ታህሣሥ 30 ፣ 2014

ለአማርኛ ቋንቋ እንግዳ የሆኑ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ቃላት

City: Dire Dawaየአኗኗር ዘይቤ

ድሬደዋ ከተማ ውስጥ የተለዩ የሚባሉት ቃላቶች በአብዛኛው የቁሳቁስና የነገሮች ስያሜዎች ናቸው።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ለአማርኛ ቋንቋ እንግዳ የሆኑ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ቃላት

ድሬዳዋ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አደርኛ፣ ሐረሪ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች በስፋት የሚነገሩባት ከተማ ናት። ከእነዚህ መካከል አማርኛን ወስደን ብንመከለከት በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሚነገረው የአማርኛ ቋንቋ የሚለይባቸው በርካታ ቃላት አሉት። በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ በስፋት ከሚነገሩት ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፤ እንዲሁም በከተማዋ ምስረታ ወቅት በአካባቢው ከኖሩ የፈረንሳይ፣ የግሪክ፣ የአርመን፣ የየመን፣ የአረብ እና ሌሎች የውጭ ሐገር ዜጎች ቋንቋዎች የተወሰዱ ወይም የተዳቀሉ ቃላት በድሬዳዋ አማርኛ ላይ ተቀላቅለዋል። እነኚህ በድሬዳዋ ነዋሪዎች ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ተዘውታሪ መግባቢያ ቃላት እንግዶችን ግር ሊያሰኙ ወይም “ምን ማለት ነው?” ብሎ እንዲጠይቅ የሚያስገድዱ ሊሆኑ ይችላሉ። በስፋት ከሚታወቁት እና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ከተስፋፉት “አቦ”፣ “ሀዬ”፣ “ሀይ”፣ “መርሃባ”፣ “አብሽር” ጀምሮ ሌሎችም የድሬዳዋ ብቻ የሆኑ ቋንቋዎች አሉ። የተለዩት ቋንቋዎች ድርጊትን የሚገልጹ ወይም የቁሳቁስ መጠሪያ ሊሆኑ ይችላሉ።

“ሙሉ የሚባል ቋንቋ የለም” የምትለው ኑአሚን አበበ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ የማስተርስ ደረጃ መምህርት ነች። መምህርቷ በሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች ቋንቋ ሊወራረስ እንደሚችል ታስረዳለች። “ቋንቋ በሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች ይዋዋሳል። እነርሱም መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ባህል እና በሀይማኖት ናቸው” እንደ መምህርት ኑአሚን ማብራሪያ ከአንድ ቋንቋ የተወረሰ ቃል መነሻው ከተወረሰበት ቋንቋ ውጭ የሆነ ሌላ ቋንቋ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ። መምህርት ኑአሚን አባባሏን በምሳሌ አስረድታለች።

ለምሳሌከተንበሪ’ የሚለው ቃል በድሬደዋ አማርኛ የውጪ (የግቢ) በርን ለመግለፅ የሚያገለግል ቃል ነው። የዚህ ቃል መነሻ ሶማልኛ ቢሆንም የቃሉ ዋና ምንጩ ግን ፈረንሳይኛ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ሶማሊያ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር በመቆየቷ ነው። በድሬዳዋ ሶማልኛ በስፋት ስለሚነገር ደግሞ በድሬዳዋ አማርኛ ውስጥ ሊገኝ ችሏል። ሶማልኛ ከፈረንሳይኛ የተዋሰውን ለአማርኛ አውሶታል።”

ድሬደዋ ከተማ ውስጥ የተለዩ የሚባሉት ቃላቶች በአብዛኛው የቁሳቁስና የነገሮች ስያሜዎች ናቸው። ቁሳቁሶቹ ከመጡበት አካባቢ ስያሜአቸውን እንደያዙ ቋንቋውን ይቀላቀላሉ። አጋጣሚው ለወሳጁ ቋንቋ አዳዲስ ቃላትን ይጨምርለታል። በሂደቱ ቋንቋው ራሱን ያዳብራል፤ መዝገበ ቃላቱን ያሰፋል። በሌላ በኩል ደግሞ ነባሩን ቋንቋ ሊያዳክመው ይችላል የሚሉ የስነ-ልሳን ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ የመግለጽ አቅሙን እያዳበረ ያዘምነዋል የሚሉም ጥቂት አይደሉም።

በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የአማርኛ እና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ነጋ አበራ የቃላት መወራረስን ከቋንቋ አና ከባህል ጥናት አኳያም የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ ያስቀምጣሉ።  

“ድሬደዋ ውስጥ ታጥፈህ ለማለት ‘ተኮርበህ’ ይባላል። ተኮርበህ የሚለው ቃል ኩርባ  ከሚለው የመጣ ሲሆን ቅፅል የሆነውን ወደ ግስ፣ ግሱን ደሞ ወደ ስም ወይም ቅፅል በመውሰድም አዲስ የሚመስሉ ቃላት ሊፈጠሩ ይችላል።

ሀይማኖትም ሌላው ቋንቋዎች ቃላትን እንዲዋዋሱ ያደርጋል። ለምሳሌ የእስልምና እምነት ከአረብኛ ቋንቋ ጋር ቁርኝት አለው ስለዚህ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ድሬደዋ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች በመኖራቸው አማርኛ ላይ የአረብኛ ተፅኖ እንዲያርፍበት ሆኗል” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በድሬዳዋ ነዋሪዎች አንደበት የእለት ተእለት መግባቢያ ቃለት ከሆኑት እና በሌሎች ከተሞች በሚኖሩ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ከማይታወቁት ቃላት መካከል ጥቂቶቹን በተከታዩ ሰንጠረዥ ተመልክተናል።