ማስታወቂያ

የበዓላት ሰሞንና የትራፊክ አደጋ

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌጥር 6 ፣ 2014
City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች
የበዓላት ሰሞንና የትራፊክ አደጋ
Camera Icon

photo:የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ

በበዓላት ወቅት ከወትሮው የተለየ የህዝብ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መበራከት ግልጽ ነው። ግብይት በተለያዩ ዘርፎች ይጧጧፋል፤ ሰዎች ቤተዘመድ ለመጠየቅ ከቦታ ቦታ ይዟዟራሉ፤ ቤታቸውን በዓል በዓል ለማስመሰል ለሸመታ ወደ ገበያ ይወጣሉ፤ በተጨማሪም አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በስፋት ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የንግድ ስራዎችን በስፋት የሚከወኑበት ወቅት ነው፤ በእነዚህ ምክኒያቶች የተነሳ ከተማዋ ትጭናነቃለች።

በበዓላት ወቅት የህብረተሰቡ ትኩረት ወደ ገበያውና መዝናናቱ የሚያተኩር በመሆኑ የመንገድ ደህንነት ላይ መዘናጋቶች እንደሚስተዋሉ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጅንሲ ይገልጻል። 

ብርሃኑ ኩማ የኤጀንሲዉ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት እንደሚሉት “የትራፊክ አደጋዎች የመከሰት እድል በሚኖረው የትራፊክ እንቅስቃሴ ልክ የሚጨምር በመሆኑ የበዓላት ወቅት የተለየ ትኩረት ይፈልጋሉ።”“ይህ ወቅት በዓላት የሚደጋገሙበት ነው፤ ገና፣ ከተራ ጥምቀት እንዲሁም ሌሎች ሀገራዊና ሀይማኖታዊ በዓላት በመኖራቸው ህብረተሰቡ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት” ሲሉ ብርሃኑ ኩማ አሳስበዋል።

በበዓላት ወቅት የትራፊክ አደጋዎች እንዲባባሱ መንሳኤ የሚሆኑት ጉዳዮች አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ወቅቱን ያገናዘበ ትኩረትና ጥንቃቄ ማነስ ዋነኛ ነው። 

እንደ ብርሃኑ ኩማ ገለጻ “ከአልኮል መጠጦች ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎችን በተመለከተ በአሽከርካሪዎች የከፋ ቢሆንም በእግረኞች ላይም የሚስተዋል ክፍተተ ነው።” 

በእግረኞች በኩል ለጉዳዮቻቸው መቻኮል፣ ለእግረኛ ደህንነት የተዘጋጁ የመሻገሪያ ቦታዎችና የትራፊክ መብራት ህጎችን አለማክበር እንዲሁም ጠጥቶ መጓዝ ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አሽከርካሪዎች በማንኛውም ጊዜ ሊከበሩ የሚገባቸውን የትራፊክ ደንቦች መጣስ፣ ጠጥቶ ማሽከርከር እና ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት ዋነኛዎቹ ናቸው። 

የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር እንደሚገልጹት “እግረኞች ጠጥተው ሲንቀሳቀሱ በተሽከርካሪ መንገድ የመጓዝ እና የትራፊክ ህጎችን አለማክበር የሚያጋጥም ሲሆን አሽከርካሪዎች ደግሞ በመጠጥ ኃይል ሲያሽከረክሩ ራሳቸውንም እግረኞችንም አደጋ ላይ ይጥላሉ።”

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚደርሱ ሞትን ከሚያስከትሉ የትራፊክ አደጋዎች መካከል ጠጥቶ ማሽከርከር አንዱ ነው። ይህን ተከትሎም ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ከተማዋ የአሽከርካሪዎችን በሰውነት ውስጥ የሚገኝ የአልኮል መጠን በትንፋሽ አማካይነት የሚመረምር መሳሪያ መጠቀም ጀምራለች።   

