የካቲት 22 ፣ 2014

ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ያሸነፉት የአለምን ህግ ነበር

City: Addis Ababaታሪክ

ያኔ ጥቁር ህዝቦች እንደእንስሣ ከመቆጠራቸው ብዛት የተነሳ “ጥቁሮችን ረግጦ መግዛት የነጮች እዳ ነው” ይባል ነበር። ኢትዮጵያውያን ይህንን የአለም ህግ አድዋ ላይ ሻሩት።

Avatar: Yirga Gelaw
Yirga Gelaw

Yirga Gelaw is an academic, multidisciplinary researcher and writer. He researches African experience and Ethiopian traditions. He has won university and industry awards for his teaching, research, and creative writing.

ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ያሸነፉት የአለምን ህግ ነበር
Camera Icon

Credit: Getty Images (Painting of Emperor Menilik II at the Battle of Adwa 1896)

የሃገራችን ህዝቦች መልካቸውም፣ ባህላቸውም፣ ሃይማኖታቸውም፣ ቋንቋቸውም፣ ታሪካቸውም፣ ፍላጎታቸውም፣ ስነልቦናቸውም.... ተመሳሳይ ነው። ተመሳሳይ ማለት “አንድ” ማለት አይደለም። ልክ ከአንድ ምድር ላይ እንደሚበቅሉ ልዩ ልዩ እጽዋት፣ ልክ ከአንድ የቤተሰብ ግንድ እንደሚመዘዙ የተለያዩ ልጆች፣ ምንጫቸው ላይ፣ የማንነታቸው ንጥረነገር ውስጥ አንድ የሚያደርጋቸው መሰረት አለ። አድዋ የዚህ የአንድነት መሰረት ገሃዳዊ መገለጫ ነው። አድዋ የሃገራችንን ልዩ ልዩ ህዝቦች አንድነት ያስመሰከረ ብቻ ሳይሆን፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከወራሪ ቅኝ ገዢዎች ጋር ያላትን ልዩነት አንጥሮ ያወጣ የድል ቀን ነው።

የአድዋ ጦርነት አይቀሬ ነበር። ምክንያቱም የሃገራችን ህዝቦች ያላቸው ስነልቦና፣ ቋንቋ፣ አስተሳሰብ፣ እምነት፣ ባህል፣ ፍላጎት ሁሉ ጣልያን ከአውሮፓ ይዞት ከመጣው የተለየና ተቃራኒ ስለነበረ ነው። በመላው አለም “አውሮፓን የሚቃረን ማንነት ሁሉ ለአውሮፓ መገዛት ወይ መጥፋት አለበት” የሚል እምነት ገኖ ነበር። ስለዚህ በአድዋ የገጠሙት ኢትዮጵያዊነትና አውሮፓዊነት ነበሩ። የጦርነቱ ጎራ “ኢትዮጵያ ያለአውሮፓዊነት ሃገር ልትባል አይገባትም፣ ወደፊትም አትሆንም፤” በሚልና “ኢትዮጵያ ከአውሮፓ በፊት ሃገር ሆና ኖራለች፣ ወደፊትም ትኖራለች፤” በሚል የእምነት ልዩነት ላይ የተሰመረ ነበር። ጦርነቱ እአአ በ1884 በበርሊን ኮንፈረንስ በተወሰነው የአለማቀፍ የቅኝ አገዛዝ ህግና፣ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺህ አመታት ሃገር ሆነው በኖሩበት ህግ መካከል የተካሄደ ጦርነት ነበር። 

