መጋቢት 14 ፣ 2014

ወላጆችና ት/ቤቶችን የሚያገናኝ ፈጠራ የሰራዉ የ12ኛ ክፍል ተማሪ

ቴክማህበራዊ ጉዳዮች

ከልጅነቱ አንስቶ ለኮምፒዩተር ትምህርት ልዩ ዝንባሌና ተሰጥዖ ስለነበረዉ ገና የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ኮምፒዩተሮችን ፕሮግራም ማድረግ መጀመሩን ይናገራል።

Avatar: Mahlet Yared
ማህሌት ያሬድ

Mahlet is an intern at Addis Zeybe who explore her passion for storytelling

ወላጆችና ት/ቤቶችን የሚያገናኝ ፈጠራ የሰራዉ የ12ኛ ክፍል ተማሪ

ሰለሞን ዘፍኔ በወላይታ ዞን ከተማ በሚገኝ ደቡብ የካቶሊክ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከልጅነቱ አንስቶ ለኮምፒዩተር ትምህርት ልዩ ዝንባሌና ተሰጥዖ ስለነበረዉ ገና የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ኮምፒዩተሮችን ፕሮግራም ማድረግ መጀመሩን ይናገራል። 

“ሁልጊዜ ቴክኖሎጂ ነክ ለሆኑ ነገሮች በጣም ፍላጎት ነበረኝ፤ ኮምፒዩተሮች እንዴት እንደሚሰሩ አፕልኬሽኖች እና ኘሮግራሞች እንዴት እንደሚሰሩ ለማወቅ ጥረት አደርግ ነበር" ይላል።

የሀይስኩል ተማሪ እያለ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሚገናኙበት እንደ ፌስቡክ ያለ የማህበራዊ ትሥሥር መድረክ መስራቱን የሚናገረዉ ሰለሞን ድረገጹ እንዳሰበው በርካታ ተጠቃሚዎችን ባለመሳቡ ሌላ የተለየ 'ፊቼር' መጨመር እንዳለበት በማሰብ ይበልጥ ለማሻሻል ጥረቱን እንደቀጠለ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

“ተማሪዎች በሙሉ ይጠቀሙታል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር ነገ ግን አብዛኞቹ ተማሪዎች እንደ ፌስቡክ እና ቴሌግራም ያሉት የማህበራዊ ሚድያዎች ተጠቃሚ ስለነበሩ እኔ ወደፈጠርኳት አነስተኛ የተማሪዎች መገናኛ ድረ ገጽ ዝር የሚል ጠፋ” ይላል ሰለሞን "ከዛም ምን ቢጨመር ነው ተጠቃሚ መሳብ የምችለው ብዬ ማሰብ ጀመርኩ" ይላል። ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ ሙከራ በኋላ ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ አድርጎ እና የስልክ አፕሊኬሽን ሰርቶ ድረገፁን እንዴት እንዳሳደገው ይናገራል።

“ተማሪዎች የፈተና ውጤታቸውን፣ የቤት ስራዎችን፣ አቴንዳሶችን፣ የክፍያ ዝርዝሮችን እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በኦንላይን ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ቢቻል ተማሪዎች መረጃዎችን ለማግኘት ሲሉ ወደ ድረገጹ ይመጣሉ፤ ዌብሳይቱም ተጠቃሚ ያገኛል የሚል ሀሳብ መጣልኝና ኮድ ማድረግ ጀመርኩ” ይላል ሰለሞን።

ሰለሞን  ግንቦት 2013 ዓ.ም. የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ባዘጋጀው ብሩህ ተስፋ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ላይ ሽልማት በተበረከተለት ወቅት

በዚህ ጥረቱ የቀጠለዉ ታዳጊ ድረገፁን ይበልጥ አሻሽሎና ተጨማሪ አገልግሎቶችን አካቶበት "ትምህርት ቤቴ" በሚል ስያሜ  ከዓመት በፊት ከሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ለተጠቃሚዎች አቀረበዉ። ድረገጹ ወላጆች የልጆቻቸዉን የትምህርት ሁኔታ ለመከታተለ በአካል መሄድ ሳይጠበቀባቸዉ መገልገል የሚችሉበትን አሰራርና ሌሎች ተጨማሪ የትምህርት ቤት አስተዳደር አገልግሎቶችን አካቶ ይዟል።

