ጥር 4 ፣ 2014

ታሪካዊው “ምሁር ኢየሱስ” ገዳም

City: Hawassaየአኗኗር ዘይቤ

ገዳሙ በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊያን አድባራትና ገዳማት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደሚሰለፍ ብዙዎች ይስማማሉ።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ታሪካዊው “ምሁር ኢየሱስ” ገዳም

“ምሁር ኢየሱስ ገዳም” ከተገደመ 250 ዓመታትን ያስቆጠረ ጥንታዊ ገዳም ነው። በጉራጌ ሐገረ ስብከት ምሁር ወረዳ ውስጥ ይገኛል። ስያሜውን ያገኘው ከሰባት ቤት ጉራጌ የአንዱ ቤት መጠሪያ በመሆነው “ምሁር” ነው። ገዳሙ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከፊደል ገበታ ትምህርት ጀምሮ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ስለማበርከቱ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። ብዕር ቀርጾ፣ ቀለም በጥብጦ፣ ብራና ፍቆ ታሪክን የመሰነድ ስልጣኔ በደቡብ ኢትዮጵያ እንዲስፋፋ የትምህርት ማዕከል ሆኖ ስለማገልገሉ በብዙዎች ተመስክሮለታል።  

ሳይንሳዊም ሆነ ባህላዊ ስያሜአቸው በአካባቢው አስጎብኚዎች ጭምር በውል ያልታወቀ እድሜ ጠገብ ዛፎች፣ ጥቅጥቅ ደኑን የተጠለሉ ብርቅዬ እንስሳትም የገዳሙ ድምቀቶች ናቸው። ነብር፣ ጦጣ፣ ድኩላ እና ሌሎችም የዱር እንስሳት እንደሚገኙ ሰምተናል።

በገዳሙ ከዘመነ ዮዲት ጉዲት በፊት በ804 ዓ.ም. እንደተተከለ ታሪክ ያስረዳል። በገዳምነት የተመሰረተው (የተገደመው) በኢትዮጵያዊው ፃዲቅ አብነ ዜና ማርቆስ በ13ኛው ክ.ዘ በ1250 ዓ.ም. መሆኑን መዛግብት ይጠቁማሉ። አካባቢዉ ከባህር ወለል በላይ 2,330 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል። የገዳሙ ስፋት ወደ 10 ሄክታር የሚጠጋ ሆኖ ከ6 በላይ  ትልልቅ ግቢዎች የተከፈሉ ናቸው። ዘመናዊ የት/ቤት ግቢ፣ የመንፈሳዊ ት/ቤት ግቢ፣ የካህናት ማሰልጠኛ ግቢ፣ የዋናው የቤተክርስቲያን ግቢ፣ የወንድ መነኮሳት ግቢ፣ የከብት ርባታ ግቢ እና ሌሎችም ይገኛሉ።

ገዳሙ በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊያን አድባራትና ገዳማት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደሚሰለፍ ብዙዎች ይስማማሉ። ክርስትና ኢትዮጵያ ውስጥ የገባው በ350 ዓ.ም. ክርስትና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሐይማኖት መሆኑን በማንሳት ለአባባላቸው ማስረጃ ያስቀምጣሉ።

በዚህ ታሪክ ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣታቸው የሚነገርላቸው ዘጠኝ መነኮሳት ናቸው። እነኝህ መነኮሳት ቋንቋን ተምረው ክርስትናን ካስፋፉ በኋላ አብያተ ክርስቲያናት ታነፁ፣ ገዳማት ተገደሙ። የምንኩስና ህይወትም በዚያን ጊዜ ተጀመረ። በ"ምሁር እየሱስ ገዳም" ዙርያ የተጻፉ የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱት ገዳሙ ከሐገር በቀል ባህላዊ ዕምነቶች ውጭ ያለ ሐይማኖት በመስበክ በአካባቢው ቀዳሚ ነው።

ከወይራ ዛፍ የተሰሩት እድሜ ጠገብ ቤቶች የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ። ቤቶቹ ከሕጻን እስከ አዋቂ እንደ ደረጃቸው መንፈሳዊ ትምህርት የሚያገኙባቸው ናቸው። የገዳሙ አስጎብኚ አባ ኤልሳ ካሱ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት በገዳሙ ግቢ ሰባት ጉባዔ ቤቶች ይገኛሉ። ከቀለም ትምህርት ውጭ ሁሉም ዓይነት የቤተ-ክህነት ትምህርቶች ይሰጡባቸዋል።

ሰባቱ የጉባዔ ቤቶች የንባብ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት፣ ዜማ ቤት፣ መጽሐፍ ትርጓሜ፣ አቋቋም ቤት፣ የቅኔ ቤት እና በገና ቤት (በገና ቤት የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን የበገና ድርደራ ትምህርት የሚሰጥበት ነው) ይባላሉ። የገዳሙ የአብነት ተማሪዎች በእነዚህ የጉባዔ ቤቶች እንደ ደረጃቸው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።

በ"ምሁር ኢየሱስ ገዳም" ውስጥ ያለፈው ትውልድ ለአሁኑ ምን እንዳወረሰ የሚያሳይ ቤተ-መዘክር ይገኛል። ቤተ-መዘክሩ በወቅቱ የገዳሙ የበላይ ጠባቂ በነበሩት አቡነ መልከ ጼዴቅ አማካኝነት በ1995 ዓ.ም. እንደሆነ ይነገራል። በቤተ መዘክሩ ውስጥ የኢትዮጵያን ታሪክ በየፈርጁ የሰነዱ መዛግብት ተሰንደው ይገኛሉ። የአፄ ምኒልክ የጦር መሳሪያ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ ለቤተክርስቲያኗ ያበረከቱት ብራና መጽሐፍ፣ በይዘት እና በክብደት የገዘፈ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፈ የብራና መጽሐፍ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ በጦርነት ወቅት እንዲጸለይላቸው ለቤተክርስቲያን የላኩት ደብዳቤ እና ሌሎች ታሪካዊ መዛግብት ይገኛሉ።

አባ ኤልሳ ካሱ የገዳሙ ጎብኚዎች ቁጥር አነስተኛ ስለመሆኑ ነግረውናል። ይህ ለመሆኑ እንደምክንያት የተቀመጠው የመንገድ መሰረተ ልማት አለመኖር መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

አስተያየት