ያኔ ጥቁር ህዝቦች እንደእንስሣ ከመቆጠራቸው ብዛት የተነሳ “ጥቁሮችን ረግጦ መግዛት የነጮች እዳ ነው” ይባል ነበር። ኢትዮጵያውያን ይህንን የአለም ህግ አድዋ ላይ ሻሩት። ሴቶች፣ ወንዶች፣ ቄሶች፣ ሼኮች፥ ገበሬዎች፣ መኳንንቶች፣ የልዩ ልዩ ነገድ ተወላጆች፣ ልዩነታቸው ከአንድ ቆዳ ላይ እንዳለ ዥንጉርጉር ቀለም ሆነ። ተመሳሳይ በሆነው ሃገርበቀል ህይወታቸውና፣ ይህንን ህይወት ሊያጠፋ በመጣው ባእድ መካከል ባላቸው ልዩነት ላይ ብዥታ አልነበራቸውም። ድላቸው፣ በምድር ላይ ለጥቁሮች እጅግ ውድ የሆነውን ነገር አተረፈ። ነጭ ሳይሆኑ ሰው መሆን፣ አውሮፓን ሳይከተሉ ሃገር መሆን፤ ያለፈውን እያጠፉ ሳይሆን ባለፈው ነገር እያሸነፉ ወደፊት መጓዝ እንደሚቻል ለአለም አሳዩ። 

ከ50 አመታት በኋላ ግን የአድዋን መንፈስ የሚቃረን ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። አድዋ ላይ ያሸነፉት የጠላት ማንነት ሱፍ ለብሶ፣ ብእር ጨብጦ፣ የራሱን ቋንቋ፣ የራሱን እውቀትና ፍላጎት የጥቂት ኢትዮጵያውያን እምነትና ፍላጎት አድርጎ መሃል ከተማ ላይ ነገሰ። በጠመንጃ አልገዛም ያለ ህዝብ፣ እንስሣ አይደለሁም ያለ ህዝብ፣ የማሳድጋቸው የማበለጽጋቸው የራሴ የሆኑ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ ፈጠራዎች፣ ጥበቦች፣ ባህሎች አሉኝ ያለ ህዝብ፣ በወለዳቸው በራሱ ልጆች ተናቀ። ኋላቀር ተብሎ ተፈረጀ። የቅኝ ገዚዎችን ቋንቋና ሃሳብ የገለበጠው “ስልጡን” ተባለ። 

አድዋ ላይ ያሸነፈ ማንነት በተሸናፊዎቹ የማንነት ሚዛን ተመዝኖ ዋጋቢስ ከተደረገ በኋላ፣ ሃገሪቱ ላይ፣ ለብዙ ሺ ዘመናት ያኖራት ሃገራዊ ማንነት እንዳልነበረ ተቆጥሮ፣ አዲስ የሃገር ግንባታ ተረት ተረት ተጫነባት። የህዝቡ ታሪክ፣ ባህሉ፣ አፈታሪኩ በአውሮፓ ኃሳብ እንዲመራና፣ ቋንቋው ከከፍተኛ ትምህርትና ከሳይንሳዊ ምርምር  እንዲገለል ተደረገ። ትምህርት ቤት ኢትዮጵያዊ እውቀትን የማጥፊያ መሳሪያ ሆነ። ልማት የገበሬ ድህነት ማስፋፊያ ሆነ። የሃገሪቱ ምሁራንና ተማሪዎች የብዙሃኑን ችግር በጥልቀት እንዳይረዱ፣ ከህዝባቸው አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ስነልቦና ተነቅለው የባእዳን ቋንቋ፣ አስተሳሰብና ስነልቦና ጥገኛ ሆኑ። መሬት ላይ የሚሰሩ እጆች ቆርሰው የሚጎርሱት እንጀራ አጡ። 

ያ አድዋ ላይ የተሸነፈው “አውሮፓን ተስፋ እንዲያደርጉ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ተስፋ መቁረጥ አለባቸው” የሚለው የቅኝ አገዛዝ መርህ በሃገሪቱ ልሂቃን መተግበር ጀመረ። በዚህ አሳዛኝ ታሪክ እንዲያልፍ እየተደረገ ያለ ህዝብ የችግሩ ምንጭና ተጠያቂው የራሱ የህዝቡ ባህል፣ ያለፈ ታሪኩ፣ ዘሩ፣ ቋንቋው እንዲሆን ተደረገ። 

