መጋቢት 1 ፣ 2014

በሶማሌ ክልል የጌራሌ ብርቅዬ የዱር እንስሳት በተከሰተው ድርቅ ለከፋ አደጋ ተጋልጠዋል

City: Jigjigaዜናቱሪዝም

ፓርኩ 38ሺህ 580 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን እንደ ቀጭኔ፣ የአፍሪካ ዝሆን፣ ጥቁር አውራሪስ፣ የተለያዩ የሳቫና ዱር እንስሳት እንዲሁም አያሌ ብርቅዬ አዕዋፍ ይገኙበታል።

Avatar: Abdi Ismail
አብዲ ኢስማኤል

Abdi Ismail is Addis Zeybe's correspondent in Somali regional state

በሶማሌ ክልል የጌራሌ ብርቅዬ የዱር እንስሳት በተከሰተው ድርቅ ለከፋ አደጋ ተጋልጠዋል
Camera Icon

Credit: https://www.worqambatour.com

በሶማሌ ክልላዊ መንግስት፣ ዳዋ ዞን በሚገኘው የጌራሌ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ በአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት የተከሰተው ድርቅ ባስተከለው የውሃና ግጦሽ እጥረት ምክንያት ለከፋ አደጋ እየተጋለጡ መሆኑን የፓርኩ የቱሪዝም ፕሮሞሽን ባለሙያዎች አስታወቁ።

የፓርኩ የማህበረሰብ ግንዛቤና የቱሪዝም ፕሮሞሽን ልማት ዳይሬክተር አቶ አብዲዋሌ ሁሴን እንደተናገሩት የፓርኩ ብርቅዬ አዕዋፍና ሌሎች የዱር እንስሳት ከጌራሌ ፓርክ ወደ ኬንያ መልካ መሪ ብሔራዊ ፓርክና ወደ ሌሎች ያልታወቁ አካባቢዎች በመሰደድ ላይ ይገኛሉ።

የፓርኩ ተፈጥሮ የቱሪዝም ሀብቶችና ስነ ምህዳር አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮች ቀደም ብሎ ስላልተሟላለት እንዲሁም የአከባቢውን ህዝብ ከፓርኩ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ምንም አይነት ትኩረት አልተሰጠም ብሏል የማህበረሰብ ልማት ዳይሬክተሩ።

በጌራሌ ብሔራዊ ፓርክ በተከሰተው አስከፊ የድርቅ አደጋ እየሞቱና ለስቃይ እየተዳረጉ ላሉት የዱር እንስሳት በፓርኩ አካባቢ በሚገኙ 36 ቀበሌዎች በሚኖረው ህብረተሰብ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነና በሺዎች የሚቆጠሩ የዱር እንስሳትን ከአደጋው መታደግ እንደተቻለ ታውቋል።

በጌራሌ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳትንና ልዩ ልዩ አዕዋፍ በቆላማ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተደጋጋሚ ከሚከሰተው ድርቅ ለመታደግ እንዲሁም የፓርኩን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ለማሳደግና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እነዚህን የተፈጥሮ ፀጋዎች ለመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ለማድረስ የልማት ስትራቴጂ፣ እቅዶችና ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጁለት ፓርኩ ጥሪ አስተላልፏል። 

ጌራሌ ብሔራዊ ፓርክ እኤአ በ 2006 የተመሰረተ ሲሆን ፓርኩ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በስተደቡብ ምዕራብ በዳዋ ዞን በሁደት፣ ሙረክና በሞያሌ ወረዳዎች መካከል የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ በ900 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።

ፓርኩ 38ሺህ 580 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን እንደ ቀጭኔ፣ የአፍሪካ ዝሆን፣ ጥቁር አውራሪስ፣ የተለያዩ የሳቫና ዱር እንስሳት እንዲሁም አያሌ ብርቅዬ አዕዋፍ ይገኙበታል። 

የዳዋ ወንዝ ለዚህ በረሃማ ቦታ አይነተኛ የገፀ-ምድር ውሃ ሆኖ ያገለግላል። ጌራሌ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 13 ብሄራዊ ፓርኮች በቆዳ ስፋት አንደኛ መሆኑ ይነገርለታል።

ጌራሌ ብሔራዊ ፓርክ ሙሉ በሙሉ በጁባ/ሸበሌ የሀገር በቀል የወፍ ክልል የሚገኝ ሲሆን በሶማሌ/ማሳይ የእንሰሳት ዝርያ ስብስብ ውስጥ ከተካተቱት የወፍ ዝርያዎች 50% የሚሆኑት ዝርያዎችም መኖሪያ ነው።

አስተያየት