የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በአለም ኢኮኖሚ ላይ የበረታ ጫና ያደርሳል ተብሎ ተፈርቷል። የጦርነቱን መጀምር ተከትሎ ከወዲሁ የአለም ገበያ በተለይም የነዳጅ ንግድ በርካታ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እያስተናገደ ይገኛል። ግጭቱ በመላው ዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ሲሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2008 በኋላ ከፍተኛ የሆነውን የመሸጫ ዋጋ በማስመዝገብ ከ100 ዶላር ተሻግሯል።
ሩሲያ በበኩሏ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል እንደገለፀችው በጀርመን በኩል ከአውሮፓ ሀገራት ጋር የሚያገናኛትን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ልትዘጋ እንደምትችል እና በአዉሮፓ ሀገራት የነዳጅ ዋጋ በበርሜል እስከ 300 ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችል አሳስባለች። ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ላይ የከፋ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት ይሰማል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ በ1993 ዓ.ም. የፀደቀውን ‘የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ’ን በማንሳት “እየሰፋ የመጣዉን በፖሊሲ ያልተደገፈ የነዳጅ ድጎማ ከተመረጡ ተሽከርካሪዎች በሂደት ለመቀንስና ለማስቀረት” የሚያስችል ያለውን አሰራር አፅድቆ ከስድስት ወራት የዝግጅት ምዕራፍ በኋላ ተፈፃሚ እንዲሆን ወስኗል።
ይህም ከአለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ ጋር ተደምሮ በኢትዮጲያ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ምን አይነት ተጽአኖ ይኖረዋል?
አብዱልመናን መሀመድ ነዋሪነታቸዉ በእንግሊዝ ሀገር ያደረጉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከብር የመግዛት አቅም መውረድ ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ የከፋ ነው ይላሉ።
የዳሎል ነዳጅ ማደያ ባለቤት አቶ ደሳለኝ አበባየሁ እንደሚገልፁት ደግሞ የሩሲያ እና ዩክሬን ግጭት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። “በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ መንግስት ከፍተኛ ድጎማ ለነዳጅ ገበያ ይመድባል፤ የዓለም አቀፉ ዋጋ መናር ደግሞ ችግሮቹን ያባብሳል” ብለዋል አቶ ደሳለኝ።
የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም ገበያ በሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ ምክንያት የሚፈለገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጎም የነዳጅ ዋጋን ማረጋጋትን ዓላማ አድርጋ ባፀደቀችው አዋጅ እየተመራች ብትቆይም የሀገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ የዓለም አቀፉን ዋጋ በሚያንፀባርቅ መልኩ በየጊዜው እየተከለሰ ለሸማቾች እንዲቀርብ ባለመደረጉ በዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ላይ ከፍተኛ እዳ እየተከማቸ መሆኑ ተገልጿል።
በአዋጁ መሰረትም የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት የሃገር ውስጥ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በሚወሰንበት ጊዜ ለነዳጅ መግዣና ለሌሎችም ጉዳዮች ታሳቢ ተደርገው በነበሩ ወጪዎች እና በትክክል በተደረገው ወጪ መካከል የሚኖረውን ልዩነት ለፈንዱ ሂሳብ ገቢ እንደሚያደርግ ተገልጿል። ይህም የነዳጅ ዋጋ በሚጨምርበት ጊዜ እንዲያገለግል ጥሩ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገልፀዋል።
የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ያለበት ጉድለት በአለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ በሚሄደበት ወቅት የሀገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያው መዘግየት ነው ይላሉ አብዱልመናን። በውጤቱም በዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ውስጥ ያለው ገንዘብ በፍጥነት ያልቅና መንግስት ተጨማሪ ገንዘብ ለመጨመር ይገደዳል ሲሉ ስጋታቸዉን ይገልጻሉ።
ይህ ሲሆን ደግሞ በመደጎሚያው ውስጥ ይህንን ገንዘብ ለማስመለስ መንግስት የሀገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ይኖርበታል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያውም “ድጎማው ይቋረጥ? አይቋረጥ? ከሚለው ሃሳብ ይልቅ በአግባቡ እየጠቀመ ነው አይደለም የሚለውን መፈተሽ የተሻለ ነው” ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ቁጥሩ ባልተጠቀሰ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፌደራል መንግስቱ ከ100 ቢልየን ብር በላይ ለነዳጅ ድጎማ ማዋሉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ዋነኛው ምክንያት በቀጠናው ካሉ ሀገራት አንፃር የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ ህገ ወጥ ነጋዴዎች እና የቦቴ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርበውን ነዳጅ ድንበር እያሻገሩ በውድ ዋጋ መሸጣቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ጠቅሰዋል።
ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና ከ40 ዓመታት በላይ በነዳጅ ንግድ ውስጥ የቆዩ ግለሰብ እንደሚገልፁት በሀገር ውስጥ ያለው የነዳጅ ገበያ የተደራጀ ወንጀል እና ሙስና በስፋት የሚሰራበት ዘርፍ ሆኗል ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ምክንያትም የሚያጠናክሩ በርካታ ክስተቶችን መታዘባቸውን የሚገልፁት ነጋዴው “ነዳጅ ከኢትዮጵያ አውጥተው በጎረቤት ሀገራት ለመሸጥ እንዲሁም ሀገር ውስጥ በሚሸጥበት ወቅት በዋጋና ከሌሎች ምርቶች ጋር በመቀላቀል የማጭበርበር ስራ አለ፤ በእዚህ ውስጥ ደግሞ የነዳጅ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናትም የወንጀሉ ተሳታፊ ናቸው” ብለዋል።
“እኔ በግሌ በማስተዳድረው የነዳጅ ማደያ አብሮ የማጭበርበር ጥያቄዎች እና በሀሳቡ ካልተስማማን በስራችን ላይ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያዎች ቀርበውበኛል” ሲሉ የገጠማቸውን ይገልፃሉ።
እነዚህ ሁሉ ወንጀሎችን ማጥራት ካልተቻለ መንግስት የሚያደርገው የነዳጅ ድጎማ ለወንጀለኞች ሲሳይ ከመሆን አይተርፍም።
የዳሎል ነዳጅ ማደያ ባለቤት የሆኑት ደሳለኝ አበባየሁ እንደሚሉት አብዛኛው የመንግስት ድጎማ በሚውልበት አዲስ አበባ ነዳጅ በሊትር እስከ 25 ብር እየተሸጠ መሆኑን ይገልፃሉ። በቃለ መጠይቁ ወቅት ለስራ ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኙ የነብሩት አቶ ደሳለኝ አርሶ አደሮች ለእርሻ ለሚጠቀሟቸው ማሽኖች ነዳጅ በሊትር እስከ 53 ብር ሲሸምቱ መታዘባቸዉን ነግረዉናል።
“ከ80 በመቶ የሚበልጠው ህዝብ የሚኖርበት ገጠር የሚገኙ አርሶ አደሮች ችለው ከገዙት በከተማ ያለው ከዚያ ባነሰ ዋጋ መግዛት አይችልም ብዬ አላስብም።” ብለዋል የዳሎል ነዳጅ ማደያ ባለቤት።
የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ መነሳት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚሉት ለአራት አስርት ዓመታት በዘርፉ የቆዩት የነዳጅ ነጋዴ “አብዛኛው ጉዳት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ የሚወድቅ ነው። ከህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ጀምሮ የግብርና ምርቶችና ሌሎች መጓጓዣ የሚያስፈልግላቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ ይጨምራሉ” ብለው “ቢሆንም ዝርፊያውን መቆጣጠር ከተቻለ ዋጋው የሚከብድ አይሆንም ስለዚህ የድጎማው መነሳት የግዴታ ነው” ብለዋል።
አቶ ደሳለኝ አበባየሁም በእዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። “በእኔ እይታ የነዳጅ ዋጋ ድጎማው በፍጥነት መነሳት አለበት። ለነዳጅ ሲውል የነበረ በቢልየን የሚቆጠር ገንዘብም ወደ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እና ሌሎች አንገብጋቢ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት መዋል ይገባዋል” ብለዋል አቶ ደሳለኝ።
ይሁን እንጂ የህዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ የሚያገኘው ድጎማ መቀጠል አለበት የሚሉት የዳሎል ነዳጅ ማደያ ባለቤት፤ ይህ ካልሆነ ጉዳቱ በትራንስፖርት አቅራቢዎችም በህዝቡም ላይ የከፋ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ለዓመታት በነዳጅ ገበያ ላይ የቆዩት ግለሰብ እንደሚገልፁት ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ባህል መስተካከል ዋነኛው መፍትሄ ነው። “የተወሰኑ ባለሀብቶች በሚልየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ አድርገው ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቧቸው ተሽከርካሪዎች ነዳጅ የማይቆጥቡ በመሆናቸው በእዚህ አካሄድ የነዳጅ ችግርን በዘላቂነት መፍታት አይታሰብም” ብለዋል። ባለሙያው አክለውም የሀገሪቱ ህዝብ በአንድ ድሃ ሀገር ውስጥ እንደሚኖር ሰው መኖር መልመድ ካልቻሉ በድሃው ላይ የሚፈጠረው ተፅእኖ እያደገ እንዲሄድ ያደርጋል።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አብዱልመናን “የሚፈጠረው የዋጋ መናር የዜጎችን ኪስ የሚበዘብዝ ነው። ይህ ደግሞ የዋጋ ውድነቱን ያገናዘበ ገንዘብ ለነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ጊዜያዊ ወጪ እንዲመድብ መንግስትን ያስገድዳል” ብሏል። በተጨማሪም የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ በህዝብ ትራስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ መቋረጥ ስለሌበት መንግስት ድጎማውን በተመረጡ ተሽከርካሪዎች ላይ መተግበር ይኖርበታል ብለዋል ባለሙያው።
አዲስ ዘይቤ ያናገረቻቸው ሁሉም ባለሙያዎች የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚፈጠው የነዳጅ ምርት እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ መዘጋጀት እንዳለበት ይስማማሉ። በተጨማሪም በሀገሪቱ በሚገኙት የነዳጅ ማከማቻ ስፍራዎች በቂ ተቀማጭ ሊኖረው እንደሚገባ የነዳጅ ዘርፉ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።