ፓጋ ግሩፕ የተሰኘ የናይጄሪያ የፋይናንስ ኩባንያ ከአቢሲንያ ባንክ ጋር በመተባበር ኦንላይን የክፍያ ስርዓት መጀመራቸውን አብስረዋል። የፋይናንስ ተቋማቱ ስምምነት በብሔራዊ ባንክ በተፈቀዱ የኦንላይን ክፍያ እና የገንዘብ ዝውውር መመሪያዎች መሰረት ይፋ የተደረገ መሆኑን ፓጋ ግሩፕ አስታዉቋል።
ፓጋ የሚጀምረው አገልግሎት በኦንላይን ስርዓት መገበያየት፣ ክፍያዎችን መፈፀም እንዲሁም ገንዘብ ማተላለፍን የሚከውን ነዉ። ይህ አሰራር ለንግዱ ማህበረሰብ እና ለደንበኞች የገንዘብ እንቅስቃሴን ከማቅለሉም በተጨማሪም ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ያግዛል ተብሏል።
የፓጋ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አዳም አባተ እንደገለፁት “በኢትዮጵያ ረጅም የስራ ታሪክ ያለው ፓጋ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የጎላ ሚናውን እየተወጣ ከሚገኘው አቢሲንያ ባንክ ጋር መጣመራችን፤ በቀጣይ በፈጠራ የታገዘ የክፍያ እና የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የተሻለ እድል ነው” ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም ፓጋ እና አቢሲንያ ባንክ በጋራ የሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች ለኢትዮጵያውን ደንበኞችና የንግድ ድርጅቶች ጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
የአቢሲንያ ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ኃላፊ የሆኑት ሶስና መንገሻ በበኩሏ፤ “ፓጋ የሚሰራቸው የፈጠራና የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያሰፉ ተግባራት አስፈላጊ በመሆናቸው፤ የኦንላይን ክፍያ ስርዓታቸውን ለኢትዮጵያውያን ማቅረብ በመቻላችን ደስተኛ ነን” ብላለች።
እ.አ.አ በ2009 ገበያዉን የተቀላቀለው ፓጋ ግሩፕ በናይጄሪያ ከ18 ሚልየን በላይን ደንበኞች አሉት። ፓጋ ግሩፕ ደንበኞች በስልክ ቁጥር ብቻ፣ በአቅራቢያቸው ከሚኖሩ ወኪሎች እንዲሁም ኤቲኤም ማሽኖችን ያለ ካርድ በእጅ ስልክ በማዘዝ ገንዘብ የማንቀሳቀስና ክፍያ የመፈፀም አገልግሎት በማቅረብ የሚታወቅ ነው።
በ1988 ዓ.ም. የባንክ ስራውን የጀመረው አቢሲን ያ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ670 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ከ6.3 ሚልየን በላይ ደንበኞችም አሉት። አቢሲን ያ ባንክ በቅርቡ ስራ ላይ ካዋላቸው አሰራሮች ውስጥ የቨርቹዋል ባንኪንግ እንዲሁም ለዓይነ ስውራን በድምፅ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጡ አዉቶማቲክ ማሽን (ኤቲኤም) ይጠቀሳሉ።