መጋቢት 1 ፣ 2014

አዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው ‘ከፍታ’ ሕንጻ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸነፈ

City: Addis Ababaዜና

ሕንፃው ከ1 ቢልየን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ሲሆን ጥር 2013 ዓ.ም. ግንባታው ተጀምሮ በ2015 ዓ.ም. ግንባታውን እና ሽያጩን እንደሚያጠናቅቅ ተነግሯል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

አዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው ‘ከፍታ’ ሕንጻ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸነፈ

አዲስ አበባ ውስጥ ሮክስቶን ሪልስቴት እያስገነባው የሚገኘው ‘ከፍታ’ ሕንፃ መቀመጫውን እንግሊዝ ሐገር ያደረገው ‘ኢንተርናሽናል ፕሮፐርቲ አዋርድ’ የሚያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ውድድር ማሸነፉ ተሰማ። ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ መካሄድ በጀመረው ውድድር በአፍሪካ ዘርፍ ‘የአፍሪካ ምርጥ’ የተሰኘውን ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባ ሕንጻ ሲያሸንፍ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑን ኩባንያው ለአዲስ ዘይቤ በላከው መግለጫ አሳውቋል።  

‘ከፍታ’ የኤሌክትሪክ ፍጆታን የሚቀንስ፣ የዝናብ ውሃን የሚሰበስብ እንዲሁም ቆሻሻን መቆጣጠር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም በተጨማሪ ለግንባታ ሥራው የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንደሚጠቀም የተናገሩት የሮክስቶን መስራችና ስራ አስኪያጅ ዲትሪክ ኢ. ሮጅ፤ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የአረንጓዴ ሕንፃ ማረጋገጫ ማግኘት ቀጣይ ትኩረታቸው ስለመሆኑ ተናግረዋል።

‘ምርጥ ዘላቂ የመኖሪያ ቤት’ ዘርፍ አሸናፊ የሆነው ሕንፃም የግንባታ አካባቢውን ተፈጥሮ ያገናዘበ በመሆን፣ አዳዲስ ኃይል እና ቆሻሻ ቆጣቢ ስርዓቶችን በመተግበር እና የሀገር ውስጥ ባህላዊ ቅርፆችን ለሕንጻው ማስዋቢያ በመጠቀሙ እንደሆነ ታውቋል።

በአዲስ አበባ ሲግናል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው 70 ሜትር ከፍታ ያለው ሕንፃ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት ብቻ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን 105 ነጠላ አፓርትመንቶችን፣ ከ150 በላይ ተሽከርካሪ ማቆሚያ እና የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ ስለመሆኑ ከሮክስቶን ሪልስቴት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሕንፃው ከ1 ቢልየን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ሲሆን ጥር 2013 ዓ.ም. ግንባታው ተጀምሮ በ2015 ዓ.ም. ግንባታውን እና ሽያጩን እንደሚያጠናቅቅ ተነግሯል።

ምስረታውን ጀርመን ያደረገው ሮክስቶን ሪልስቴት የኢንቨስትመንት እና የሪልስቴት ልማት ተቋም ሲሆን በአሁኑ ወቅት በጀርመን፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ቅርንጫፍ ቢሮ አለው። በአፍሪካ የመጀመሪያ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፍቶ በኬንያ አስከትሏል። ቢሮውን በኢትዮጵያ ከከፈተ በኋላ ከ650 ሚልየን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል።

አስተያየት