“ብርሃን ለሁሉ” እ.ኤ.አ 2017 ዓ.ም. የተጀመረው የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን መርሃ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2025ዓ.ም. ሊደረስበት እቅድ የተያዘለትን ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ሽፋን ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ አንድ አካል ነው።
በመጀመሪያው መርሃ ግብር ማጠናቀቂያ ላይ እንደሀገር የኤሌክትሪክ ሽፋን በግሪድ 33በመቶ እና በኦፍ-ግሪድ 11በመቶ በአጠቃላይ 44በመቶ መድረሱን መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ ገልጿል።
ይህ የብርሃን ለሁሉ እቅድ ከኤሌክትሪክ ማመንጨት፣ ማከፋፋል እና ማሰራጨት በተጨማሪ የአገልግሎት ጥራትን እና ተደራሽነትንም አካቶ ይሰራል። አዳማ በብርሃን ለሁሉም ፓይለት ፕሮጀክት ውስጥ ከተካተቱ 8 ከተሞች አንዷ ናት። ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት ከዚህ ቀደም የሚወቀስበትን አገልግሎት በእጅጉ አሻሽያለሁ ይላል።
"ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡህ ገንዘብ እስክትከፍል ነው" የሚለው አንዷለም ዳምጤ አዲስ ቆጣሪ ለማስገባት የተገመተባቸውን ሙሉ ክፍያ 15 ሺህ ብር ከፍለው ካጠናቀቁ 8 ወር እንዳለፋቸው ይናገራል። "ምሰሶ የለም፣ ሌላ ጊዜ ቆጣሪ የለም፣ ሌላ ጊዜ ገመድ የለም የማይቋረጥ ምላሽ ነው።" የሚለው አንዷለም ፖል በግላችሁ ግዙና ይሰራላችኋል ይላሉ። በግል ከየት እንደሚገኝ አላቅም። በግል ሲገዛ አንድ ፖል 10ሺህ ብር ነው።
ወደ አዋሽ ተፋሰስ ሶሌ ሳይት መኖሪያ ቤት ገንብቶ ከገባ አራት ዓመት እንደሆነው የሚናገረው ደረጀ አውግቸው ለመኖሪያ ቤቱ የመብራት ቆጣሪ ለማስገባት የሚኖርበት አካባቢ የጋራ ኮሚቴ እንዳላቸው ይናገራል። ከአራት ዓመት ጥበቃ በኋላ በጋራ 7500 ብር ከፍለው ያስገቡት መስመር ሰኔ 2013 ዓ.ም. ደጃቸው ቢደርስም አስከ አሁን ግን መብራት አልሆናቸውም። "ፖሎቹ ላይ የሚሰቀል ስኒ (ሸክላዎች) እጥረት አለብን ብለው እስከአሁን አልሰሩልንም" የሚለው ደረጀ ሁለት ቦታ ወጪ ኑሯችንን ፈትኖታል ይላል።
እስከ 400 ሜትር ርቀት ላይ ካሉ የግለሰብ ቆጣሪዎች ላይ ኤሌክትሪክ ጠልፈን በወር 600 ብር ድረስ እየከፈልን ነው እየኖርን ያለነው ሲል የአካባቢውን የኤሌክትሪክ ችግር ይገልጻል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀጥለው የሚጠቀሙባቸው ገመዶች ውድ እንደሆኑና የገመድ ስርቆት እጅጉን እንዳስመረራቸውና ለተደጋጋሚ ወጪ እንደዳረጋቸውም ይናገራል።
በቦኩ ሸነን ክ/ከተማ አርሴማ 105 አካባቢ ያሉ ኗሪዎች በመብራት ችግር መጉላላት ከጀመሩ 5 ዓመት ሆነ። በአካባቢው ከሚገኙ የቤት ገንቢ ማኅበራት አንዱ ሊቀ-መንበር አቶ ታምሩ ኢፋ ናቸው። ‹‹ካሉን በርካታ የልማት ጥያቄዎች አንዱ መብራት ነው›› የሚሉት አቶ ታምሩ እያንዳንዱ ማኅበር በስሩ ከ20 ያላነሰ ከ30 ያልበለጠ ቤት ገንቢ ግለሰቦች እንዳሉት ይናገራሉ። አጠቃላይ 20 ማኅበራት እንዳሉም ይናገራሉ። "ከመስመር ያለን ርቀት 500 ሜትር ነው። የተገመተው 1 ሚሊዮን በላይ ብር ስንከፋፈለው የሚከብደን አልነበረም። ነገር ግን እስካሁን መፍትሔ አላገኘንም" ብላውናል።
