በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስር ከሚተዳደሩ ወረዳዎች መካከል አንዱ የሆነው የአርጎባ ወረዳ በማኅበረሰቡ ነዋሪዎች ዘንድ አለመግባባት ሲፈጠር የሚዳኝበትና የሚያስታርቅበት ስርአት አለው። የእርቅ ስርአቱ መጠሪያ “አበጋር” ይባላል።
አርጎባ ወረዳ በደቡብ ወሎ ዞን ምስራቃዊ አቅጣጫ ይገኛል። የአርጎባ ብሄረ-ሰብ ተወላጆች መኖሪያ የሆነው አርጎባ ወረዳ ከአፋርና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር ድንበርተኛ ነው። ከወረዳው ነዋሪዎች በተጨማሪ በጉርብትና የተሳሰሩት ህዝቦች በተለያዩ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ይገናኛሉ። ህዝቡ በእለት ተእለት ኑሮ በማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ግንኙነቱ አለመግባባት ወይም ግጭት ሲፈጠር “አበጋር”ን በመጠቀም የተካረረውን ያረግቡበታል። ድርጊቱ ማኅበረሰቡ በፍቅርና በመከባበር ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። አልፎ አልፎ በሚነሱ ግጭቶች ልዩነቶች ጎልተው የመከፋፈል መንስኤ እንዳይሆኑ “አበጋር” ከፍ ያለ ሚና ይጫወታል።
የ”አበጋር” የሽምግልና ስርአት በየአካባቢው ከሚፈጠረው የግለሰቦች ጸብ አንስቶ የአፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ነዋሪ ድንበርተኞች መካከል የሚፈጠርን አለመግባባት ይፈቱበታል። “ሙስባሃ” (ሙስሊሞች በሚጸልዩበት ጊዜ በእጃቸው የሚይዙት መቁጠሪያ ነው። በአርጎባ ማህበረሰብ ትልቅ ክብር ይሰጠዋል። ለሽምግልና የተፈለገ ሰው ከፊት ለፊቱ ሙስበሃ ይቀመጥና አበጋሮች ያናግሩታል። ሰውየውም ምን የከፋ በደል ቢደርስበት ከአባቶች ቃል መውጣት ስለማይችል ከበዳዩ ጋር ለመሸማገል ፈቃደኛ ይሆናል። ይህ አልሆን ብሎ አበጋሮች ያስቀመጡትን “ሙስበሃ” በማን አለብኝነት ረግጦ የቀረበውን የሽምግልና ጥያቄ እምቢ ብሎ ከሄደ የማህበረሰቡን ባህል አራክሷልና ከማህበራዊ ህይወት ይገለላል። ሀገሩን ጥሎ እስከመሄድ የሚያደርስ ቅጣት ሊተላለፍበት ይችላል) ጥለው በማስታረቅ ያጠፋ ተመክሮ፣ በደለኛ ተክሶ ማኅበራዊ ህይወት ይቀጥላል።
ከወረዳው ነዋሪ አበጋሮች አንዱ ሸህ ኑሩ ሰይድ ስለ ስነ-ስርዓቱ ሲያብራሩ “ከአርጎባ፣ ከአፋርና ከኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች መካከል የተጋጩ ሰዎች ሲኖሩ አበጋሮች ለሽምግልና ይቀመጣሉ። በሽምግልናው ወቅት ከሦስቱም ብሔሮች የተገኙ ሽማግሌዎች በታዛቢነት ይቀመጣሉ። እንዲህ የሚደረገው በውሳኔው ላይ የሁሉም ስምምነት እንዲኖርና አድልዎ እንዳይፈጸም ነው። ዳኞች ፍርድ ሲሰጡ ለራሳቸውና ለፈጣሪ ታማኝ ሆነው ነው” ብለዋል።
ስልታዊው የአበጋር ስነ-ስርዓት መጽሐፍ ተገልጦ፣ አንቀጽ ተጠቅሶ የሚከናወን አይደለም። ዳኝነቱ ህሊናዊ ነው። በዳይና ተበዳይ ፊትለፊታቸው ለቆሙት ሽማግሌዎች ጉዳያቸውን ያስረዳሉ። የየራሳቸውን እውነት ፍርዱን ለሚሰጡ አበጋሮች እና ለታዛቢ የብሔረሰብ ተወካዮች ያስረዳሉ። ምስክሮቻቸውን ጨምሮ እውነተኛነቴን ሊያስረዳልኝ ይችላል የሚሉትን ማስረጃ ያቀርባሉ።
