ጥር 3 ፣ 2014

“ሴራ” የሀዲያ ህዝብ ባህላዊ መተዳደሪያ

City: Hawassaየአኗኗር ዘይቤ

"ሴራ” ለሀዲያዎች ሸንጎ ወይም ችሎት ሊባል የሚችል የሕግ ስርዓት ነው።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

“ሴራ” የሀዲያ ህዝብ ባህላዊ መተዳደሪያ

“ሴራ” (seera) የሲዳማ ሕዝብ ባህላዊ መተዳደሪያ ነው። በዘርፉ ላይ ጥናት ያካሄዱ የ“ፎክሎር” ባለሙያዎች “ሴራ” ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚዳኝ ደንብ ስለመሆኑ ይናገራሉ። በአለባቸው ኬዕሚሶ እና በሳሙኤል ሀንዳሞ ተጽፎ በ2002 ዓ.ም. ለንባብ የበቃው “የሀዲያ ህዝብ ታሪክ እና ባህል” የተሰኘ መጽሐፍም "ሴራ" የራሱ አደረጃጀትና መዋቅወር ያለው፣ ተፈጻሚነቱን የሚቆጣጠሩ ተቋማትን ያካተተ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ ጥንታዊ ማኅበራዊ ሕገ-ደንብ ስለመሆኑ አብራርቷል። በተጨማሪም “ሴራ” ሀዘንተኞችን ለማጽናናት እንዲሁም ለመረዳዳት የሚያገለግል ማኅበራዊ ተቋም ነው።

"ሴራ” ለሀዲያዎች ሸንጎ ወይም ችሎት ሊባል የሚችል የሕግ ስርዓት ነው። በሕገ-ደንቡ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአከባቢው ነዋሪዎች ፍትሕ እንደሚያገኙበት ያምናሉ። "ሴራ" በማኅበረሰቡ ውስጥ መስተጋብርን ከመፍጠሩ በተጨማሪ የመቻቻል ባህልን የሚያሰርጽ ያልተበረዘ ትውፊት ነው ማለት ይቻላል። ለሀዲያዎች የሴራ ስርዓት ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነትን እንዲሁም መዋቅርን የሚወስን ማኅበራዊ ሕግ ወይም ደንብ ተደርጎ ይወሰዳል።

ለሀዲያ ሕዝብ እንደ ፍቅርና ጋብቻ፣ ግጭትና እርቅ፣ የቤተሰብ ግንኙነት፣ የሀብት ውርስና የንብረት ክፍፍል ያሉ የሕይወት እንቅስቃሴዎች ሁሉ የ"ሴራ" አካል ናቸው።
የ"ሴራ"ን ስርአት ልዩ የሚያደርገው ማንኛውም ውሳኔ በድምጽ ብልጫ ወይም የተለያየ እርከን ባላቸው መሪዎች ፍላጎት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑ ነው፡፡ ረዥም ጊዜ ሊወስድ ቢችል እንኳን ችግሮች እልባት የሚያገኙት በመተማመን እና በስምምነት ነው፡፡

የሀዲያ ማኅበረሰብ በእለት ተእለት የሰዎች የኑሮ ዑደት የሚያጋጥምን ችግር የሚፈታበት 6 ደረጃዎች አሉት፡፡

1.ምኔ (Mine) ወይም አበሮሳ (Abaroosa)

በእድሜ በገፉ ሰዎች የሚመራ በአያትና በቅድመ አያት የሚገናኙ ሰዎች የሚሰባሰቡበት የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች የሚታዮበት መዋቅር ነው። በዚህ መዋቅር ውስጥ መሪ የሆነው ታላቅ ሰው ሚንዳና (mi'indaana) ይባላል። በጥሬ ትርጉሙ የቤተሰብ ዳኛ ማለት ነው።

በባልና በሚስት መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ በጎረቤታሞች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ይፈታበታል።

2.ነፈራ (Nafara)

