ጥር 13 ፣ 2014

ከጦርነቱ ጉዳት በማገገም ላይ የምትገኘው ደሴ

City: Dessieወቅታዊ ጉዳዮች

ደሴ በህወሃት ታጣቂ ቡድን አማካይነት ጉዳት ከደረሰባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል አንዷ ናት።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከጦርነቱ ጉዳት በማገገም ላይ የምትገኘው ደሴ
Camera Icon

Photo Credit: Idris Abdu

ደሴ በህወሃት ታጣቂ ቡድን አማካይነት ጉዳት ከደረሰባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል አንዷ ናት። ከተማዋ ከወረራው ነፃ ከወጣች በኋላ የአገልግሎት መስጫዎች እየተከፈቱ፣ የወደሙ ንብረቶች እየተተኩ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችም እየተጀመሩ መሆኑ ተሰምቷል።

በከተማዋ የሚገኙ ተቋማት የቴክኖሎጂ መገልገያዎች፣ የቢሮ ቁሳቁሶች ወድመው ከተለያዩ አካላት በሚመጡ ድጋፎች ለማሟላት እየተሰራ ስለመሆኑም መንግሥታዊ መግለጫዎች እና ሪፖርቶች አመላክተዋል። በርካታ የመንግስት መ/ቤቶች ተዘግተው፣ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውም ታሽገው የሚከፈቱበትን ቀን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

በከተማዋ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና ሌሎች አገልግሎቶችን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ተመልክቷል። በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት የተራዘሙ ወረፋዎች አልፎ አልፎ ቢከሰቱም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን ታዝቧል።

አቶ ወርቁ አሞኜ የደሴ ከተማ ውሃ አገልግሎት ኃላፊ ናቸው። በህወሃት የወደሙ የውሃ ተቋማትን በአጭር ጊዜ በመጠገን ወደ አገልግሎት ማስገባታቸውን ይናገራሉ። ውሃ በሙሉ አቅም ያልደረሰባቸው አካባቢዎች እንዳሉ የሚናገሩት ኃላፊው በሂደት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የሚገልፁት።

በደሴ ከተማ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያም ተገኝተን ቅኝት አድርገናል። ከመሬት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ አልተጀመሩም። ይህ ደግሞ በተዝረከረኩት ፋይሎች፣ ባልተጣራው የዝርፊያና ውድመት ምክንያት መሆኑን ሰምተናል። አገልግሎት ያልተጀመረው የሰነዶች ማጣራት ሂደት እስከሚጠናቀቅ እንደሆነ የሚናገሩት የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ እሸቱ ናቸው።

እንደ አቶ ሰኢድ ገለጻ ሕብረተሰቡን መልሶ በማረጋጋትና መልሶ በማቋቋም በኩል የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ናቸው።

የወደሙ ንብረቶችን የሚያጠናና በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ 16 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ወደስራ ገብቷል።

በሁሉም ክፍለ ከተማ የሚገኙ ሠራተኞች ስራቸውን በአግባቡ እንዲጀምሩ በተደረሰ ውሳኔም እስካሁን 97 ከመቶ የሚሆነው የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኛ ወደስራ የገባ መሆኑን ነግረውናል።

ተቋማትም እንደ ገቢዎች፣ ንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ያሉ ተቋማትን በአንድ ማእከል በማደራጀት አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የመሬት ነክ አገልግሎትም በቅርቡ እንደሚጀመር የተናገሩት ኃላፊው ከተማዋን በቁሳቁስ በማደራጀት በኩል ግን ሰላም የነበሩ ከተሞች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደቀጥሉና ከተማዋን ወደነበረችበት ገጽታ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት አጋዥ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየት