ጉዛራ ቤተመንግሥት በጣና ተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኝ የመጀመሪያው ቤተመንግሥት ነው። ጉዛራ ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ትርጉሙም ምቹ ማለት ነው። በጎንደር የነገሥታት ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የጉዛራን ቤተመንግሥት የመሰረቱትም ያሳነፁትም ኢትዮጵያን ከ1556-1589 ዓ.ም. ድረስ በመሩት በአፄ ሰርፀ ድንግል መሆናቸው ይነገራል።
የጉዛራ ቤተመንግሥት ከእንፍራንዝ በስተደቡብ 5ኪሎሜትር ወጣ ብሎ የተሰራ ግምብ ነው። ይህም ማለት በጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ከጣና ሐይቅ በስተ ስሜን ምስራቅ መሆኑ ነው።
አፄ ሠርፀ ድንግል በጉዛራ ቤተመንግሥት ከ1555 እስከ 1589 ዓ.ም ለ34 ዓመታት ነግሰዋል። በዚህ ጊዜ የጎንደርም የጎርጎራም አቢያተ መንግስታት አልተመሰረቱም። ከጎንደር ነገስታት የመጀመሪያው እና የጎንደር መስራችም በመባል የሚታወቁት አፄ ሠርፀ ድንግል አባታቸው አፄ ሚናስ ሲሆኑ አፄ ልብነድንግልና አፄ ናኦድ ደግሞ አያትና ቅድመ አያታቸው ናቸው። ከአፄ ሠርፀ ድንግል በኋላ ልጃቸው አፄ ያዕቆብ ለ7 ዓመታት፣ የወንድማቸው ልጅ ዘድንግል ለአንድ ዓመት ተኩል እንዲሁም አፄ ሱሲንዮስ ለ3 ዓመት እንደነገሱበት የታሪካቸው ስንክሳር ያትታል።
በክረምቱ ዝናብና በበጋው ፀሐይ አማካኝነት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጉዛራ ቤተመንግሥት ጉዳት እየደረሰበት እንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ ከአስጎብኚዎች ሰምታለች። እንደ አስጎብኚዎቹ ገለጻ በተለይ በ2012 ዓ.ም. ክረምት የዘነበው ዝናብ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሷል።
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቅርስ ጠበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ ግርማቸው ሙሉጌታ እንደሚሉት በዝናቡ አማካኝነት ጉዳት የደረሰው ነሐሴ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ነው። ጉዳት የደረሰበት በ1980ቹ አካባቢ በኢህኣዴግ እና በደርግ ጦርነት ወቅት በከባድ መሳሪያ የተመታውን ክፍል 1997 ዓ.ም. ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥገና የተደረገለት የቤተመንግስቱ በሁሉም ክፍሎች ውሃ የሚያስገባ (የሚያሰርግ) በመሆኑ መወጣጫ ደረጃዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተጎድተዋል።
በጥገና ወቅት ደረጃው በአፈርና በኖራ ቅልቅል በመሆኑ አደጋውን አባብሶታል። ዝናቡ አፈሩን በመጥረጉ መወጣጫ ደረጃው መደርመሱን አቶ ግርማቸው ሙሉጌታ ተናግረዋል። በዘመን ርዝማኔ የደረሰበትን የተፈጥሮ ዱላ ተቋቁሞ ከ400 ዓመታት በላይ በጽናት እንደቆመ የኖረው ጉዛራ ቤተመንግሥት በ 1979 ዓ.ም. ከጎንደር ኪነሕንጻዎች ጋር የዓለም አቀፍ ቅርስነትን እውቅና ተቀዳጅቷል።