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መከሰት ግን የትንፋሽ መመርመሪያ መሳሪያውን ተግባር እንዳይቀጥል ማድረጉን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገልጿል። “ከወረርሺኙ በፊት እንደነበረው የትራፊክ ፖሊሶች አሽከርካሪዎችን አስቁመው በትንፋሽ መመርመሪያው መፈተሽ ከወረርሺኙ ጋር አብሮ ስለማይሄድ ቀርቷል።” 

የኤጀንሲው የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ብርሃኑ ኩማ “ወረርሺኙ ከተከሰተ በኋላ የትንፋሽ መመርመሪያውን መጠቀም አዳጋች በመሆኑ ተቋርጧል፤ ስለዚህ ጠጥቶ በማሽከርከር የሚፈጠሩ የትራፊክ አደጋዎችን ከመጋቢት 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኗል።” ብለዋል።

አሁን የትራፊክ አደጋ ከደረሰ በኋላ የአደጋዉን መንሳኤ በማጣራት ሂደት ተፈትሾ ከማወቅ በስተቀር ጠጥቶ በማሽከርከር የተከሰቱ አደጋዎች አይለዩም።

እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ በጠጥቶ ማሽከርከር የሚደርስ የትራፊክ አደጋን በ89 በመቶ መቀነስ መቻሉን አዲስ ዘይቤ ከአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ የመተግበሪያ ዕቅድ (2013-2015) ላይ መመልከት ችላለች።

እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ ባለው መረጃ በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ አደጋ የሚደርስ የሞት ቁጥር በየዓመቱ 7 በመቶ እየጨመረ ነበር። የከተማ አስተዳደሩም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ብሎ ያዘጋጀው ስትራቴጂ ላይ በ5 ዓመታት ውስጥ የትራፊክ አደጋ ሞትን በግማሽ (50 በመቶ) ለመቀነስ ግብ ይዟል።

የ2012 እና 2013 ዓመት የትራፊክ አደጋዎች ሲንጻጸሩ “በ2013 ዓ.ም. በአደጋ የሟቾች ቁጥር በ59 ሰው ወይም በ13 በመቶ ቀንሷል። የከባድ አካል ጉዳቶችንም 1.25 በመቶ ማለትም 23 ከባድ የአካል ጉዳትን መቀነስ ተችሏል።” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በአዲስ አበባ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ በዘላቂነት ይቀርፋል ተብሎ የሚጠበቀው የመንገድ ደህንነት ግንዛቤዎችን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ማካተት ነው ሲሉ የትራፊክ ኤጀንሲው የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።  

“አንድ አሽከርካሪ ዛሬ ተቀጥቶ ከሳምንት በኋላ ድጋሜ የሚቀጣ ከሆነ ችግሩ የግንዛቤና የመረጃ ሳይሆን የአመለካከት ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ ብርሃኑ ኩማ “አመለካከት ላይ ያለውን ችግር በዋነኛነት ይፈታል ተብሎ የታቀደው እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተሰራ የሚገኘው የትራፊክ ህግና ደንቦች እንዲሁም የመንገድ ደህንነት እውቀት በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ላይ ማካተት ነው።” ብለዋል።

የአሽከርካሪ ፈቃድ አሰልጣኞች ላይም እገዛ ማድረና መቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ ነው። “ህግ አስከባሪዎች አሉ የሉም የሚል ጨዋታ በሰው ህይወት ላይ መቀለድ ነው፤ ስለዚህ ከህግ አስከባሪዎቹ ይልቅ ለህጉ ተገዢ መሆን ይገባቸዋል።” ብለዋል ብርሃኑ ኩማ።

የመንገድ ደህንነትን አስተማማኝ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት መናበብ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ያምናል። የትራፊክ ማኔጅመንት፣ የመንገዶች አስተዳደር፣ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ፣ የተሽከርካሪዎች ጥራት፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ዋነኞቹ ተዋናዮች መሆን እንደሚገባቸዉም ኤጀንሲው ያሳስባል።

Author: undefined undefined
ጦማሪኤልያስ ክፍሌ

Ilyas is a reporter at Addis Zeybe experienced in creative writing and content production.