የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በቀላሉ የማይታከም ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳደረሰ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቀድሞውንም በማሻቀብ ላይ የነበረውን የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ጦርነቱ ይበልጥ አባብሶታል። ጦርነቱ ከፍ ያለ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ካስከተለባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ደሴ አንደኛዋ ምናልባትም ዋነኛዋ ተብላ ልትጠቀስ ትችላለች። በጦርነቱ የወደሙትን፣ የተበላሹትን፣ ከፊል ጉዳት የደረሰባቸውን ወደቀደመ አገልግሎታቸው እንዲመለሱ ከማድረግ በተጨማሪ የዕለት ደራሽ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የከተማ እና የገጠር ተፈናቃዮች ማቋቋም የከተማዋ ብቻ ሳይሆን የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት አስቸኳይ የቤት ስራ ሆኖ ይገኛል።
መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች፣ የሰብል ምርቶችን ጨምሮ ሌሎችም ምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ “የማይቀመስ” የሚባልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። የዋጋው ጉዳይ ከጦርነቱ በፊት፣ በጦርነቱ ወቅት እና ከጦርነቱ በኋላ ሦስት ዓይነት መልክ እንዳለው ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ።
አቶ አያሌው ደበበ በደሴ ከተማ በቧንቧ ውሃ ክፍለከተማ ነዋሪ ናቸው። በግል ስራ የሚተዳደሩት የ53 ዓመት ጎልማሳ “ወራሪው ኃይል ከከተማችን ከወጣ በኋላም የሸቀጦች ዋጋ አልቀነሰም” ይላሉ። የህወሓት ጦር ደሴ ከተማን በተቆጣጠረበት ወቅት የሸቀጦች ዋጋ በፊት ከነበረበት ጭማሪ ማሳየቱን የሚናገሩት አቶ አያሌው ከጦርነቱ በኋላም ትርጉም ያለው ቅናሽ አለማሳየቱ ግልጽ ምክንያት እንደሌለው ያስቀምጣሉ። ሐሳባቸውን በምሳሌ ሲያስረዱ
“ለምሳሌ ከወረራው በፊት አንድ የጾም በየዓይነት ከ30-35 ብር ይሸጥ ነበር። በወረራው ወቅት ከ80-100 ብር ተሸጧል። አሁን ላይ ያለው ዋጋ በወረራው ጊዜ እንደነበረው ነው። የጀበና ቡና ከ5ብር ወደ 10ብር፣ ደረቅ እንጀራ ከ10ብር ወደ 15 ብር፣ ስኳር ከ35 ብር ወደ 70 ብር፣ ማኪያቶ ከ13ብር ወደ 25 ብር፣ የልብስ ሳሙና ከ25 ብር ወደ 35 ብር ክፍ ብለው እየተሸጡ ይገኛል”
ያሉ ሲሆን በተጨማሪም በተጋነነው የዋጋ ንረት ምክንያት ነዋሪው እየተማረረ መሆኑን አንስተዋል። መንግሥት ምንጩን በማጥናት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድም አሳስበዋል። የኑሮ ጫና ውስጥ የሚገኘው ነዋሪ ጫናውን መቋቋም ከሚችልበት ደረጃ በላይ ሲሆን ጣቱን ወደ መንግሥት መጠቆሙ እንደማይቀር በማስታወስም “ሳይቃጠል በቅጠል” ሊባል ይገባል ሲሉ መክረዋል።
“ሮቢት ገበያ” የሚባለው የግብይት ስፍራ ላይ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ የተሰማራችው ወጣት ኢክራም ሙሀመድም “እቃው ዋጋ ጨምሮ ነው የሚመጣው። አከፋፋዮች ጨምረው ሲያስረክቡን እኛም ተጠቃሚው ላይ እንጨምራለን” ብላለች። “ተጠቃሚው የጭማሪው ምክንያት ቸርቻሪ ነጋዴው ይመስለዋል። ችግሩን የፈጠርነው ግን እኛ አይደለንም” ትላለች።
መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ በሂሳብ ባለሙያነት የሚያገለግሉት አቶ ምህረት ዋልተንጉሥ በበኩላቸው “መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ገበያውን ማረጋጋት አለበት” ይላሉ። እንደ አቶ ምህረት አባባል መንግሥት እንደ ነዳጅ ያሉ ምርቶች ግብይት ላይ ጣልቃ በመግባት ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት እንደሚያደርገው ሁሉ ሌሎች ምርቶች ላይ እጁን አስገብቶ መቆጣጠር ይኖርበታል። የገበያው አንቀሳቃሾች ግልጽ አሰራር ተዘርግቶላቸው ሥራቸውን ከትርፍ አንጻር ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰብን ከማገልገል እና ሐገርን ከማስቀጠል አንጻር እንዲሰሩ ማነቃቃት ይገባል። አቶ ምህረት ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ፡- “የሸማቾች ማኅበራት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች በፍጥነት ወደ አገልግሎት ሊገቡ ይገባል” ብለዋል።
ቤተልሄም ዓለማየሁ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ዲፓርትመንት የ3ኛ ዓመት ተማሪ ነች። በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ የደሴ ከተማ የኑሮ ውድነት አሳሳቢ ሊባል የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አንስታለች። “መንግሥት ችላ ያለው ይመስላል” የምትለው ቤተልሄም አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ የሚከሰተው ቀውስ ከፍ ያለ እንደሚሆን ያላትን ስጋት ተናግራለች።
የወሎ ዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ አቶ አህመድ አብዱልቃድር በበኩላቸው የዋጋ ንረትን የሚፈጥረው የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን መሆኑን በማስረዳት ይጀምራሉ። የምርት ማነስ እና የገንዘብ አቅርቦት መብዛት የዋጋ ንረተን የሚያስከትሉ ሰበቦች ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።
“ጦርነቱ የሰብል ምርቶች በበቂ መጠን እንዳይሰበሰቡ በማስገደዱ ምርት አንሷል። የፈላጊው ቁጥር ደግሞ በፊት ከነበረው ጨምሯል። ይህ የዋጋ ንረትን የሚያስከትል አንድ ምክንያት ነው። ሌላው ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በፊት የነበራት ዓመታዊ የገንዘብ አቅርቦት 67 ቢልየን ብር ነበር። ዓመታዊ የገንዘብ አቅርቦቱ አሁን ላይ ያለው 1 ትሪሊየን ደርሷል። ይህ የሚያሳየው ገበያው ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት እንዳለ ነው። ክስተቱ የዋጋ ንረቱን በከፍተኛ መጠን ያባብሰዋል። ገዢው ከኢኮኖሚው አቅም በላይ የሆነ ከፍተኛ ገንዘብ በከፈለ ቁጥር የገንዘብ ፍሰቱ የዋጋ ንረቱን ያባብሰዋል” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የነጋዴዎች ያለአግባብ ምርትን ማከማቸት፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የጥቁር ገበያ መስፋፋት፣ የሰዎች ምክንያታዊ ያልሆነ የእቃ ግዢ፣ በሰላም ማጣት ምክንያት የሚፈጠር ተቋማዊ ውድቀት እና መሰል ምክንያቶች የዋጋ ንረትን የመፍጠር እና የማባባስ እድል እንዳላቸው በምጣኔ ሐብት መምህሩ የተዘረዘሩ ምክንያቶች ናቸው።
የኢኮኖሚክስ መምህሩ እና ተመራማሪው አቶ አህመድ በደሴ ከተማ እንደተከሰተው ዓይነት የዋጋ ንረት ሲያጋጥም መንግሥት መውሰድ የሚገባውን እርምጃ በተመለከተ ሲናገሩ ሕገ-ወጦችን መቆጣጠር፣ ተቋማትን ማጠናከር፣ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ማቋቋም እንደሚገባ መክረዋል።
“በእንአዚህ ዓይነት ወቅት ከመንግስት የሚጠበቀው፣ ምርቶችን በማኅበራት በኩል ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማድረግ አንዱ ነው። ሕገ-ወጦችን መቆጣጠር፣ ጥቁር ገበያን መቆጣጠር እና የማያዳግም ርምጃ መውሰድ፣ መንግስት ተቋማቱን በመገምገም መዋቅራዊ ማሻሻዎች ማድረግ፣ በጦርነት የተጎዳ አካባቢ ላይ ምርት እንዲጨምር ማድረግ፣ ሌሎች ቦታዎች ላይ ትርፍ የሆኑ (ከበቂ በላይ ያሉ ወይም የማይፈለጉ) ምርቶችን ጉዳት ወዳለባቸው አካባቢዎች መውሰድ፣ የተፈናቀለ ማኅበረሰብ ካለ ወደ አካባቢው እንዲመለስ ማድረግ፣ የህዝብ ብዛትን የሚቆጣጠር ፖሊሲ ማውጣት እና የመሳሰሉት ናቸው” በማለት ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