በዚህ ሂደት የተሳተፍን ሁሉ የጥፋቱ ተካፋዮች ሆነናል። በጣሊያን ተጭኖ ሊወረን የመጣው አውሮፓዊ መንፈስና ስነልቦና ለጥቂት ከተሜዎች ተስፋችንና አለኝታችን ሆኗል። አድዋ ላይ የወደቁት ቅድመ አያቶቻችን የወደቁለትን ሃገርበቀል ማንነት ረግጠናል። አብዛኛው ህዝብ ዛሬም በዱሮው ቴክኖሎጂና ባህል እየኖረ፣ በእጁ  ያለውን አሻሽሎ ህይወቱን መቀየር እንዲችል ማገዝ ሲገባ፣ ድሃው ሊያገኘውና ሊጠቀምበት የማይችለውን የባእዳን እውቀት መኮረጅን የስልጣኔ ጎዳና አደረግነው።

የኮረጅነው ሁሉ ዋጋቢስ ቢሆንም ማንነትታችን ውስጥ ስለተዋሃደ ጉድለቱን መመልከት አቃተን። የእኛን አማራጭ ማጣት የህዝባችን አማራጭ ማጣት አድርገን ቆጠርነውና ገፋንበት። የአውሮፓ መንፈስ የሥልጣን ምንጭ የሆናቸው ሰዎች ቁጥር ሲበዛም በዚያው ልክ የስልጣን ፍጅቱ ተጧጧፈ። በአውሮፓ መንፈስ ስለተበረዝን አድዋን የምናከብርበት ስሜት ዝብርቅርቅ ያለ ሆነ።

በእርግጥ የአድዋን ድል እንኮራበታለን፤ ልንኮራበትም ይገባል። አድዋን ስናስብ የአድዋን ጀግኖች እናደንቃለን፣ ጽናታቸውን እንዘክራለን፤ የገበሬ ልብስ ለብሰን ፎቶ እንነሳለን። አንዳንዶች ደግሞ ያቃልሉታል ወይም የሞቱትን ይወቅሱበታል። ግን አነሰም በዛም ሁላችንም አድዋን የምናከብርበት ስሜት ኢትዮጵያዊ ሳይሆን አውሮፓዊ ሆኗል። ምክንያቱም የአድዋ ጀግኖች ይኖሩ የነበረውን አይነት ህይወት ዛሬ እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ዘለናቸዋል። በዚህ የአድዋ ድል ቀን እንኳን አናስታውሳቸውም። እነዚህ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ የሚኖሩት ህይወት ወደ አድዋ ከዘመቱት ቅድመ አያቶቻችን ጋር ተመሳሳይ ነው። 

የገጠሩ ህዝብና የከተማው ድሃ ህዝብ ህይወት የአድዋ ተጓዦች ህይወት ነው። ዛሬ ድሃው ህዝብ፣ ድሮ አድዋ እንደዘመተው ህዝብ ህይወቱን፣ ልምዱን፣ እውቀቱን፣ እርሻውን፣ ስራውን፣ ሰብአዊ ክብሩን ለማስቀጠል የህልውና ትግል ላይ ነው። ዛሬም “መሬቴን፣ ቤተሰቤን፣ ተስፋዬን፣ ክብሬን፣ ባህሌን” እያለ ይጮኻል። የሚደርስበት በደል ከመሰደብ እስከመታረድ  ደርሷል። ዛሬም የምድሪቱ ቋንቋ፣ ሃገርበቀል እውቀትና ባህል የእውቀትና የስልጣኔ ማስፋፊያ ሳይሆን የስልጣንና የጥላቻ ማስፋፊያ ሆኗል። 

ኢትዮጵያዊ መስሎ የባእዳንን መንፈስ በማንገስ ራሱን ለማተለቅ የሚሰራው ሃይል ደግሞ ድሃውን ህዝብ በኋላቀርነት ኮንኖ የምድሪቱን ሃብት ለባእዳን ቅራቅንቦ መሸመቻ ለማዋል ይሯሯጣል። የድሃውን ሃብት ወደሃብታሞች ኪስ ማስገባት ለእሱ ልማትና እድገት ነው። ህዝቡን በልዩ ልዩ የጠላትነት ጎራ ከፍሎ፣ እርስ በርስ እንዲገዳደል፣ እንዲጠላላ፣ እንዳይተዛዘን የሚያደርግ የፖለቲካ ስርአት እስረኛ እያደረገው ነው። 

ታዲያ በዚህ ሰአት አድዋን እንዴት እናስባት? አድዋ ያስከበረችው ህይወት በሚረገጥባት ሃገር ላይ እንዴት ብለን አድዋን እናክብር?

