አወቀ አራርሶ የ27 ዓመት ወጣት ነው። ከ6 ዓመታት በላይ የጎዳና ተዳዳሪ ሆኖ አሳልፏል። በራሱ አነሳሽነት በሐዋሳ ከተማ የሚገኙ ጽዳት የጎደላቸውን አካባቢዎች በማጽዳትና አረንጓዴ በማልበስ ይታወቃል። የተደፈኑ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን ከፍቶ፣ ተገቢ ያልሆነ ቦታ የተጣለ ደረቅ ቆሻሻ አንስቶ፣ ህዝብ በሚበዛባቸው መተላለፊያ ቦታዎች የተጠራቀመ ፍሳሽ ቆሻሻን አስወግዶ ንጹህና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር ጥሯል። የጸዳው አካባቢ ድጋሚ እንዳይበላሽ ከማጠር ጀምሮ አረንጓዴ የማልበስና የአካባቢው ነዋሪ ድጋሚ እንደዳያበላሸው የማስተማር ስራ ስለመስራቱ ተመስክሮለታል።
ትውልዱ እና እድገቱ በደቡብ ክልል ዲላ ዞን ጨርሶ ወረዳ እንደሆነ የሚናገረው አወቀ ከተወለደበት ቀዬ ወጥቶ ሐዋሳ መኖር የጀመረው ከ2002 ዓ.ም. አንስቶ ነው። “ሐዋሳ ለመኖር የወሰንኩት የተሻለ ሥራ ለማግኘት ነው። የምበላው፣ የምጠጣው፣ የምለብሰው ስላልነበረኝ ጉልበቴን እና እውቀቴን ተጠቅሜ በሥራ ራሴን ለማሸነፍ ሐዋሳ ከተማ ገባሁ” ይላል። ይሁን እንጂ ተስፋ ሰንቆ የተጓዘባት ሐዋሳ በጠበቀው መልኩ አልተቀበለችውም። ከ6 ዓመታት በላይ ህይወቱን በጎዳና ላይ ለመምራት ተገደደ። “በ2008 ዓ.ም. ከጎዳና ህይወት እስከተላቀቅኩበት ጊዜ ድረስ ጎዳና ተዳዳሪ ነበርኩ” ሲል ያለፈበትን የህይወት መስመር ያስረዳል።
አወቀ ከማንም ወገን ከፍያ እና ምስጋና ሳይጠብቅ በራሱ አነሳሽነት ለፈጸመው በጎ ተግባር ከቀበሌ እስከ ፌደራል ባሉ መስሪያቤቶች ከ100 በላይ የምስክር ወረቀት አግኝቷል። ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት የምስክር ወረቀቶቹን ጨምሮ 5 ሜዳልያ መሸለሙን ይናገራል። ከሜዳልያ ሽልማቶቹ መካከል የሲዳማ ክልል ተጽእኖ ፈጣሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣት በሚል በ2012 ዓ.ም. የተበረከተለት ሜዳልያ ይገኝበታል። ሽልማቱን ያገኘው ከጽዳት ሥራው በተጨማሪ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ሴቶችና በጎዳና ህይወት ለሚኖሩ ወጣቶች የሥራ እድል በማመቻቸቱ ነው። የአካባቢውን ነዋሪዎችና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ሻይ ቡና በማቅረብ፣ ችግኝ በማፍላት፣ በልብስ አጠባ፣ ሱቅ በደረቴ፣ ሊስትሮ ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ያገዛቸው ሰዎች ቁጥር ከ151 በላይ ነው።
“የተገኘሁት ከድሃ ቤተሰብ ነው። ለቤተሰቡ 3ኛ ልጅ ነኝ። አንድ ወንድም እና 5 እህቶች አሉኝ። ቤታችን ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ አልነበረም። ችግሩ ሲበረታብኝ ሐዋሳ ለመሄድ ቆረጥኩ” ይላል። በአሁን ሰዓት ወንድሞቹ እና እህቶቹ የትእንዳሉ የማያውቀው ወጣቱ በየሐገሩ መበታተናቸው እንደሚያቆጨው አጫውቶናል።
ለ6 ዓመታት የኖረበት የጎዳና ህይወት አስከፊ እንደነበረም ያነሳል። “ስለ ጎዳና ህይወት ሲነሳ ብርዱ፣ ረሃቡ፣ ሱሱ እየተባለ ይወራል። ነገር ግን እንደሚነገረው ቀላል አይደለም። ሁሉም ነገር ከምንናገረው በላይ ከባድ ነው” ሲል ያስታውሳል።