አቶ ይማም ሰይድ የደሴ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ ናቸው። ወራሪ ቡድኑ በደሴ ከተማ በነበረው ቆይታ ሕጋዊ የንግድ ሰንሰለቱ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ እንደነበር ይናገራሉ። በዚህ ምከንያት የጎዳና ላይ ንግድ መስፋፋት፣ ሕግን ተከትለው የሚሰሩ ነጋዴዎች በገበያው ላይ የገጠማቸውን ፈተና ለመቋቋም አለመቻላቸው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደነበር ይናገራሉ።
"የከተማ ደንብ ማስከበርና የንግድና ገበያ ልማት የስራ ቡድኖችና መምሪያው እንደ ተቋም መደበኛ አገልግሎቱን መስጠት አልቻለም። የቢሮ ቁሳቁሶች ውድመትና ዝርፊያም ተከስቶባቸዋል። የንግድ ቁጥጥሩ የሚካሄድበት ሲስተምም ስላልነበር ሕጋዊውን እና ሕገ-ወጡን መቆጣጠር አልተቻለም። አሁን በርካታ የንግድ ድርጅቶች አገልግሎታቸውን ጀምረዋል። የጠቀስነው የቁጥጥር ሥርዓት አለመጀመር ግን ዋጋ በዘፈቀደ እንዲጫንና ሕገ-ወጥነት እንዲበራከት ምክንያት ሆኗል። የመሠረታዊ ምርቶችና ሸቀጦች አቅርቦትም አልነበረም። አሁን የተለያዩ ድርጅቶች ደብዳቤ እየተጻፈላቸው ለሕብረተሰቡ ከተለያዩ አካባቢዎች እያመጡ እንዲያሰራጩ በተደረገ ሙከራ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ጥረት ተደርጓል። ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግሥት በመመደብ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማማሟላት እየተሠራ ነው” ብለዋል።
ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ ጤፍ እና ከ8መቶ ኩንታል በላይ ዱቄት በሸማች ማኅበራት እንዲቀርቡ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል። ወደፌትም ወሳኝ የሚባሉ መሠረታዊ ፍጆታወችን ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ እንደሚሰራ አቶ ይማም ተናግረዋል።
በከተማዋ ከቤንዚንና ነዳጅ አቅርቦት ጋር የሚነሳውን ችግር ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑንና በዚህም ከነዳጅ ማደያ ባለሀብቶች ጋር ውይይት የተደረገ መሆኑን ተናግረው አቅርቦት እያለ እጥረት የሚፈጥር አካል ካለ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል። የተቋሙ የቁጥጥር ሰራተኞች በማደያዎች ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን የገለጹት አቶ ይማም “ተግባሩ ተጠናቅሮ ይቀጥላል። የሚታየውን የሕገ-ወጥ ንግድ ለመቆጣጠር እቅድ በማውጣት ወደ ተግባር ገብተናል። መምሪያውን ጨምሮ 10 ማእከላትን ወደ ሰራ በማሰገባት ሕገ-ወጥ የቡና ንግድ የጎዳና ላይ ንግድና ካለ ንግድ ፈቃድ የሚሰሩ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥርር እየተደረገ መሆኑን፣ ከዚህ በፊት ይነሳ የነበረውን ሕገ-ወጥ የቡና ንግድ ለመቆጣጠር ከ120 ነጋዴዎች ጋር በመወያየትና ኮሚቴዎችን በመዋቀር ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ንግድ ፈቃድ ባላደሱና ንግድ ፈቃድ በሌላቸው ነጋዴዎችም ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የገለጹት አቶ ይማም በከተማዋ የተንሰራፋውን ሕገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎል የተባለ ሲሆን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ስራ ይገባል። ከጸጥታ ኃይሎች፣ ከደንብ ማሰከበር ጋር በመተባበር ሕገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ለማስቆም ወደ ተግባር እንደሚገባ ተገልጿል።