ማህደር መንግስቱ ሌላኛዋ የደካ አዲ ቀበሌ ኗሪ ናት። መኖሪያ ቤቷን በ2010 ዓ.ም. እንደገዛችና እንደገባች ትናገራለች። ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በማኅበር ባደረጉት ሒደት ዘንድሮ መስከረም ላይ የመብራት ቆጣሪ እንደገባላቸው ትናገራለች። "እስከ 15 ሺህ ብር ድረስ ፈጅቷል። አንድ ጊዜ 11 ሺህ ብር ሁለት ጊዜ ደግሞ ሁለት ሁለት ሺህ ብር ከፍለናል።" የምትለው ማህደር ከብዙ ጥበቃ በኋላ የገባላቸው ቆጣሪ የድህረ ክፍያ እንደሆነ ትናገራለች። ቅድመ ክፍያ እንዲገባልን ብንጠይቅም ቆጣሪው የለም ብለው ይህንን ገጥመውልናል ትላለች። ላለፉት ሶስት ወራት ለመክፈል ወደ ክፍያ ጣቢያ ስትሔድ አልገባም ብለው እንዳስመለሷት ትናገራለች። ይህም የወጪ ጫና እንደሚጨምርባት ስጋቷን ገልጻለች።
ይህ ስጋት የማህደር መንግስቱ ብቻ አይደለም ከዚህ ቀደም የድህረ ክፍያ ቆጣሪ ያላቸው ደንበኞች ለረዥም ጊዜ ከሚከፍሉት አማካኝ ክፍያ እጥፍ የመጠየቅ ነገር ተደጋግሞ ይነሳል።
በ11 ቀበሌ ቁጠባ አካባቢ ኗሪ የሆነቸው ሀፊዛ ጀማል የመኖሪያ ቤታቸውን የመብራት ቆጣሪ ከድህረ- ክፍያ ወደ ቅድሚያ ክፍያ ለመቀየር ከዓመት በላይ እንደጠበቁ ትናገራለች። ከዓመት ጥበቃ በኋላ 1700 ብር የአገልግሎት ክፍያ ከፍለው ከወራት በፊት አገልግሎቱን እንዳገኙ ትናገራለች። ሁለት እና ሦስት መቶ ስንከፍል ቆይተን በአንድ ጊዜ ሦስት እና አራት ሺህ ብር ክፈሉ መባላችን ነው እንድንቀይር ያስገደደን።" የምትለው ሀፊዛ ጀማል ይህ ዓይነት ችግር ብዙ ሰዎች የሚማረሩበት እንደሆነ ነግራናለች። ሌላው ስለጉዳዩ ያነሳችው ቅሬታ የክፍያ መጋነኑን አንስተን ለቅሬታ ወደ ቢሮ ስንሄድ ግማሽ ክፍያ ካልተከፈላችሁ አናስተናግድም ይላሉ ስትል ያጋጠማትን ችግር ትናገራለች።
ከዚህ ቀደም በአዲስ ዘይቤ የአዳማ ነዋሪዎች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ መዘባችን ይታወሳል።
አመለወርቅ ገመቹ ለመኖሪያ ቤቷ የቅድመ-ክፍያ ቆጣሪ ትጠቀማለች። በቅድመ ክፍያ አጠቃቀም ዙሪያ ሲስተሙ በሚሰራ ሰዓት ጥሩ የምንገለገል ሲሆን አንድ ጊዜ እስከሁለት ቀን ድረስ ስለሚጠፉ ከፍተኛ መጉላላት እና ወረፉ ይፈጠራል።" ትላለች። ምክንያቱን ስንጠይቅ የሲስተም መቋረጥ ነው የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠው ትላለች።
ዋጆ አዲስ እየለማ ያለ መኖሪያ መንደር ነው የሚለው ዳግም ተስፋዬ የኃይል ማነስ የቤት ውስጥ መጠቀሚያ መሳሪያዎችን እንኳን እንዳንጠቀም ከልክሎናል ይላል። አዲስ መስመር ለማስገባት ወረፋ ይበዛል ምሶሶ የለም፣ ቆጣሪ እና ሌሎች ግብዓቶች የሉም ማለት የተለመደ ምላሽ ነው የሚለው ዳግም ተስፋዬ አንዳንዴ ምሶሶ ከአዲስ አበባ አምጡና ይሰራላችኋል እንባላለን ሲል ይናገራል።
