መጋቢት 14 ፣ 2014

በ7 ቢልዮን ብር በጀት የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ያላለሙ 12 ኢንቨስተሮች 12 ሄክታር መሬት ተነጠቁ

City: Gonderዜና

ኢንቨስተሮቹ በጎንደር ከተማ ከ9 በላይ ሪልስቴቶች፣ ከ5 በላይ ባለኮኮብ ሆቴሎች እና ማምረቻ ድርጅቶችን ለመገንባት ዝግጅት ላይ ናቸው

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በ7 ቢልዮን ብር በጀት የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ያላለሙ 12 ኢንቨስተሮች 12 ሄክታር መሬት ተነጠቁ
Camera Icon

Credit: Flickr

በጎንደር ከተማ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ 307 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በአስተዳደሩ ተቀባይነት አግኝተው መሬት ተረክበዋል። ከእነዚህም መካከል የ7 ቢልዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 12 ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ፕሮጀክቱን ማስጀመር ባለመቻላቸው የወሰዱትን 12 ሄክታር መሬት ተነጥቀዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ግርማይ ልጅዓለም እንደሚሉት 5 ቢሊዬን ብር  ካፒታል ያስመዘገቡ ወደ ግንባታ ስራ ያልገቡ 69 ኢንቨስተሮች፣ 4.5 ቢልዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ግንባታ ላይ የሚገኙ 44  ኢንቨስተሮች፣ አጥር የማጠር  እና ለግንባታ የሚሆኑ ግብአቶችን በማቅረብ (ቅድመ ግንባታ) ላይ ያሉ 23 ኢንቨስተሮች፣ ማሽን ተከላ ላይ ያሉ 7 ኢንቨስተሮች እንደሚገኙ ታውቋል። ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ አጥር አጥረው ብቻ የተቀመጡ 16 ኢንቨተሮችም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷዋል። የቀሩት 12 ኢንቨስተሮች የተሰጣቸውን ቦታ ለረዥም ጊዜ አጥረው በማስቀመጣቸው ተነጥቀዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት 6 ወራት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ነባር አምራች ኢንዱስትሪዎችን ሙሉ መረጃ በመስክ ጉብኝት በታገዘ ምዝገባ ተካሂዷል። በምዝገባውም በከተማዋ በድምሩ 159 አምራች ኢንዱሰትሪዎች መረጃ ተጠናቅሯል። ኢንዱስትሪዎቹ 77 በአነስተኛ፣ 66 በመካከለኛ፣ 16 በከፍተኛ ደረጃ ያሉ ናቸው ተብሏል።  

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለመጨመር በበጀት ዓመቱ የ111 አምራች ኢንዱሰትሪዎችን የሥራ ማስኬጃ ችግር ለመቅረፍ እቅድ ቢያዝም ምንም የተፈታ ችግር እንደሌለ በሪፖርቱ ተካቷል።

የጎንደር ከተማ ኢንቨስትመንት መምሪያ በ2014 ዓ.ም. ጥር ወር አካባቢ 2.5 ቢልዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን 28 ዲያስፖራዎች ፈቃድ መስጠታቸውን ተናግረዋል። ኢንቨስተሮቹ በጎንደር ከተማ ከ9 በላይ ሪልስቴቶች፣ ከ5 በላይ ባለኮኮብ ሆቴሎች እና ማምረቻ ድርጅቶችን ለመገንባት ዝግጅት ላይ ናቸው ብለዋል።

የተረከባችሁትን መሬት አላለማችሁም የሚል ወቀሳ የተሰነዘረባቸው ባለሐብቶች በበኩላቸው ለግንባታቸው መጓተት የመሰረተ ልማት አለመሟላትን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ። በኢንቨስትመንት ባገኙት መሬት ሆቴል በመገንባት ላይ የሚገኙት አቶ ሲሳይ አባተ የሐሳቡ ተጋሪ ናቸው። “ግንባታችንን የጀመርነው በሁለት ዓመታት ለማጠናቀቅ እቅድ ይዘን ነው” የሚሉት አቶ ሲሳይ ግንባታቸውን እንዳያጠናቅቁ የመብራት አለመኖር እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ግንባታው ቢጠናቀቅም ለሆቴሉ አገልግሎት የሚውሉ ከውጭ የመጡ ቁሳቁሶች እና ማሽኖች በመብራት እጦት ምክንያት ስራ ላይ አልዋሉም። ሁኔታው ሆቴሉ በግንባታ ሂደት ብቻ ስድስት ዓመታት እንዲያልፉ ያስገደደውም መስተዳድሩ ማሟላት የሚገባውን መሰረተ ልማት ሳይሟላ በመቅረቱ እንደሆነ ደጋግመው አንስተዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መረጃ የጥናትና የፕሮሞሽን ባለሙያው አቶ ሃብታሙ አዳነ ለግንባታዎቹ መጓተት በከተማዋ  ኢንዱስትሪ ፓርክ አለመቋቋሙ፣ የአበዳሪ ተቋማትና አጋር አካላት በቅንጅት አለመስራት፣ ከሦስተኛ ወገን የጸዳ መሬት አለመኖሩ፣ ጦርነት እና የመሳሰሉት ችግሮች ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዳይጀመሩ ያደረጉ ምክንያቶች ስለመሆናቸው ነግረውናል።

የጎንደር ከተማ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ባለሙያ አቶ ንጉሡ ክብረት በበኩላቸው “ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው እቅድና ጊዜ ያልተጠናቀቁት የካፒታላቸውን 10 በመቶ በዝግ አካውንት እንዲያስቀምጡ መታዘዙ ነው” ብለዋል። የካፒታላችንን 10 በመቶ ማስያዛችን የግንባታ አቅማችንን ዝቅ አድርጓል የሚሉ በርካታ ባለኃብቶች ቅሬታ ማሰማታቸውን አቶ ንጉሡ አስታውሰዋል።