የካቲት 29 ፣ 2014

በሶማሌ ክልል የእርዳታ እህል የዘረፉ አመራሮች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

City: Somaliዜና

የምግብ ዘይት በመዝረፍ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የተጠረጠሩ ሦስት አመራሮችና አንድ ግብረአበራቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈባቸው።

Avatar: Abdi Ismail
አብዲ ኢስማኤል

Abdi Ismail is Addis Zeybe's correspondent in Somali regional state

በሶማሌ ክልል የእርዳታ እህል የዘረፉ አመራሮች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ
Camera Icon

ፎቶ፡ አብይ ሰለሞን

በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የአፍዴር ዞን ጎድጎድ ወረዳ ማኅበረሰብ ነዋሪዎች ሊታደል የተዘጋጀ 30 ኩንታል ሩዝ፣ 25 ኩንታል ስኳር፣ 5 ባለ 20 ሊትር የምግብ ዘይት በመዝረፍ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የተጠረጠሩ ሦስት አመራሮችና አንድ ግብረአበራቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈባቸው።

በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት አመራሮች የአፍዴር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ፣ የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም በአፍሬር ዞን የጎድጎድ ወረዳ አደጋ ሥራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም የተዘረፈውን የምግብ ግብአት በመግዛት የወንጀል ተባባሪ የሆነ ግለሰብ መሆናቸው ታውቋል።

በሶማሌ ክልል የአፍዴር ዞን 1ኛ ደረጃ መደበኛ ፍርድ ቤት ሊቀመንበር አቶ አህመድ ፋራህ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት አመራሮቹና ተባባሪያቸው ለአፍዴር ዞን ጎድጎድ ወረዳ ማኅበረሰብ የድርቅ ተጎጂዎች የተዘጋጀውን 30 ኩንታል ሩዝ፣ 25 ኩንታል ስኳር፣ 5 ባለ 20 ሊትር የምግብ ዘይት በመዝረፍ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል።

የአፍዴር ዞን 1ኛ ደረጃ መደበኛ ፍርድ ቤት ሊቀ መንበር አቶ አህመድ ፋራህ ተጠርጣሪዎቹ አዋጅ ቁጥር 881/2015 አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በሙስና ወንጀል ድንጋጌዎች ስር የተደነገጉትን በሥልጣን አላግባብ መገልገል ክልከላዎች በመተላለፍ ክስ እንደተመሰረተባቸው ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

አመራሮቹ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ15 ሺህ ብር እንዲቀጡ ፍርድቤት ወስኗል። በተጨማሪም የተዘረፉትን የእርዳታ ምግቦች በመግዛት በጥፋት ተባባሪነት የተከሰሰው ግለሰብ በሌለበት በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ15 ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበታል።

በሶማሌ እና በኦሮምያ ክልሎች ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመታት የሚጠበቅ ዝናብ ባለመዝነቡ ባጋጠመው ድርቅ በሶማሌ ክልል ፋፋን እና ሲቲ ዞኖች ከፍተኛ የምርት እጥረት ማጋጠሙን የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ አስታውቋል። በርካታ አርብቶ አደሮችና፣ አርሶ አደር አርብቶ አደሮች በዋናነት ከቆራሄይ፣ ጃረር፣ ኤረር እና ኖጎብ ዞኖችና በፋፋን ዞን በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ለግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ መሰደዳቸውን፣ በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል 2.3 ሚሊዮን እና ከ870,000 በላይ ደግሞ በደቡብ ኦሮሚያ በአጠቃላይ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለውሃ እጥረት መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) በሪፖርቱ አስፍሯል።

በድርቁ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እና የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር ባለመኖሩ በሶማሌ 99 ሺህ ተማሪዎች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ 56 ሺህ ተማሪዎች በአጠቃላይ 155 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ በሁሉም ድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ከ6.4 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ሰዎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ኦቻ አስታውቋል። ከእነዚህም መካከል ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉት ዜጎች በሶማሌ ክልል የሚገኙ ናቸው።

በያዝነው ዓመት በሶማሌ እና በኦሮምያ ክልሎች ባለፉት 40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ማጋጠሙ በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል። የዓለም አቀፉ የልማት ድርጅት ዩኤስኤይድ እንዳስታወቀው የክልሎቹ ነዋሪዎች የኑሯቸው መሰረት የሆኑት እንስሳቶቻቸው ምግብ በማጣት ምክንያት በከፍተኛ መጠን እየሞቱ ይገኛሉ። ሁኔታውን ያስተዋለው ዓለም አቀፉ ነብስ አድን ኮሚቴም በደቡበ ምሥራቅ ኢትዮጵያና በሶማሊያ በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከታዩት የከፋ ድርቅ እንዳጋጠማቸውና በእነዚህ አካካቢዎች ለሰብዓዊ ቀውስ መባባስ ምክንያት መሆኑንም በቅርብ ጊዜ ባደረገው ግምገማ መመልከቱንም በሪፖርቱ አስታውቋል።

አስተያየት