ጥር 1 ፣ 2014

የተዛባ የመድኃኒት አጠቃቀም የሚያስከትለው ጉዳት

City: Gonderጤናማህበራዊ ጉዳዮች

 ባለሙያዎቹ በሐኪሙ ካርድ ላይ የተጻፈውን ተመልክተው ለፋርማሲዎች የሚቀርብበት ማዘዣ ደረሰኝ ላይ ይገለብጡትና ለታካሚዎች ይሰጣሉ።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የተዛባ የመድኃኒት አጠቃቀም የሚያስከትለው ጉዳት

“መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት በሐኪም ሊታዘዙ ይገባል” የሚለው መመሪያ የመድኃኒት አጠቃቀም ሀ ሁ ነው። ተገቢውን ፈዋሽ ንጥረ-ነገር የያዘው መድኃኒትም የጥራት ፍተሻ ተደርጎለት በሕጋዊ መንገድ ወደ ሐገር ውስጥ የገባ መሆን ይኖርበታል። የመጠቀሚያ ጊዜው እንዳላለፈበት፣ በተገቢው የሙቀት ወይም የቅዝቃዜ መጠን የተቀመጠ መሆኑም ሊረጋገጥ ይገባል። ይህንን ቅደም ተከተል የማያሟላ የመድኃኒት አጠቃቀም ለአደጋ የሚያጋልጥ ስለ መሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተጨማሪም መድኃኒቶች ተጀምረው እንዳይቋረጡ፣ አንድ ጊዜ በሐኪም የታዘዘ መድኃኒት ሐኪሙ በድጋሚ ካላዘዘው በስተቀር ተደጋግሞ እንዳይወሰድ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

መመሪያው እና ምክሩ ከተጣሰ ፈዋሽ መድኃኒቶችን የተላመዱ ሕመሞች እንዲፈጠሩ (በዚህም ሳቢያ መድኃኒቶቹ ጥቅም እንዳይሰጡ)፣ ሰዎች ላይ በመድኃኒቱ ሳቢያ የጎንዮሽ ጉዳት እንዲደርስ (ከመፈወስ ይልቅ ሌላ በሽታ እንዲያስከትሉ) ምክንያት ይሆናል። ይህንን መሰሉ ተደጋጋሚ ልማድ በቀላል ዋጋ እና ድካም ሊገኙ በሚችሉ መድኃኒቶች የሚገኝን ፈውስ በውስብስብ እና በማይገኙ መድኃኒቶች እንኳን ሊቀረፍ የማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አጋጣሚ ይፈጥርለታል።  

የጎንደር ከተማ የቀበሌ 16 የ“አዳም መካከለኛ ክሊኒክ” ጤና መኮንን የሆኑት ሲሳይ መኮንን መድኃኒቶችን ከማዘዣ ወረቀቶች ውጭ መጠቀም እየተለመደ ስለመምጣቱ ይናገራሉ። “ያለ ማዘዣ ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉ መድኃኒቶች ጥቂት ናቸው። እነርሱም በተደጋጋሚ እና በቋሚነት መውሰድ አይኖርባቸውም። አብዛኛዎቹ ፋርማሲዎች ግን ከታማሚው በተነገራቸው የበሽታ ምልክት ተመስርተው ያለ ሐኪም ማዘዣ መድኃኒቶችን ይሸጣሉ” ብለዋል። የጤና መኮንኑ በተጨማሪም ከመድኃኒት መሸጫ መደብሮች ውጭ በሸቀጣሸቀጥ እና በሌሎችም ሱቆች ደህንነቱ ያልተጠበቀ መድኃኒት ሲሸጥ መታዘባቸውን ነግረውናል። 

ለተነሳው ችግር መፍትሔ ያሉትንም ሲያብራሩ “ታማሚዎች የታዘዙላቸውን መድኃኒቶች ከተቻለ ከአንድ የመድኃኒት መሸጫ ብቻ ቢገዙ መልካም ነው” ያሉ ሲሆን፤ ስለ መድኃኒቱ አጠቃቀም ከፋርማሲስቱ የሚያገኙትን መረጃ በጥንቃቄ ማድመጥና መተግበር፣ የገዙት መድኃኒት የመጠቀሚያ ጊዜ ያላለፈበት መሆኑን ማረጋገጥ፣ ከመድኃኒቱ ጋር የሚገኙትን የአጠቃቀም መመሪያዎች መከተል እንደሚገባ መክረዋል። 

የጤና ተማሪዋ ቃልኪዳን አስፋቸው ለረዥም ጊዜ መድኃኒት የሚወስዱ የልብ፣ የደም ግፊትና የስኳር እንዲሁም ተያያዥ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ህሙማን ከመድኃኒት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮች እንደሚስተዋሉባቸው ትናገራለች። “ሀኪሙ ለአንድ ወር ለሦስት ወር ወይም ለስድስት ወር ሊጠቀምበት የሚያስችለውን የመድኃኒት ማዘዣ ወረቀት ለታካሚው ይሰጠዋል። ታካሚዎቹም የጤና ክትትል ላለማድረግ አንድ ጊዜ በታዘዘላቸው ወረቀት በተደጋጋሚ መድኃኒት እየገዙ ለዓመታት ይጠቀሙበታል። ህመምተኛው ከአንድና ከሁለት ዓመት በፊት መድኃኒቱ ሲታዘዝለት የነበረው የጤንነት ሁኔታ አሁን ካለው ጋር ሲነጻጸር በፍጹም የተለየ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በየጊዜው በጤና ተቋማት በመገኘት መመርመርና ካለንበት የጤንነት ደረጃ ጋር የተመጣጠነ መድኃኒት መውሰድ ይገባዋል” ስትል ሐሳቧን ትደመድማለች።

