ጥር 7 ፣ 2014

የሥራ ላይ ደህንነታቸው ያልተጠበቀ የግንባታ ሰራተኞች በባህር ዳር

City: Bahir Darማህበራዊ ጉዳዮች

ባህር ዳር ከተማ የግለሰብ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ የመንግስት እና የግል ግንባታዎችን ማዘውተሯን የተመለከቱ ኗሪዎች በመገንባት ላይ ያለች ከተማ ይሏታል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የሥራ ላይ ደህንነታቸው ያልተጠበቀ የግንባታ ሰራተኞች በባህር ዳር
Camera Icon

Photo: Abinet Bihonegn

ወጣት አለሙ ታያቸው "በግንበኝነት"ስራ ይተዳደራል። ተግባሩን በየዕለቱ በሚከውንበት ጊዜ ልብሱ እንዳይበላሽ ከመቀየር በተረፈ" ምንም አይነት የደህንነት መጠበቂያ እንደማይጠቀም" አጫውቶናል። ነግር ግን ለእሱ ስራ የሚያስፈልጉትን የደህንነት መጠበቂያ ቁሶችን በተመለከተ ዕውቅናው እንዳለው ተናግሯል። 

አለሙ"የደህንነት መጠበቂያ ቁሶች በአሰሪዎች አይሟሉም" ይላል ሰራተኛው ችግሩን ሲያስረዳ። በተመሳሳይ መልኩ የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙ የሚያስተምርም ሆነ የስራ ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ አካል አጋጥሞት እንደማያውቅ አልሸሸገም።በስራ ላይ እያለ ጉዳት የደረሰብት ሰው አውቃለሁ እኔ ግን የከፋ ችግር ገጥሞኝ አያውቅም ይላል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ዘይነባ በከተማው ሴቶች በብዛት በሚመረጡበት የህንፃ "ልሰን" ስራ ትሰራለች። ሲሚንቶው በቆዳዋ ላይ ከሚያሳድረው የቆዳ ድርቀት ለመከላከል ቅባቶች ስራ ስትጨርስ ከመጠቀም ወጭ ሌላ የደህንነት መጠበቂያ እንደማትጠቀም አልሸሸገች።

የሙያ ደህንነት መጠበቂያ ቁሶች በአሰሪው ወይም ባለሙያው መሟላት እንዳለበት ዕውቅና እንደሌላት ትናግራለች።በሌላ መልኩ በከተማው በተለያዩ ቦታዎች ስትሰራ በሰራተኞች ላይ አደጋ ሲደርስ "የአደጋ ጊዜ የእርዳታ መስጫ የለም" ትላለች ዘይነባ ትዝብቷን ስታጋራ።

በቀለም ቅብ ስራ እራሱን እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ወጣት በቀለ ጌታቸው በከተማዋ በመጠናቅ ላይ በሚገኝ ህንፃ በቀለም ህንፃውን ሲያስውብ አግንተነዋል። ስራውን ሲሰራ ምንም አይነት የደህንነት(የሴፍቲ) መጠበቂያ እንደማይጠቀም አጫውቶናል።እንደ ወጣት በቀለ ገለፃ የኬሚካሉ ሽታም ሆነ ሌላ ነገር የጤና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ግንዛቤ እንደሌለው ነግሮናል። አልፎ አልፎ ከሚከሰት የአፍንጫ መታፈን ውጭ እምብዛም ችግር እንዳላጋጠመው ይናገራል።

ባህር ዳር ከተማ የግለሰብ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ የመንግስት እና የግል ግንባታዎችን ማዘውተሯን የተመለከቱ ኗሪዎች በመገንባት ላይ ያለች ከተማ ይሏታል። ግንባታዎች በከተማዋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከሚኖራቸው አስተዋጽኦ ባለፈ ዘርፉ ከሚፈጥረው ሰፊ የስራ እድል በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸው አያጠያይቅም። ይሁን እንጅ ከግንባታ ደህንነት ጥንቃቄ ጉድለቶች ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው እያሻቀቡ የመጡት የሥራ ላይ አደጋዎች በርካቶችን ለአካል ጉዳት ብሎም ለሞት እየዳረጉ አሳሳቢ የሚባል ማህበራዊ ጫና እየፈጠሩ እንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ ከከተማው ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

በስራ ቦታዎች የህንፃ ግንባታ ቦታዎችን ጨምሮ የሙያ ጤንነት ጠንቆች ሊያስከትል የሚችል ስጋት መኖሩን በተለያዩ መንገዶች መለየት እንደሚቻል የዘርፉባለሙያዎች ይመክራሉ።ከመንገዷችም መካከል በምልከታ፣በዳሰሳ ጥናት/survey study፣የቅድመ ድህረ አደጋ ትንተና በመስራት፣የነበሩ ዶክመንቶችን በመከለስ እና ተከታታይ የአደጋ መንስኤ ክትትል በማድረግ  አደጋ ሊያስከትል የሚችል ስጋት መኖሩን መለየት ይቻላል።