በሐዋሳ ከተማ በተለምዶ አሮጌዉ መናኸሪያ ጀርባ እና ጫት ተራ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ከመንገደኛው የሚጣል ቆሻሻ የተጠራቀመባቸውን መጥፎ ጠረን ያስከተሉ ቦታዎች በራሱ ተነሳሽነት ወደ አረንጓዴ ስፍራነት ቀይሯቸዋል። በተጨማሪም የሺ ሆቴል አካባቢ፣ ሐዋሳ ዮኒቨርሲቲ ፊት ለፊት እና ሌሎችም አካባቢዎች ጓደኞቹን በማስተባበር የጽዳት ዘመቻውን ካከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ለ5 ዓመታት በጎዳና ህይወት ኑሮውን የገፋው አየለ አበበ በአወቀ አማካኝነት ራሳቸውን ከቀየሩ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። “አሁን ከጎዳና ወጥቻለሁ። ራሴን የማስተዳድረው ልብስ በማጠብ ነው። የአካባቢዬ ነዋሪዎች የሚያመጡልኝን አልባሳት አጥቤ፣ አድርቄ እመልሳለሁ። ለአገልግሎቴም ለአንድ ልብስ ከ5 እስከ 10 ብር እቀበላለሁ” ብሎናል። የሥራውን ሐሳብ ያመጣለትን እና መሳሪያዎችን ያሟላለትን አወቀን የሚያመሰግነው አየለ የጎዳና ልጆች እገዛ ካገኙ ራሳቸውን መቀየር እንደሚችሉ ሁሉም ሰው እንዲረዳለት ይፈልጋል።
በስድስት ዓመታት በጎዳና ላይ ቆይታው ከሰባት በላይ የልብ ጓደኞችን ማፍራት ችሏል። የፅዳት ስራውን ሲያስብ ከውጥኑ እስከ ተግባራዊነቱ ያገዙት እነርሱ መሆናቸውን ይናገራል። ራቅ ካለ አካባቢ ተቆፍሮ የሚመጣውን ለአትክልት የሚሆን ለም አፈር በማጓጓዝ፣ የጽዳት ሥራውን በማገዝ፣ ችግኝ በማፈላለግ እና አጠቃላይ ሥራውን በመደገፍ ከጎኑ ነበሩ። “የምከፍላቸው ነገር አልነበረኝም። ክፍያ ሳይጠብቁ አብረውኝ ባይሆኑ የሰራሁትን ልሰራ አልችልም ነበር” ሲል ራዕዩን የተጋሩትን ጓደኞቹን አመስግኗል። “ከአጋር ድርጅቶች በሚገኝ እርዳታ ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረጌ፣ ከጎዳና ህይወት በማላቀቄ ግን ኩራት ይሰማኛል” ይላል።
ሥራውን ለመስራት የተነሳሳበትን ሁኔታ ሲያስረዳ “በመጀመርያ ለራሴ ደስታ ስል ጀመርኩት። የምውልበትና የማድርበት ቦታ መቆሸሽ የለበትም ስል ተነሳሁ። እየቀጠለ ሲሄድ ለአካባቢው ነዋሪዎች ብሎም ለከተማዋ ተረፈ” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።
አወቀ ሌሎችን ከመርዳት በተጨማሪ ራሱን የሚያስተዳድረው በችግኝ ማፍላት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ያጋጠመው የውሃ ችግር ለሥራው እንቅፋት መሆኑን ይናገራል። “ችግራችንን እንዲፈቱልን የተለያዩ የመንግሥት አካላትን በር አኳኩተናል። መፍትሄ ግን አላገኘንም። አሁን ላይ ችግኞቹ ደርቀዉ ጠፍተዋል። በፊት የተለያዩ አተክልቶችን ለማኅበረሰብ የማቅረብ እተዳደር ነበር” ብሎናል።
“የጎዳናን ህይወት በድጋሚ ዕንዳላየው እፈራለሁ። መስራት እየቻልኩ መስራት አለመቻሌም ያሳዝነኛል” የሚለው አወቀ የእኔን ብቻ ሳይሆን የሌሎችን በጎዳና የሚገኙ እንዲሁም ጎዳና ለመውጣት ጫፍ ላይ ያሉ ሰዎችን የሚያግዝ የበጎ አድራጎት ድርጅት የማቋቋም ሐሳብ አለው።
“በጸጋ” የሚል ስያሜ ያወጣለት የበጎ አድራጎት ማኅበር ችግረኛ አዛውንቶችኝ፣ ኑሯቸዉን በጎዳና ላይ ያደረጉ ወጣቶችን እና ሴተኛ አዳሪዎችን ይረዳል የሚል ራዕይ ሰንቋል።
ተሸላሚውን በጎ ፈቃደኛ ወጣት በተመለከተ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የምስራቅ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ግርማ አርባቻ ወጣቶቹን መርዳት የሁሉም ሰው ኃላፊነት ስለመሆኑ ተናግረዋል። “ኑሯቸውን ጎዳና አድርገው በጽዳት እና በአረንጓዴ ልማት እንዲሁም በበጎ አድራጎት ላይ የተሰማሩትን ወጣቶች መርዳት የሁሉም ሰው ኃላፊነት ነው” ያሉ ሲሆን ክፍለ ከተማው ልጆቹን ለማገዝ እየጣረ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ሥራቸውን እስከማቆም ያደረሳቸውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ከውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ላይ ስለመሆናቸውም ኃላፊው ተናግረዋል። ክፍለ ከተማው ለተሸላሚው ወጣት የቀበሌ ቤት መስጠቱም የእገዛው አንድ አካል ነው።