ድረገጹ ዌብቤዝ እና የስልክ አፕልኬሽን ያለው ሲሆን የትምህርት ቤቱን አስተዳደር እና ደንበኞችን ማለትም ተማሪ እና ወላጅን የሚያገናኙበት ነዉ።  የተማሪዎች ምዝገባ፣ የትምህርት ቤት ክፈያ፤ የተማሪ ዉጤት መግለጫ፣ ተማሪ ወይም ወላጆችን ከአስተማሪዎች እንዲሁም አስተዳደሩ ጋር በድምጽ እና በቪዲዮ በኦንላይን የሚገናኙበት፣ ለወላጆች ስለልጆቻቸዉ መረጃ ሪፖርት የሚያገኙበት፣ ከትምህርት ቤቱ የሚላኩትን ማስታዎቂያዎችና አሳይንመንቶችን ማግኘት የሚችሉበትንና መሰል አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑን የፈጠራው ባለቤት ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። 

ፈጠራው በትምህርት ቤቶች፣ በተማሪ፣ በወላጅና በአስተማሪ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል በኩል የራሱን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል የሚለው ሰለሞን ድረገፁ ወላጆች በልጆች ትምህርት ላይ በቂ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደረጉ ስለሚያስችል ተማሪዎች በዉጤታቸዉም ሆነ በስነ ምግባራቸዉ የተሻሉ እንዲሆኑ፤ የመማር ማስተማር ሂደቱንም እንዲሳለጥ ያግዛል የሚል እምነት አለዉ።

“አንዳንድ ተማሪዎች ዝቅተኛ ዉጤት ሲያመጡ ከወላጆች ይደብቃሉ ወላጆች ስለ ተማሪው የትምህርት ቤት ቆይታ መረጃ የማያገኙ ከሆነ አስፈላጊዉን ድጋፍ ማድረግ አይችሉም። ይህ ሲስተም ወላጆች ባሉበት ሆነዉ መረጃ እንዲያገኙ ሰለሚያሰችል መሰል ክፍተቶች እንዳየፈጠሩ ያደረጋል”  

ስለ አጠቃቀሙ ሲያስረዳ አጠቃቀሙ በጣም ቀላል ነው ትምህርት ቤቶቹ የራሳቸው የዌብ ሳይት ፎርም ይኖራቸዋል አስተዳደሩ፣ ወላጆቸ እና ተማሪዎች ዌብ ሳይቱ  ላይ ይመዘገባሉ። ሲለ ሰለሞን ያስረዳል በተጨማሪም የስልክ አፕሊኬሽኖች ከፕለይ ስቶር እና ከአፕስቶር ላይ አውርደው ከትምህርት ቤቱ የሚሰጣቸውን ስም እና የይለፍ ቃል አስገብተው በቀላሉ መመዝገብ ይችላሉ ብሏል።

ክፍያውን የሚከፍለው ትምህርት ቤቱ ሲሆን ከፍያዉም በተለያዩ አማራጮች በወር ከ4500 እስክ 10,000 ብር ይደርሳል። በቀጣይም “በትምህርት ቤቴ ድረገጽ” ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በአንድ አባል ውስጥ የሚያገናኝ እና በአመት በመገናኘት ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትን መድረክ ለማዘጋጀት እቅድ እንዳለዉ ሰለሞን ይናገራል።

የፈጠራ ስራዉን ለገበያ ለማቅረብና ከባድ ፈተና እንደሆነበት የሚናገረዉ ሰለሞን ምንም እንኳን ስራዉ የሚያሳምን ቢሆንም ያነጋገራቸዉ ትምህርት ቤቶች አገልግሎቱን ለመጠቀም ያመነታሉ ይላል። ይሁን እንጂ በርካቶች “ ስለአገልግሎቱ የሚሰጡን አስተያየት አበረታች ነው” ይላል።

“ወደ ገበያው ከመግባታችን በፊት ጥናት አድርገን ነበር በጥናቱ መሰረትም ያነጋገርናቸው ትምህርት ቤቶች በሃሳባችን ደስተኛ ነበሩ አፕሊኬሽኑን ለሶስት ትምህርት ቤቶችም በነጻ ሰጥተን አስተያየታቸዉን ጠይቀናቸው የሰጡን ምላሽ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነበር። ”

በአፍሪካ ህብረት በተዘጋጀዉ የኢኖቬሽን ሳምንት ላይ ቀርቦ የፈጠራ ሀሳቡን የማካፋል እድል ያገኘዉ ሰለሞን ይህም በፈጠራ ስራዉ እንዲበረታ እንዳገዘዉ ይናገራል።

አስተያየት