ከሙያ ደህንት እና ጤንነት አንፃር በግንባታ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ደህንነታቸውን (ሴፍቲያቸውን) ለመጠበቅ የሚችሉ አንፀባራቂ ልብስ፣ የደህንነት ጫማ (Safety Shoes)፣ ማስክ፣ ግላቭ፣ ሄልሜት፣ የመጀመሪያ ዕርዳታ መስጫ(First aid)፣የደህንነት ቀበቶ፣እና ሌሎች እንደ አስፈላጊነቱ የጆሮ እና የአይንን ደህንነት ለመጠበቅ የሚችሉ ቁሶች እንደሆኑ ባለሙያዎች ይዘረዝራሉ።

በስራ ቦታዎች የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች ባለሙያዎች እየተጠቀሙ መሆኑን በምልከታ ማረጋገጥ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በከተማው በግንባታው ላይ በሚገኝ ህንፃ በርካታ ሰራተኞች በተለያየ ሙያ እየተረባረቡ ቢገኙም ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ጥረት አለማድረጋቸውን መታዘብ ችለናል። 

የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ይህን ዘገባ ለማጠናከር በከተማዋ የግንባታ በተዘዋዋረበት ወቅት በከተማዋ በአንዳንድ አካባቢዮች በህንፃ ግንባታ ላይ ያሉ ሰራተኞች የደህንነት መሳሪያዎች ከአለመጠቀማቸው በተጨማሪ የህንፃዎች ለመስራት የተዘረጉ የእንጨት መወጣቻዎች (እስካፎልዲግ) ሰራተኞችን ለችግር ሊዳርጉ የሚችሉ መሆናቸውን መታዘብ ችሏል። ነገር ግን ችግሩን በተመለከተ የአሰሪዎች ምላሽ ፍቃደኛ በአለመሆናቸው ማካተት አልተቻለም።

አቶ ዘወዱ ደሳለኝ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የስራ ስምሪት ቡድን መሪ ነወ። በከተማዋ ለህንፃ ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የስራ ዘርፎች በድርጅቶች እና በግንባታ ቦታዎች የስራ ሁኔታ ቁጥጥሮች እንደሚደረጉ ይገልጻሉ ነገር ግን "ውስን የሰው ሀይል በመኖሩ ተደራሽ አደለም" ይላሉ እንደ ቡድን መሪወ ገለፃ በአሰሪው በኩል "የግንዛቤ እና የቁሶችን ለማሟላት ፍላጎት አለመኖር" ችግር እንዳለ ይናገራል። በሌላ መልኩ የደህንነት መጠበቂያ ቁሶችን ለመጠቀም "በአሰሪዎም በሰራተኛውም ዘንድ ሰፊ የግንዛቤ ችግር ይስተወላል።" ይላሉ ቡድን መሪው። የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች መቅረብ ያለባቸው በአሰሪው በኩል መሆኑን ገልፀዋል። አሰሪዎች እንዲያሟሉ ሰራተኞች እንዲጠቀሙ ለማድረግ ህጉን "በቁርጥኝነት ለመስፈፀም " ችግር እንዳለ ቡድን መሪው አልሸሸጉም።

በአማራ ክልል በስራ ላይ አደጋ የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጥቂት እንዳልሆነ ሪፖርቶች ይናገራሉ። በዚህም መሰረት በክልሉ የስራ ፈጠራና ስልጠና ቢሮ ሪፖርት በ2013 ዓ.ም በክልሉ ሰባት መቶ ሰላሳ ስድስት ሰራተኞች በሁሉም የስራ ዘርፎች የአካል ጉደት እንደደረሰባቸው ያሳያል። በተመሳሳይ መልኩ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የአስር ሰራተኞች ሞት ተመዝግቧል። ይህም በመረጃ ክፍት ምክንያት እንጅ ቁጥሩ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታለ። አሁን ያለው መረጃም ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው።

ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የተስማማባቸው ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦች መካከል ምቹ ስራ አንዱ ነው። ይህን ግብ ለማሳካት በህንፃ ግንባታ ቦታዎች ጨምሮ በድርጅቶች የስራ ሁኔታ ቁጥጥር እና ክትትል በሚፈለገው ልክ ማጠናከር ያስፈልጋል። በተጨማሪ ስለሙያ ጤንነት እና ደህንነት ዕውቅናው ለሌላቸው ሰራተኞች እና አሰሪዎች በሚጠበቀው ልክ እውቅና መፍጠር ይሻል። እንደ ባህር ዳር ያሉ  በግንቦታ ላይ ያሉ ከተሞች ለዘርፉ በቂ ትኩረት ሊሰጡ ግድ ይላል።

አስተያየት