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ታሪካዊ ቅርሶች አስጎብኝና የጉዛራ ቤተመንግሥት ቅጥር ግቢ ባልደረባ የሆኑት አቶ ሳሙኤል መኮነን እንደሚሉት የጉዛራ ቤተመንግሥት ስፋቱ 12ሜትር በ18 ነው። ቁመቱ 16 ሜትር ሲሆን በአጠቃላይ 216 ሜትር ስኩዌር ስፋት አለው። ውስጡ ባለ አምስት ክፍል ነው። አቶ ሳሙኤል አክለውም “የፋሲል ቤተመንግሥት አርክቲክቼራል ንድፍ የተወሰደው ከዚህ ከጉዛራ ቤተመንግሥት ነው” ብለዋል።
ከባህር ጠለል በላይ 2001 ጫማ ከፍ ያለው ይህ ገላጣ አካባቢ ያን ጊዜ ለወታደራዊ ስልቶች ብቻም ሳይሆን ወደ ጎረቤት ሃገሮች ጎራ ለማለትም የሚያስችል ሁነኛ በር ነበር። እናም ለሰባ ዓመታት ያክል ሦስት ነገስታት ማለትም ያቆብ፣ ቆጋ እና ዘድንግል በዚሁ አካባቢ ነግሠው የጥንቱን የጎንደሮችን ኪነ-ሕንጻ ታሪክ ይህ ቤተ መንግሥት ቀድሞ ጽፏል። ቤተመንግስቱ ሲሰራ የንጉሱ ወታደሮች የንጉሱን ትዕዛዝ እናክብር ”እዝ እንፍራ” ከሚል አንጻር በዚሁ ቤተመንግሥት አጠገብ ”እንፍራንዝ” የምትባል ከተማ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ይህ ቤተመንግሥት አደጋ የደረሰበት በክረምት ወቅት ሲዘንብ በነበረው ዝናብ ሳቢያ እንደሆነና ቅርሱን የሚሸፍን ጣራ (shelter or cover) እንደሚያስፈልገው አቶ ሳሙኤል መኮነን አሳስበዋል። አክለውም በወረዳው ቅርስ አስተዳደር አማካኝነት ከ350 ኩንታል በላይ “ኖራ” የቀበርን ሲሆን ከተቀበረ ሦስት ዓመት እያለፈው ነው። መንግሥት አዳምጦ ዝም ማለት የለበትም። ለሚመለከተው አካል፣ ለክልል ባህልና ቱሪዝም፣ ለፌዴራል ቅርስ ጥበቃና ለዓለም አቀፍ ቅርስ ዩኒስኮ አዳምጠው ዝም ማለት ሳይሆን ባለን ማተሪያል ስራ እንድንጀምር በጀት መመደብ አለባቸው” የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ቡድን መሪ እና የመምሪያው ተወካይ አቶ አስናቀው አዳነ እንደሚሉት “በዚህ ቅርስ ጉዳይ ፌዴራል ድረስ ጥያቄ አቅርበናል እስካሁን ግን ምንም ምላሽ አላገኘንም። በእኛ በኩል የተወሰነ ጊዚአዊ ጥገና አድርገናል ግን ቅርሱ እንደቅርስ እንዲቆይ ከተፈለገ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በአጭር ጊዜ አስፈላጊውን በጀት መድቦ ቢያስጠግንልን መልካም ነው” ብለዋል።
አክለውም ይህ ቅርስ ከሌሎች አብያተ መንግሥታት ልዩ የሚያደርገው የመጀመሪያው ቤተመንግሥት ከመሆኑም በተጨማሪ የጣና ተፋሰስን ጨምሮ ምቹና ማራኪ ነው። አብዛኛውን የጎንደር ክፍል የሚያሳይ አቀማመጡም ተመራጭ ያደርገዋል” ብለዋል።
በቅርሶቹ ላይ የሚደረጉት ጥገናዎች ሙሉ ጥገና ሳይሆን የተናደ ወይም ያዘመመን የግንብ ክፍል የመደገፍ ዓይነት ሥራ ብቻ እንጂ ተጠቃሎ ሁሉንም የሚያጠቃልል የጥገና ስራ አልተካሄደም ብለዋል። ለዚህ መፍትሔ ያሉት ደግሞ ሙሉ ጥናት በማካሄድ የጥገና ሥራ ማከናወን ነው።