መጋቢት 8 ፣ 2014

ልማት ባንክ የሚያስተዳድረው “ኢቱር ቴክስታይል” ፋብሪካ ሰራተኞችና ማኔጅመንት ውዝግብ

City: Adamaመልካም አስተዳደርዜና

የተለመደ የቀድሞ ሥራቸውን በአዲስ አመራር የቀጠሉት ከአንድ ሺህ በላይ የፋብሪካው ሰራተኞች ከአዲሱ አመራር ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደሚገኙ ስማችን እንዳይጠቀስ ያሉ የፋብሪካው ሰራተኞች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ልማት ባንክ የሚያስተዳድረው “ኢቱር ቴክስታይል” ፋብሪካ ሰራተኞችና ማኔጅመንት ውዝግብ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

ካሳለፍነው ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተመለሰ ብድር ማካካሻ እንዲሆን “ኢቱር ቴክስታይል” የተሰኘውን የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ተረክቦ በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቴክስታይሉ ሰራተኞች ቅሬታ ቀርቦበታል። የቀድሞው አስተዳደር በየዓመቱ የሚያደርገውን የደሞዝ ጭማሪ አዲሱ አስተዳደር ሊከለክለን አይገባም፣ በፈቃድም ቢሆን ከሥራ ለምንቀርባቸው ቀናት ደሞዝ መቆረጥ የለበትም የሚል ጥያቄ ያነሱት ሰራተኞቹ ለ2ቀናት ስራ ላይ ሆነው ለግማሽ ሰዓት ሥራ በማቆም አድማ እስከማካሄድ ደርሰዋል።

የተለመደ የቀድሞ ሥራቸውን በአዲስ አመራር የቀጠሉት ከአንድ ሺህ በላይ የፋብሪካው ሰራተኞች ከአዲሱ አመራር ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደሚገኙ ስማችን እንዳይጠቀስ ያሉ የፋብሪካው ሰራተኞች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። የአለመግባባቱ ምክንያት የተለመደው ዓመታዊ የደሞዝ ጭማሪ በዚህ ዓመት መዘለሉ እና አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ደሞዝ መቆረጡ መሆኑን ሰምተናል።

በቱርካዊያን ባለሐብቶች ባለቤትነት አዳማ ከተማ ደንበላ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ መልካ ሂዳ በሚባል አካባቢ በ2002 ዓ.ም. የተቋቋመው ፋብሪካው ለማስፋፊያ አገልግሎት እንዲውል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ቢበደርም ለ6 ዓመታት በወቅቱ መመለስ አልቻለም። “ኢቱር ቴክስታይል” ብድሩን በወቅቱ መመለስ ባለመቻሉ ፋብሪካውን የማስተዳደር ኃላፊነቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተረክቧል።

በየዓመቱ በፈረንጆቹ ዓመት በወሩ መጀመርያ ጃንዋሪ ላይ የሚካሄደው የደሞዝ ጭማሪ በዋናነት የስራ ብቃትን ያማከለና የቅርብ አለቃ የሚሰጠውን ማረጋገጫ የተመረኮዘ እንደነበር የሚያስታውሱት ሰራተኞቹ፤ አዲሱ አስተዳደር ፋብሪካውን ሲረከብ “በቂ በጀት አለኝ” ቢልም አሁን ላይ የሥራ ዋስትናቸው ራሱ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“በአጠቃላይ ሐገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ጫና፣ የተለመደውን የቀደመ የድርጅቱን አሰራር እና ሌሎች ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጭማሪው እንዲደረግልን በደብዳቤ ጠይቀናል” የሚሉት ሰራተኞቹ ከፍተኛ አመራሩ ለጥያቄአቸው ተገቢ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል። “የፋብሪካው ሥራ ለግማሽ ሰዓት ያህል ተቋርጦ ውይይት ተደርጓል። በወቅቱ የማኔጅመንት ሰዎች ሁለት ወራት ታገሱን የሚል ምላሽ ነበር የሰጡን። ሁለት ወራት አልፎም የተለወጠ ነገር የለም” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በፈቃድም ቢሆን በሥራ ገበታው ላይ ያልተገኘ ሰራተኛ ከወርሃዊ ደሞዙ ላይ 200 ብር መቆረጡ እንዳማረራቸው ስማችንን ደብቁልን ካሉን የፋብሪካው ሰራተኞች ሰምተናል።

በፋብሪካው ላይ የተነሳውን ቅሬታ አስመልክቶ ሥራ አስኪያጁ አቶ ዮሐንስ ኃ/ጊዮርጊስ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ “ፋብሪካው ከሁሉም በፊት ሰራተኞቹን ያስቀድማል” ብለዋል። “ድርጅቱ  እየሰራ የሚገኘው በከፍተኛ ግብዓት እና መለዋወጫ አቅርቦት እጥረት ላይ ነው። ነገር ግን እንደዚያ ቢሆንም ከሁሉም በፊት የሰራተኞቹን የስራ እድል ለመጠበቅ እየሰራ ነው” ያሉ ሲሆን ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ከሰራተኞች የስራ ፍቃድ ጋር በተገናኘ ስለተነሳው ቅሬታ በሰጡት ምላሽም “የሰራተኞች መቅረት ፋብሪካው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ምርት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። የቀረ ሰው የሚቀጣው ከዚህ መነሻ ነው። በቀና ጎኑ ቢወሰድ ጥሩ ነው። ከበፊቱ አመራር የተሻለ የአሰራር ሂደት ለመከተል እየጣርን ነው” ብለዋል።

ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ በቱርካዊያን ባለሐብቶች ተቋቁመው ጨርቃጨርቅ ማምረት ከጀመሩ ፋብሪካዎች መካል ብድር ባለመክፈል ምክንያት ከሐገር የወጣው “ኢቱር ቴክስታይል” ብቻ አለመሆኑ ይታወሳል። ከኢቱር በተጨማሪ “አይካ አዲስ” እና “ኤልሲ አዲስ” ብድራቸውን ሳያጠናቅቁ ሥራ ካቋረጡት መካከል ይጠቀሳሉ።

አስተያየት