መጋቢት 13 ፣ 2014

በምስራቅ አፍሪካ 28 ሚልየን የሚሆኑ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ ሊጋለጡ ይችላል ተባለ

ዜና

ኦክስፋም ኢንተርናሽናል ድርጅት በዛሬዉ እለት ባወጣዉ መገለጫ  በቀጠናው አሁንም የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጡ 21 ሚልየን ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

Addis Zeybe is a Digital News Media.

በምስራቅ አፍሪካ 28 ሚልየን የሚሆኑ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ ሊጋለጡ ይችላል ተባለ
Camera Icon

Credit: NBC news

በአሁኑ ሰዓት በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ ሀገራት የሚታየዉ የዝናብ መጠን አነስተኛ ሆኖ ከቀጠለ 28 ሚልየን የሚሆኑ ሰዎች ለረሃብ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገለጸ።

ኦክስፋም ኢንተርናሽናል ድርጅት በዛሬዉ እለት ባወጣዉ መገለጫ  በቀጠናው አሁንም የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጡ 21 ሚልየን ሰዎች መኖራቸውን ገልጾ በሩስያ እና ዩክሬን ግጭት ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየናረ የመጣው የምግብና ቁሳቁስ ዋጋ ስጋቱን ያባብሰዋል ብሏል።

የኦክስፋም ዋና ዳይሬክተር ጋብሬይላ በቸር እንደገልፁት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ዋነኛ ተጋላጮች ናቸው። በእዚህ ወቅት ማግኘት ያለባቸውን ዝናብ ቢያገኙ እንኳን ካሉበት የረሃብ ሁኔታ በፍጥነት ለማገገም እንደማይችሉም ተገልጿል።

የቀጠናው ሀገራት ከ90 በመቶ በላይ የስንዴ ፍላጎታቸውን ከሩስያ እና ዩክሬን እንደሚያገኙ የገለፀው የኦስፋም ሪፖርት 21 ሚልየን ሰዎች በረሃብ ውስጥ ለሚገኙበት ቀጠና ተጨማሪ ራስ ምታት ነው ብሏል።

እንደ ኦክስፋም መግለጫ ከሆነ በ2022 ሩብ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ ብቻ 13 ሚልየን ሰዎች ውሃ እና ለእንስሣቶቻቸው የግጦሽ መሬት ፍለጋ ከመኖሪያ ቀዬያቸው ለመንቀሳቀስ ተገደዋል።  

በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት የተከሰተው ዓለም አቀፍ የምግብ እና ቁሳቁስ ዋጋ መናር በእዳ ውስጥ ለተዘፈቁት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አጣብቂኝ መሆኑ ሳያንስ፤ የሩስያ እና ዩክሬን ጉዳይ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ ዋጋ ላይ እየታየ ያለው ጭማሪ ችግሩን ይበልጥ የሚያወሳስብ እና የቀጠናው ሀገራት የማይሸከሙት እዳ እየሆነ ነው ተብሏል።

የኬንያ ዓመታዊ የግብርና ምርት 70 በመቶ ቀንሶ 3.1 ሚልየን ሰዎች አስከፊ ረሃብ ውስጥ በመገኘታቸው ብሔራዊ አደጋ አውጃለች። ደቡብ ሱዳን እንደሀገር ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ገጥሟት በማያውቅ የበረሃ አንበጣ መንጋ ከመጠቃት ባለፈ በገጠሟት የጎርፍ አደጋዎች በሚልየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ውስጥ ናቸው። 

ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ አይታው የማታውቀው የምግብ ዋስትና ቀውስ የገጠማት ሲሆን በሚልየን የሚቆጠሩ እንስሳት በሶማሌ ክልል ብቻ የሞቱ ሲሆን 3.5 ሚልየን ሰዎች በክልሉ ለመጠጥ ውሃ እና ምግብ እጥረት ተዳርገዋል።  

የቀጠናው ሀገራት ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ የገጠማቸው በመሆኑ “በኋላ ከመፀፀት ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲል ኦክስፋም አሳስቧል።