እንደሚመስለኝ፣ ለብዙዎቻችን አድዋ ጠፍታብናለች። መጀመሪያ አድዋን ከራሳችን ውስጥና ከአካባቢያችን እናግኛት። ዛሬ የአድዋ ጦርነት የሚካሄደው በእያንዳንዳችን ህይወት፣ ስነልቦና፣ ፍላጎትና ምርጫ ላይ ነው። የምናደንቀው፣ የምንመኘው፣ ጊዜአችንን የምናጠፋው ለባእዳን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ከሆነ አድዋ ጠፍታብናለች ማለት ነው። መጀመሪያ አድዋ ላይ ድል የነሱትን እሴቶች፣ አስተሳሰቦችና የህይወት መሰረቶችን እንማራቸው፣ በግል ህይወታችን ላይ እናክብራቸው። ምድሪቱ ያበቀለችውን ህይወት አንንቀል። 

አድዋ የቆመችላቸው የሃገራችን እሴቶችና ሃብቶች ከአንድ ቆዳ ላይ እንደተገኙ ቀለማት፣ ከአንድ መሬት ላይ እንደበቀሉ እጽዋት የሁላችን ናቸው እንጂ የፖለቲከኞች የስልጣን ፍጆታ አይደሉም። ቆሰሉ እንጅ አልሞቱም፤ ተዳከሙ እንጅ አልጠፉም። ተስፋ መቁረጥ ያለብን በምንከተለው የምእራባዊነት መንፈስ እንጂ አድዋን በፈጠሩት እሴቶችና ህይወቶች አይደለም። በህዝባችን ተስፋ መቁረጥ የአድዋን መንፈስ መቃወም ነው። ውስጣችንን አጽድተን ከዚያም ወደአካባቢያችን እንመልከት።   

ዛሬ የአድዋ አይነት ጦርነት ያቆሰላቸው አርበኞች ከቤታቸውና ከንብረታቸው ተባረው በሃገራቸው ስደተኛ ሆነዋል። የግፍ ግፍ እየደረሰባቸው ነው። በተለያየ የፖለቲካ ክልል ውስጥ ቢኖሩም እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ ነው። ትግራይ ውስጥ፣ አማራ ውስጥ፣ አፋር ውስጥ፣ ኦሮምያ ውስጥ፣ ደቡብ ውስጥ፣ ወዘተ ያሉት ረሃብተኞች ሁሉ የአድዋ የመንፈስ ልጆች ናቸው።

በባእዳን መንፈስ ሳይበረዝ ድሃ ድሃን አይረግጥምና በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ቢኖሩም እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ ነው። ያሉበትን ሁኔታ ባንዴ መቀየር ባንችልም በአቅማችን ከጎናቸው ለመቆም እንሞክር። ባህልና ቋንቋዎቻቸውን የስልጣን ሳይሆን የፍቅር መሳሪያ እናድርጋቸው። 

ፖለቲከኞች የቱንም አይነት ትርጉም ቢሰጡት፣ የፖለቲካ ስርአቱ ህዝብን ከህዝብ ለማራራቅ፣ መተዛዘንን ለማድረቅና ለማለያየት ቢሰራም፣ ሁሉም ህዝቦች በተገዢነታቸው፣ በመከራቸው፣ በመገፋታቸው፣ ጥረው ግረው በመስራታቸው፣ በባህላቸው ህይወታቸው ተመሳሳይ ነው። እጣ ፈንታቸው አንድ ነው። 

ስለዚህ ግፍን ለመቃወም፣ በቤታቸው መደፈርን፣ ባገራቸው መሰደድን፣ ለማስቆም ወደአድዋ አብረናቸው እንድንዘምት ጥሪ ያደርጉልናል። አብረናቸው የምንዘምተው፣ ለተረገጠው ማንነትና ህይወት መቆም ያለብን፣ እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ስለሆንን ሳይሆን ይህን ማድረግ ትክክልና በቂ ስለሆነ ነው። 

አስተያየት