በዚህ መዋቅር ውስጥ በአንድ መንደር የሚኖሩ ሰዎች የዝምድና ግንኙነት ታሳቢ ሳያደርግ ሁሉንም በአንድነት አባል አድርጎ የሚያቅፍ መዋቅር ነው። በአባላቱ መካከል የሚከሰቱ የድንበር ግጭቶች፣ በግጦሽ መሬት ሰበብ የሚከሰቱ አለመግባባቶችና በእድር እና በእቁብ ምክንያት የሚከሰቱ አለመግባባቶች መፍትሄ የሚሰጥባቸው ደረጃዎች ናቸው።

3.ሞሎ (Moolo)

ይህ ደግሞ ከአያትና ቅድመ አያት አልፎ ወደ ኋላ እስከ 5ኛና 6ኛ ትውልድ ድረስ በመቁጠር የሚገናኙ ቤተሰቦች የሚተዳደሩበት መዋቅር ነው። የተሰጡ የፍትሕ ውሳኔዎች ያልተስማማ ወይም ያልረካ ሰው ይግባኝ በማለት ወደ “ሞሎ” ዳኝነት መቅረብ ይችላል። ሞሎ ከአንድ በላይ የሆኑ ምኔዎች ጥርቅም ነው።

በዚህ መዋቅር ባህላዊ ዳኝነት የሚሰጡ ሽማግሌዎች ሞልዳና (mooldaana) ይባላሉ። በአንድ “ሞሎ” ውስጥ የሚገኙ አባላት በስራ በሀዘን እና በደስታ ይተባበራሉ።

“ሞሎ” የቤት ቃጠሎን ያስከተለ ግጭት መፍታት፣ ለእያንዳንዱ ምኔ የሞት ካሳ ቅጣትን ለመክፈል የሚደረሰቁኝ ድርሻ ማካፈል እንዲሁም ለእያንዳንዱ ምኔ የሹመት ስነስርዓትን ለማስከበር የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ሚሉት ሥልጣኖች አሉት።

4.ሱሎ (sullo)

ይህ የበርካታ “ሞሎዎች” ጥርቅም ሲሆን ብዙ ትውልዶች የሚገናኙበትን የዘር ግንድ በመቁጠር የሚፈጠር የዝምድና መዋቅር ጭምር ነው። ከ7 እስከ 10 ትውልዶች ሲያካትት የሱሎ ዳኛ ሱልዳና (suldaana) ተብሎ ይጠራል።

ይህ ሱሎ የነፍስ ማጥፋትን ያስከተለ ግጭትን የማየት የመመርመር እና ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ያለው መዋቅር ነው። በተጨማሪም ከሞሎ በላይ የሆኑ ግጭቶችን በተገቢው መንገድ የሚፈታው በዚሁ መዋቅር ነው።

5.ጊቾ (Giichcho)

“ጊቾ” የብዙ “ሱሎዎች” አንድነት ውጤት እንደሆነ ይነገራል። የጊቾ ዳኛ ጊችዳና (giichchdana) በመባል ይታወቃል፡፡ መዋቅሩ ከ10 እስከ 14 ትውልዶችን ያካትታል። የዚህ መዋቅር ዋነኛ ኃላፊነት በሁለት ሱሎዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን መመርመር እና መፍታት ነው።

6.ጊራ (Giira)

የብዙ ጊቾዎች ጥርቅምና ከፍተኛው ማኅበራዊ መዋቅር የሆነው ጊራ በዚህ ደረጃ ያሉ ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ ይታያሉ። በሌላ አባባል ጊራ ሲባል  መላውን የሀዲያ ህዝብ እንደመጥራት ይቆጠራል።

ይህ የአስተዳደርና የፍትሕ ስርዓት መዋቅር ከጊዜ ጊዜ የተወሰነ ለውጥ ዓሳይቷል። ለአብነት በምኔ እና በሞሎ መካከል የሚገኝ ናፋራ (nafara) የሚባል መዋቅር ተፈጥሯል። ይህም የተለያዩ ብሔረሰብ ተወላጆች በአንድ አካባቢ የሚኖርበትን ሁኔታ ለመግለጽ ነው።

በሌላ አባባል የሀዲያ ጎሳዎች ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በአንድ ላይ በአንድ አካባቢ ሲኖሩ ናፋራ የሚባል መዋቅር ተፈጥሯል።

አስተያየት