በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአጽዋማት ሥርዐት መሰረት በዓመት ውስጥ ሰባት የዓዋጅ አጽዋማት ይገኛሉ። አጽዋማቱ የሚጾሙባቸዉ የተለያዩ አላማዎችና ሥርዐቶች ያሏቸዉ ሲሆን ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ስብከት (ጾመ ነብያት)፣ ጸመ ፍልሰታ፣ ጾመ ድኅነት፣ ጾም ነነዌ እና ጾመ ገሃድ በመባል ይታወቃሉ።
ከሁሉም አጽዋማት መካከልም ረዘም ላለ ጊዜ ማለትም ለ55 ቀናት የሚጾመዉ የዐቢይ ጾም የአምነቱ ተከታዮች ከወትሮዉ የተለየ የጸሎትና የንስሐ መርሃ ግብር የሚያገኙበት ወቅት ነው። ይህ ጾም ከማንኛውም ጾም በተለየ በአብዘሀኛዉ ምዕመናን ዘንድ የተለየ ቦታ ይሰጠዋል። የአንድን ሰው መንፈሳዊ ጥንካሬ እና ቁርጠኝነት የሚፈትን ነው ይላሉ የእምነቱ መምህራን።
መምህር ሰለሞን በሻውረድ የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ፓውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቅ ናቸዉ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት የስብከት አገልግሎት ይሰጣሉ “ 'ዐቢይ' የሚለው ቃል ‘አበየ’ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ‘ከፍ አለ’ ማለት ነው” ይላሉ።
ይህ ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት የሚለዩት ሶስት ምክንያቶች አሉ የሚሉት መምህሩ አንደኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጾመው ስለሆነ ሁለተኛው በሚጾምበት የቀናት ብዛት ከሌሎች አጽዋማት ስለሚበልጥና ሶስተኛው እና የመጨረሻው 'ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች' እንዲሁም ደግሞ ሶስቱ ርዕሰ ኃጢአት የሚባሉት 'ትዕቢት፣ ስስትና ፍቅረ ነዋይ' በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል የተመቱበት ስለሆነ ይህ ጾም ዐቢይ ወይንም ታላቅ ተብሏል በማለት ያስረዳሉ።
እንደ መምህሩ ገለጻ ዐቢይ ጾም ከሚለዉ ስያሜ በተጨማሪ ጾመ ሁዳዴ፣ የካሳ ጾም፣ የድል ጾም እና ጾም አስተምህሮ የሚሉ መጠሪያዎች ያሉት ይህ የጾም ወቅት ሦስት ክፍሎችና ስምንት ሳምንታት አሉት። ከሦስቱ ክፍሎች ዉሰጥ የመጀመሪያዉ ዘወረደ ( ጾመ ሕርቃል ) ይባላል ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሁድ ድረስ ያሉትን ቀናት ይይዛል፡፡ ሁለተኛዉ ክፍል ደግሞ የጌታ ጾም በመባል የሚጠራ ሲሆን ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣእና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለዉ 40 ቀን ያጠቃልላል፡፡ የመጨረሻዉ ክፍል ጾመ ሕማማት የሚባለዉ ሲሆን ይህም ጌታችን በአልአዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሣዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ሥዑር ያለዉ መከራን የተቀበለበት 8 ቀን ሕማማት ጊዜ ይይዛል፡፡ ይህም 7+40+8 = 55 ቀን ማለት ነዉ፡፡
