተተኪ ባለሙያዎችን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ በክረምት ወቅት ለአራት ተከታታይ ዓመታት በየዓመቱ 25 ወጣቶችን እናሰለጥናለን" የሚለው ሚሊዮን ነጋሽ የባንዱን ዶክመንቴሽን ለመስራት እና የተለያዩ አልበሞች ለማዘጋጀት መታሰቡን ነግሮናል።

“ባንዱ ከስያሜው ጀምሮ የአዳማ ምልክት ነው” የሚለው የጽ/ቤቱ የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሳዬ በአሁን ወቅት 2.3 ሚሊየን ብር ወጪ የማጠናከሪያ ስራ ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

አስተያየት