መጋቢት 8 ፣ 2014

በደቡብ ወሎ ዞን የጫት ማሳ ወደ ፍራፍሬ ምርት እየተቀየረ መሆኑ ተሰማ

City: Dessieምጣኔ ሃብት

አርሶ አደሮቹ በማሳቸው ላይ የሚገኘውን ተክል የረዥም ጊዜ ጉዳት ከተረዱ በኋላ ማሳቸውን ጠቃሚ ወደ ሆኑ የፍራፍሬ ምርቶች እየቀየሩ እንደሚገኙ ከአቶ ገብሩ ተረድተናል።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በደቡብ ወሎ ዞን የጫት ማሳ ወደ ፍራፍሬ ምርት እየተቀየረ መሆኑ ተሰማ
Camera Icon

ፎቶ፡ አዲስ ዘይቤ

በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ 4 ጫት አምራች ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ ፈቃደኛ ገበሬዎች የጫት ማሳቸውን ወደ አትክልት እና ፍራፍሬ በመቀየር ላይ እንደሚገኙ ተሰምቷል። ተለሁደሬ፣ አምባሰል፣ ቃሉ እና ወረባቦ ከተባሉ ጫት አምራች አካባቢዎች የተውጣጡት ፈቃደኛ ገበሬዎች ማሳቸውን ወደ ፍራፍሬ የቀየሩት “ሆርቲላይፍ” በተሰኘ ፕሮጀክት አማካኝነት ነው። በሙከራ ፕሮጀክቱ የ30 ፈቃደኛ ገበሬዎች ማሳ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን እያንዳንዱ ገበሬ 500 ካሬ መሬት በፍራፍሬ አልምቶ ተጠቃሚ ሆኗል።

የደቡብ ወሎ “ሆርቲላይፍ” ክላስተር አስተባባሪ አቶ ገብሩ ነጋሽ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ “ኤስኤንቪ ሆርቲላይፍ” የሚል ፕሮጀክት በመንደፍ  በደቡብ ወሎ ዞን በተመረጡ 4 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ አድርጎታል። የአርሶ አደር፣ የመስክ፣ የት/ቤት የሚል ክፍልፋይ ያለው ፕሮጀክቱ ዋና ግቡ ጫት ከዛሬ ጥቅሙ በተለየ በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ ብሎም በሐገር ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ነው።

አርሶ አደሮቹ በማሳቸው ላይ የሚገኘውን ተክል የረዥም ጊዜ ጉዳት ከተረዱ በኋላ ማሳቸውን ጠቃሚ ወደ ሆኑ የፍራፍሬ ምርቶች እየቀየሩ እንደሚገኙ ከአቶ ገብሩ ተረድተናል።

“ከግንዛቤ ፈጠራው በኋላ ለእያንዳንዱ ገበሬ 50 የፍራፍሬ ችግኞች እንሰጣለን። በስራችን ጥሩ ውጤት ዕያየን ነው” የሚሉት አቶ ገብሩ ለገበሬዎቹ ከሚታደሉት ችግኞች መካከል ማንጎ እና ፓፓዬ እንደሚገኙበት ነግረውናል።

አርሶ አደር ሁሴን ከማል የአምባሰል ወረዳ 03 ቀበሌ ነዋሪ ነው። የነበረውን የጫት ማሳ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ቀድሞ በመቀየር ለቀበሌው መሰል አርሶ አደሮች ሞዴል ነው። ስለሁኔታው ሲናገር "እኔ መጀሪያ ላይ የለመድኩትን ስራ ቀይሬ ወደ ሌላ ለመግባት ትንሽ የፍርሃት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። ነገር ግን ጫት በአካባቢያችን ነዋሪ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉደት በተመለከተ ማወቅ ስጀምር በውሳኔዬ ገፋሁበት” ብሏል።

አሁን የሚሰማውን የመንፈስ እርካታ በተመለከተም “ቢያንስ አሁን ለሰዎች በሱስ መጠመድ፣ ለስንፍናቸው እና ለጤና መታወካቸው ምክንያት እየሆንኩ አይደለም” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

የአየር ንብረቱ እና መሬቱ ለአትክልት እና ፍራፍሬ ተስማሚ በመሆኑ ከጫት ምርቱ ያገኝ የነበረውን ገቢ እያገኘ ስለመሆኑም ነግሮናል። “ሂደቱ አድካሚ ቢሆንም በውጤቱ ደስተኛ ነኝ። ከዚህ በፊት ከፓፓያ ምርት እስከ 150ሺህ ብር አግኝቻለሁ። በቀጣይነትም ባለኝ ባዶ መሬት ስራዬን አስፋፍቼ ለመስራት በዝግጅት ላይ ነኝ” ብሎናል።