በስምንቱ ሳምንታ ዉስጥ ደግሞ ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሁዶቸን ሲኖሩ ስምንቱ እሁዶች ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ ደብረዘይት፣ ገብረ ሔር፣ ኒቆዲሞስ፣ መጻጉዕ እና ሆሳዕና የሚል ስያሜ አላቸዉ። ይህ ስያሜ በእዉቁ የዜማው ሊቅ በቅዱስ ያሬድ የተሰጠ ስለመሆኑም ይነገራል ።
“ጾም ማለት ለዘላዓለም ሁሉንም ሕዋሳት ከኃጢአት መከልከል፤ ለተወሰነ ጊዜ እህል ከመብላት ዉሃ ከመጠጣት መታቀብ ወይም ለተወሰኑ ወራት ከጥሉላት ማለትም ከስጋ፣ ከወተት፣ ከቅቤ፣ ከእንቁላል ፣በአጠቃላይ ከእንሰሳት ዉጤት መከልከል ነው ማለት ነዉ” ይላሉ መምህር ሰለሞን አክለውም ”በሐይማኖታዊ ምክንያት ያለ ምግብና ያለ መጠጥ መዋል፣ከሥጋና ከሚያረክስ መጠጥ መታቀብን ያመለክታል ከእነዚህም ሌላ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተነሳ የግል ጾም ወይም ደግሞ የማኅበር ጾም መታወጁን በመጽሐፍ ቅዱስሳችን ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኝ ያነሳሉ እናገኛለን” በማለት ያስረዳሉ።
“ይሁን እንጂ ጾም ማለት ራስን በርሀብ መቅጣት ወይም የርሃብ አድማ መምታት ማለት ሳይሆን ራሳችንን በመግዛት፣ የእግዚኣብሔርን ፈቃድ በመፈጸም፣ እግዚኣብሔርን እና የሰዉ ልጆችን በመውደድ መንፈሳዊ ጸጋ እንድናገኝ የምንጸልይበት የንስሓ ወቅት ነዉ፡፡” በማለት ይገልጻሉ።
“ጾም ነፍስን በእግዚአብሔር ፊት ትሑት ያደርጋል የሥጋን ፈቃድ አስገዝቶ ነፍስ እንድትነፃ እንድትቀደስ አቋሟን እንድታስተካክል ይረዳታል” የሚሉት መምህሩ “ጾም ለነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋ ሕይዎትም ለሆድ ዕቃዎች በተለይ ለስርአተ ምግብ ለሰውነታችን አባለ አካላት ዕረፍት እንዲያገኙ በማድረግ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል፤ ጾም ትሑትና ቅን ያደርጋል በሥጋዊ ፍላጎቶቻችን ፈቃዶቻችን ላይ አዛዦች መሆናችንን ያረጋግጥልናል” በማለት ያስረዳሉ፡፡
መምህሩ በጾም ወቅት “ለባልንጀሮቻችን መልካምን ነገር በማድረግ በእግዚኣብሔር ፊት ሞገስ አግኝተን ለኋጢያታችን ካሳ፣ ለነብሳችን ፈውስ፣ ለስጋችን ደግሞ ጤናና በረከት የምናገኝበት ወቅት እንዲሆን መፈጸም የሚገቡን ተግባራት” በማለት የሚከተሉትን ዘርዘረዋል።
“በምንጾምበት ወቅት ማድረግ የሚገቡን መሰረታዊ ነገሮችን አሉ በመጀመሪያ ደረጃ በመጽሀፍ ቅዱስ “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ” እንደተባለዉ ጾም አድካሚ እና ለሰውነት ገንቢ የሆኑ ምግቦችን ማንመገብበት ወቅት በመሆኑ የድካም ገጽታ ልናሳይ እንደምንችል ያሳስባል ስንጾም በመታበይ ለሌሎች ለማሳየት አይሁን ማለትም ነው። በሁለተኛ ደረጃም በምንጾምበት ወቅት ፊታችንን ላይ ጹዋሚ መሆናችንን ለሰዎች ለማሳየት ብለን ፊታችን ላይ የሐዘን ምልክት ማሳየት እንደ ሌለብን ያሳስበናል። በሦስተኛ ደረጃ ሃብታችንን ሌባ በሚሰርቀ ሥፍራ ሳይሆን ማኖር ያለብን ብል በማይበላው ስፍራ በሰማይ ማኖር እንደሚገባን ያሳስበናል” በማለት ያስረዳሉ።