ሌላው ከላይ ካየነው ሁኔታ ጋር ተያያዢነት ያለው ጉዳይ ደግሞ ህሙማን ለእነዚህ ህመሞች የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒቶች ያለጤና ባለሙያ ማዘዣ ወረቀት ከፋርማሲ ባለሙያ ጋር በመነጋገር ብቻ ገዝቶ የመጠቀም ሁኔታ ነው።ይህ ሁኔታ በተለይ ቋሚ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በየጊዜው ወደ ጤናተቋማት እየሄዱ ክትትል እንዳያደርጉና ያሉበትን የጤንነት ደረጃ እንዳያውቁ አሉታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ቋሚ ክትትል የማያስፈልጋቸው ህመሞች ያጋጠማቸው ታካሚዎች አንድ ጊዜ የታዘዘላቸውን መድኃኒት ተመሳሳይ ሕመም የተሰማቸው በመሰላቸው ጊዜ ሁሉ እየገዙ መጠቀማቸው ሌላው በተጠቃሚዎች የሚዘወተር ችግር ሆኖ ቀርቧል።

“በአንዳንድ ህክምና ተቋማት ህመምተኛውን የሚከታተለው የጤና ባለሙያ የሚያስፈልጉትን የመድኃኒት ዝርዝሮች በህመምተኛው ካርድ ላይ ይጽፈውና ለሌሎች ረዳት የጤና ባለሙያዎች ያስተላልፈዋል። ባለሙያዎቹ በሐኪሙ ካርድ ላይ የተጻፈውን ተመልክተው ለፋርማሲዎች የሚቀርብበት ማዘዣ ደረሰኝ ላይ ይገለብጡትና ለታካሚዎች ይሰጣሉ። በዚህ አሰራር አልፎ አልፎ ከካርድ ወደ ማዘዢያ ወረቀት ሲገለበጥ በትክክል ወይም ሙሉ ለሙሉ ያለመገልበጥና ካርዱ ላይ ስለመድኃኒቱ የተጻፉትን መረጃዎች አጉድሎ የመጻፍ ሁኔታዎች ይታያሉ” የሚሉት የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ኢንጅነር ማንደፍሮ ገብረመስቀል ናቸው።

አክለውም “ቁጥራቸው በርከት ያለመድኃኒቶችን ለህሙማኑ በሚሰጡበት ወቅት በአግባቡና በእርጋታ ያለማስረዳት ሁኔታ አለ፤ እኔም ስታከም አጋጥሞኛል” ብለውናል።

በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሐብታሙ ዘገየ እንደ ስኳር እና ደም ግፊት ያሉ ህመሞች ያሉባቸው የረዥም ጊዜ ክትትል (Chronic follow up) የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በጤና ተቋማት ውስጥ ወቅቱን የጠበቀ የጤና ክትትል አለማድረጋቸው የሚያስከትለውን ጉዳት እንደሚከተለው ዘርዝረዋል።

“የሕመማቸውን ወቅታዊ ደረጃ እንዳያውቁ ያደርጋል፤ የሚወስዱትን የመድኃኒት መጠን መቀነስ ወይም መጨመር ካልሆነም መቀየር ይገባቸው ከሆነ ያንን እድል ያሳጣቸዋል፤ ከሕመሙ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ጉዳቶችን (complications) በፍጥነት ለይቶ ለማከም እንዳይቻል ያደርጋል” ሲሉ ዋና ዋና ያሏቸውን ጉዳቶች ይናገራሉ። አንድ ጊዜ ታመው በታዘዘላቸው መድኃኒት የቀደመው የሕመም ስሜት ተሰማኝ በማለት ደጋግመው መድኃኒቱን ስለሚወስዱ ሰዎች ደግሞ ተከታዩን ብለዋል። 

“የተለያዩ በሽታዎች ተመሳሳይ የህመም ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ። ሐኪሞች ከታካሚው ያደመጡትን የህመም ምልክት ተመልክተው የላብራቶሪ ምርመራ የሚያዙት ንግግሩ በቂ ስለማይሆን እና ልዩ ልዩ ሕመሞች ምልክታቸው ስለሚመሳሰል ነው። ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ለበሽታቸው የሚያስፈልገውን ትክክለኛ መድኃኒት ያለ መውሰድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ለታካሚው ወቅታዊ የጤና ችግር ተስማሚ የሆነውን መድኃኒት የመምረጥ ዕድልን ከማሳጣቱም በላይ በሐኪሞች የሚወሰነው የመውሰጃ ጊዜ ርዝማኔ እና መጠን (ዶዝ) እንዳይወሰን እንቅፋት ይሆናል” ያሉ ሲሆን ህመሙ በሽታውን ተላምዶ የመፈወስ አቅሙ እንዲቀንስ ማድረጉም ሌላ የሚያስከትለው ችግር ስለመሆኑ ከሐኪሙ ሰምተናል። 

በመጨረሻም ሐኪሙ መድኃኒቶችን ጀምሮ ማቋረጥ ሕመሙ ተባብሶ በቀላሉ ማከም እንዳይቻል ስለማድረጉ፣ ለከፍተኛ ወጪና ለከፍተኛ የጤና ችግር ባስ ሲልም ለሞት የሚዳርግ በመሆኑ ሁሉም ሰው እንዲጠነቀቅ መክረዋል።

አስተያየት