ለእርቅ የቀረበው አለመግባባት የተፈጠረው የስጋ ዝምድና ባላቸው ሰዎች መካከል ከሆነ የጸበኞቹ ቤተሰባዊ ዝምድና ተጠንቶ የስጋ ዝምድና ያላቸውን ሁለቱንም ወገን እንደሚያሸማግሉ የታመነባቸው ሽማግሌዎች ይመረጣሉ። ጸበኞቹ በአበጋሮች እና በቤተሰብ ተወካይ ሽማግሌዎች (የቤተሰብ ጉባዔ) ፊት ቀርበው ችግራቸውን ያስረዳሉ። ከክርክሩ በኋላ በዳይ ጥፋቱን እንዲቀበል፣ ተበዳይ በይቅርታ እንዲካስ እንደ በደሉ መጠን በዳይ ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል።
ወ/ሮ መዲና ከማል የአርጎባ ብሄረሰብ ተወላጅና የአርጎባ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለሚያውቁት “አበጋር” ሲናገሩ "ጥፋቱ ምንም ዓይነት መገለጫ ይኑረው፣ ያስከተለው የጉዳት መጠን ምንም ይሁን፣ ጉዳዩን ቀድመው አስታራቂ አባቶች ዕንዲያዩት ይደረጋል” ይላሉ። ሂደቱ በእነርሱ ማለፉ ያለውን ጥቅም ሲያስረዱም ክስተቱን ተከትሎ የሚመጣውን ጥፋት ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል። “ሰዎች በተለያየ አጋጣሚ ይጋጫሉ። በተነሳው ፀብ ያጠፋው ግለሰብ በመደበኛው የሕግ ከለላ ስር ቢውልም ቅድሚያ ነገሩ አበጋሮች ጋር ይቀርባል” የሚሉት ወይዘሮዋ የድርጊቱ ዓላማ በግጭቱ ምክንያት ህይወት ካለፈ የሟች ቤተሰቦች የገዳይ ቤተሰብ ላይ የበቀል ጥቃት እንዳያደርሱ እንደሆነ ተናግረዋል።
“አበጋሮቹ የበዳይ እና የተበዳይን ቤተሰብ ፊት ለፊት በማገናኘት እንደ ባህላቸው ደም የማድረቅና የማስማማት ሥራ ይሰራሉ። ይህም ቂም እንዳይበራከት በማኅበረሰቡ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። እኔም ቤተሰብ ላይ ተመሳሳይ ችግር ገጥሞኝ በመንግስት የሕግ ስርዓት አጥፊው የሚገባውን ቅጣት ቢያገኝም በቤተሰባችን ውስጥ የነበረውን የእንበቀላለን ስሜት በአበጋሮቹ አመካኝነት እንድንተው በማድረግ ቂምና ቁርሾ ትተን አብረን በመኖር ላይ እንገኛለን" በማለት ሃሣባቸውን ገልፀዋል።
በ“አበጋር” ችግራቸውን የፈቱ ወገኖች ከእርቁ በኋላ በጸብ አይፈላለጉም። ሁለቱም ወገኖች በአበጋሮች ፊት ይቅርታውን እንደሚያጸኑ ቃለ-መሃላ ይፈጽማሉ። ችግሩ በባልና በሚስት፣ በጓደኛሞች፣ በጎረቤታሞች ወይም በሌሎች ወገኖች ቢፈጠር በተመሳሳይ መልኩ ወደ እርቅ እና ሰላም ይመጣል።
በዚህ ሁሉ ጥረት ወደ ሰላም ሊመጣ ያልቻለ የባልና ሚስት ጉዳይ ሲያጋጥም የሁለቱም ወገኖች መብት ተከብሮ፣ ሁለቱም ወገኖች ግዴታቸውን ተወጥተው ይለያያሉ። ሚስት መብቷ ተከብሮ መካፈል የሚገባትን ሐብት እና ንብረት ተካፍላ፣ የልጆች አስተዳደግን በተመለከተ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ፍቺው ይፈጸማል። ከፍቺ በኋላ ባልና ሚስቱ በክፉ ላይተሳሰቡ፣ የእርሱ የእርሷን ዘመዶች ሊያከብር እርሷም በተመሳሳይ ልታደርግ ቃል ይገባሉ።
በአጎራባች ወረዳዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት የወለደውን ጸብ በተመለከተ ሐጂ ሲያስረዱ “በቅድሚያ የችግሩ መነሻ ይለያል። የችግሩ መነሻ ከተለየ በኋላ የችግሩ ፈጣሪ ማን እንደሆነ ይጣራል። ከዚህ በኋላ ሽማግሌዎች ይወሰናሉ” ብለዋል። ችግሩ የግጦሽ መሬት፣ የከብት ዝርፊያ፣ ወይም ሌላ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሆን እንደ ጉዳዩ ክብደት ታይቶ ከነገሩ ጋር ቅርበት ያለው ሽማግሌ ከሁሉም ወገን ይመደባል። ባለጉዳዮቹም በተመሳሳይ መንገድ ጉዳያቸውን አስረድተው ችግራቸውን ይፈታሉ።
“አካባቢያችን የሚታወቀው በሰላምና በመከባበር፣ አብሮ መኖር ባህሉ ነው” የሚሉት ሸህ ኑሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስተዋለ የሚገኘው መከፋፈል በፊት ያልነበረ አዲስ ባህል እንደሆነ ያስረዳሉ።
“ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ እዚህ ስኖር ሰው በሰውነቱ እንጂ በማንነቱና በሚናገረው ቋንቋ መከፋፈል አይታወቅም። ማኅበረሰቡ አብሮ አንዱ ከሌላው ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ ነው የሚኖረው። አሁን የዘመኑ ሹመኞች አንተ ማንነትህ ይህ ነው፣ የእርሱ ደግሞ ይሄኛው እያሉ መጥፎ መጥፎ ነገሮችን እየሰበኩ አብሮ የኖረውን ማኅበረሰብ በማጋጨት ሊነጣጥሉን አስበው ነበር። እኛ ግን በባህላችን ፈታነው” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። “የቀደመ ባህላችንን ተጠቅመን በመነጋገር፣ በመደማመጥ እኩይ የሆነውን ምኞት አጨናገፍነው። ሰላማችንን በጋራ አስጠብቀን እየኖርን ነው” ብለዋል።
ሌላው አስተያየት የሰጡን ግለሰብ አቶ አህመድ ሙስጠፋ የ47 ዓመት ጎልማሳና በሙያቸው ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ ስለ አበጋር የዳኝነት ስርዓት እና ለዘመናዊው ሕግ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ሲገልጹ "ማኅበረሰቡ እንደ ወግ ባህል ልማዱ ፍትሕ የሚያገኝበት ታላቅ ስርዓት ነው። ከዚህ በፊት በአርጎባና ባቲ ወረዳዎች ላይ ለ11 ዓመት ያህል በአቃቢ ሕግና ሰብሳቢ ዳኛ ሆኘ አገልግያለሁ። የአበጋር ስርዓቱን ከስራየም ጋር ተዛመጅ በመሆኑ በቅርበት አውቀዋለሁ። ለነዋሪዎቹ ያለው ፋይዳም በጣም ከፍተኛ ነው። በአካባቢው የሚኖሩ ብሄረሰቦች ተከባብረው በአንድነት ለመኖር ያስቻላቸው የአበጋሮቹ የዳኝነት ስርዓት ለሁሉም እኩል በመሆኑና በሀይማኖት አባቶች መመራቱ ነው። ሕብረተሰቡ ከዘመናዊው የፍትሕ ስርዓት በላይ ለባህላቸው የዳኝነት ስርዓት ታመኝ በመሆናቸው አንዱ ከሌለው ጋር በፍቅር መኖርን ይመርጣል። እንደ ሕግ ባለሙያው የዚህ ዓይነት የዳኝነት ስርአት የአብሮነት ትስስርን በማጠንከር ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል የፖሊስና ለፍትህ ስርዓቱ ጫና በማቅለል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል" ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
ይህ የአበጋር ስነስረዓት ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲቆይ የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ከክልል ቢሮ ጋር በመነጋገር ወሎ ወስጥ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ማለትም ከወሎ፣ ከመቅደላ አምባ አና ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የማይዳሰሱ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል የጋራ ስምምነት በመፈራረም የተለያዩ ጥናቶችን በመድረግ ትውፊቱን የሚያስተዋውቁ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን በመስራት ባህሉ ነባር እሴቱን ጠብቆ የማቆየት ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ የቢሮው የባህል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኃይሉ ታደሰ ገልፀዋል።