"የድርጅቱ የጥገና ሰራተኞች ለጥገና መጥተው ከመስራት ይልቅ ሰበብ ያበዛሉ" የሚለው ዳግም ዛፍ ላይ የወደቀ መስመርን ለመጠገን የመጡ ሰራተኞች ዛፉ ይቆረጥ ብለው እንደተመለሱና ተመልሰው ሲመጡ ደግሞ ከስሩ ነው ያልነው ብለው ከኗሪዎች እሰጣ ገባ ውስጥ እንደገቡ ያስታውሳል። በመጨረሻም ያካባቢው ሰው አዋጥቶ በሰጣቸው የተወሰነ ገንዘብ ተስማምተው መስራታቸው ይቆረጥ ያሉትን ዛፍም ትተው ሰርተው መሄዳቸውን ይናገራል።
የኤሌክትሪካል መሀንዲሱ አቤል ዘርፉ ግሪን ሆፕ ድርጅት ባለቤት እና በኢነርጂ ዘርፍ ላይ የሚሰራ ባለሞያ ነው። "ከዚህ ቀደም የነበረው የአሰራር ክፍተት መንግስት አሰራሩን ለግሉ ዘርፍ ክፍት አለማድረጉ ነው።" የሚለው አቤል በኪሎዋት ሜትር ተለምዶ ቆጣሪ ማምረት ማስገባት፣ እስከ ፖሎች እና መሠል ስራዎች በመንግስት ብቻ መያዛቸው ቅልጥፍና እንደነሳው ይናገራል። ለአብነትም እንደአገልግሎት ቅድመ-ክፍያ ያሉ ክፍያዎችን ለግል ተቋማት መስጠት ቢቻል የሚነሳውን ቅሬታ መቅረፍ እንደሚቻል ይናገራል።
"በተደራሽነት ጥሩ ቢሰፋም የአገልግሎት ጥራት ላይ ግን ይቀረዋል" በሚል ብርሃን ለሁሉ ላይ ያለውን ግምገማ የሚናገረው አቤል ዘርፉ የወደፊቱን ትልቅ አቅም ለመፍጠር የግሉን ዘርፍ ከአነስተኛ ስራዎች ጀምሮ ማሳተፍ ፍቱን መፍትሔ ነው ሲል አስተያየቱን ይደመድማል።
አቶ ሰመረ አንበሴ የአዳማ ዲስትሪክት ደንበኞች አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ናቸው በ6 ወር ውስጥ ለማስገባት ካቀደው 26,684አዳዲስ ቆጣሪ ገደማ 12,713 የእቅዱን 48 በመቶ እንዳስገባ ነግረውናል።
ከ2013 ዓ.ም. አንፃር ለውጥ ቢኖረውም ብዙ ይቀረናል ሲሉ ነግረውናል። እንደ ምክንያት ሶስት ነገሮችን ገልፀዋል። የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የሠብስቴሽኖች ከአቅማቸው በላይ ጫና እንዲሁም የደንበኞች ከመስመር ወደራቁ አካባቢዎች መስፈር እንደሆኑ ገልፀዋል።የቋሚ ምሠሶ፣የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ፣በተለያየ አገልግሎት የሚውል የኤሌትሪክ ገመዶች መጥፋት ዋነኛ እንደሆኑ ይናገራሉ።
ከአገልግሎት ክፍያ አንፃር ለድህረ ክፍያ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚነሳውን ቅሬታ በተመለከተ በቀድሞ አሠራር የሚነሳው የቆጣሪ አለመነበብ፣በግምት መሞላት እየተቀረፈ እንደሆነም ነግረውናል። "ድርጀቻኝን CMRI የሚባል መሳሪያ በስራ ላይ በማዋል የቆጣሪ ንባብ ግልፅነት ለማከናወን እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ከቀድመ-ክፍያ አገልግሎት ላይ የተነሳውን ቅሬታ ያልተቀበሉት አቶ ሠመረ አንበሴ በባዕላት ወቅት ያለውን መጨናነቅ አምነው ግን የሲስተም መቆራረጡ ላይ ግን "ግፋ ቢል ከሠዓታት ያለፈ መቋረጥ ገጥሞን አያውቅም" ብለውናል።
ከቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ችግር በካርዶች ላይ ነው የሚሉት አቶ ሠመረ በዚህ ምክንያት አዳዲስ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ መስጠት ማቆማቸውን ይናገራሉ። ለማስተካከል በሂደት ላይ እንደሆነ ነግረውናል።
በመጨረሻም ሕብረተሰቡ መብቱን መጠየቅ እንዳለበት ካልተገባ ወጪ እራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።