እንደ አርሶ አደር ሁሴን ሁሉ ሌላው ሀሳቡን ለአዲስ ዘይቤ የገለጸው አርሶ አደር ጀማል አህመድ የተሁለደሬ ወረዳ ቀበሌ 01 ነዋሪ ነው። በጫት ማምረትና ሽያጭ ከተሰማራ ከ25 ዓመት በላይ አንደሆነው ይናገራል። ሁሴን ባለትዳርና የ5 ልጆች አባት ነው። የጫት ማምረት ስራን ከወላጆቹ አንደወረሰ ገልጾ አሁን ስላለበት ሁኔታ ሲናገር

"የጫት ስራዬን ትቼ ወደ ፓፓየ ማምረት ለመግባት ሳስብ በጣም ተቸግሬ ነበር። ሰው ሁሉ እንደ እብድ ነበር የቆጠረኝ። ባልተቤቴም ዘመድ አዝማድ ጋር በመሄድ ‘ጫት ማምረቱን በመተው ሌላ ገንዘብ የማያስገኝ ስራ እሰራለሁ እያለ እኔንም ልጆቼንም ለችግር ሊዳርገን ነው’ እያለች ክስ ብታበዛብኝም ማሳዬን ወደ ፍራፍሬ ማምረት ለመቀየር የፈለኩበትን ምክንያት እና ጫት በእኛና በልጆቻችን ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት፣ አክሳሪ ዘርፍ እንዳልመረጥኩ፣ ትንሽ ጊዜ ሰጥተው የውጤቱን ጥሩነት እንዲመለከቱ ተስማምተን ወደ ስራው ገባሁ። ጠንክሬ በመስራት፣ ከግብርና ባለሙያዎች የሚሰጠኝን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የተከልኩት ፓፓዬ ለፍሬ በቃ። ከሽያጬም 80 ሺህ ብር ገቢ አገኘሁ። አሁን ከቤተሰቤ አለፎ የአካባቢያችን አብዛኛው ጫት አምራች አርሶ አደሮች ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ" ሲል አርሶ አደር ጀማል ተናግሯል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መመሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ስለ አርሶ አደሮቹ የስራ እንቅስቃሴ ሲገለጹ "በመጀመሪያ ደረጃ ስራው አስተሳሰብ ላይ መጀመር አለበት ብለን በማመን የግንዛቤ መፍጠር ላይ ነበር ያተኮርነው። ከዚያም በጎ ፈቃደኛ አርሶ አደሮች የጫት ማሳቸውን በመቀየር በአንድ ዓመት ውስጥ የተከሉት ፓፓያ ለፍሬ በቅቶ ዓይተናል። አንድ አርሶ አደር 50 የፓፓያ ችግኝ ተክሎ በማልማት እንዲጀምር ነው የተደረገው። 200 ካሬ ሜትር የቦታ ስፋት ላይ ያለ ምርት እስከ 100 ሽህ ብር ምርት ይሰጣል። በአንድ ሄክታር ላይ እናልማ ብንል ደግሞ አንድ አርሶ አደር እስከ 2.5 ሚሊየን ብር ብር ገቢ ማግኘት ይችላል" ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ግብርና መምሪያ ለአርሶ አደሩ የሚጠቅም እናም ደግሞ ኃላፊነት የማይሰማው ትውልድ እንዲፈጠር እያደረገ ያለውን ጫት በመብቀያው ላይ እንዳይገኝ ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እንዲሰራ “ሆርቲላይፍ” የተሰኘው ኘሮጀክት የተሻሻለ የቋሚ ተክል ዝርያ በማቅረብም ይሁን ሙያዊ እገዛ እገዛ በማድረግ ሚናው ትልቅ ነው።

አቶ አሊ ሰይድ በተጨማሪነት ሲገልጹ "በቀጣይነት ስራውን ለማስፋት ወረዳዎች እየለየን ነው። በተለይም የቆላ ፍራፍሬ ለማምረት አቅም ያላቸውን ወረዳዎች ከሞዴል ተፋሰስ ልማት ጋር አቀናጅተን ለመፈጸም በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን። ለዚህም ማስፈጸሚያ በጀት ከመንግስትም፣ ከኘሮጀክትም በማሰባሰብ ወጣቱ በአንድ ዓመት ውስጥ አጥጋቢ ምርት ወደሚያስገኝለት ጤናማ ስራ እንዲሳብ የማድረግ ሰራን አጠናከረን በመቀጠልና የሰዎችንም ግንዛቤ በማስፋት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የጫት ጉዳት ቀንሰን ሰፊውን የሃገራችን ማኅበረሰብ፣ አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ ስናደርግ ትውልድንም እናተርፋለን” በመለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።