በጎንደር ከተማና በአጎራባች ዞኖችና ከተሞች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ረዣዥም ሰልፎች መመልከት የተለመደ ሆኗል። በተለይም ባለፉት ሦሰት ወራት አርሶ አደሮችም ለመስኖ እርሻቸው ማጠጫ ውኃ መሳቢያ ለሚጠቀሙባቸው ጄኔሬተሮች የነዳጅ ፍላጎት እጥረት ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ ተዘግቧል። እጥረቱን እና ችግሩን እንደ ጥሩ አጋጣሚ የቆጠሩ ደላሎችም በማደያዎች እና በተጠቃሚዎች መካከል ገብተው ‹ቢዝነስ› ለመስራት ይጥራሉ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ችግሩ የተከሰተው በወልዲያ መስመር ላይ ባጋጠመ እንከን እንደሆነ ተናግሯል። ‹‹ከተማዋ ነዳጅ የምታገኘው በወልዲያ መስመር እንደነበርና መስመሩ በህውሃት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በመዋሉ ነዳጁ መስመሩን ተጠቅሞ ከጅቡቲ ጎንደር ለመድረስ በ4 ቀናት ይፈጅበት ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ግን በአዲስ አበባ መዞር ሲጀምር 10 እና 11 ቀናትን ይፈጃል›› ብለዋል። አብዛኛዎቹ ነዳጅ ጫኝ ተሸከርካሪዎች ለደህንነታችን እንሰጋለን በሚል ለመንቀሳቀስ ፈቃደኛ አለመሆናቸው የጦርነቱ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ አሻጥር ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑንም አንስተዋል።
በጎንደር ከተማ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የቤንዚን እጥረት በመኖሩ የከተማዋ ተሽከርካሪዎች ረዥም ሠልፎችን ይዘው ነዳጅ ማደያዎች አካባቢ ይታያሉ። ሁኔታው የበርካቶችን ገቢ መቀነሱን፣ የጊዜ እና የገንዘብ ብክነት ማስከተሉን ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ ነዋሪዎች አረጋግጠዋል። ነዳጅ ለመቅዳት ሰልፍ እየጠበቀ ያገኘነው በለጠ ስመኘው እንደሚናገረው በቀን ውስጥ በነዳጅ ሰልፍ ብቻ ከሦሰት ሰዓት በላይ ያቃጥላል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር ንግድ ኢንዲስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቴውድሮስ ጸጋዬ እንደ ሰቲት ሁመራ ዞን፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና ደቡብ ጎንደር ዞን በከፊል ያሉ በአጎራባች ያሉ ዞኖች የነዳጅ ፍጆታቸውን ከጎንደር ስለሚጠቀሙ ለነዳጅ እጥረት አንዱ መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹በጎንደር ከተማ 14 ማደያዎች ያለማቋረጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው›› የሚሉት ኃላፊው ከመካከላቸው የተወሰኑት ማደያዎች በገንዘብ አቅም ደካማ በመሆናቸው አዲስ ትእዛዝ የሚያዙት አንድ ጊዜ አምጥተው አጣርተው ከሸጡ በኋላ ነው።
ያነዳጅ እስኪመጣ 10 እስከ 15 ቀን ክፍተት ይፈጠር እንደነበር ገልጸው የተፈጠረውን ችግር ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት መምሪያቸው ከነዳጅ አሠራጭ ካምፖኒዎች ጋር በመነጋገር በድምቀት ከሚከበረው የጥምቀት ባህል ጋር ተያይዞም እንግዶች እንዳይቸገሩ በቂ የነዳጅ አቅርቦት እንዳላቸው ኃላፊው ተናግረዋል።
ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ መብራት በሚጠፋበት አጋጣሚ እንዳይቸገሩ ለሆቴሎች፣ ለተሽከርካሪዎች እና ነዳጅ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በየማደያው ቤንዚን 5000 ሊትር፣ ናፍጣ 15000 ሊትር መጠባበቂያ እንደሚያስቀምጡና በቂ የነዳጅ አቅርቦት እንዳላቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም በአካባቢው ካሉ ዲፖዎች እየተፈተሸ እንዲቀርቡ ይደረጋል።
ኃላፊው የነዳጅ እጥረቱን ተክትሎ ግን በሕገ-ወጥ መንግድ ነዳጅን ዋጋ እየጨመሩ በሚሸጡ ሕገ-ወጦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሁሉ ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል። የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ባጭር ጊዜ ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖር ንግድ ኢንዲስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የነዳጅ እጥረቱ በመስኖ እርሻ ሥራቸው ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና በተመለከተ የጎንደር ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መምሪያ ቅድሚያ ለአርሶደሮች በመስኖ እርሻ ለተሰማሩት በሚል መርህ የነዳጅ አገልግሎት በመስኖ ስራ ለተሰማሩና ወፍጮ ላላቸው ከየትም ቦታ ለመጣ ሁሉ በልዩ ትኩረት ኩፖን እየሰጡ እያስተናገዱ እንደሆነ አቶ ቴድሮስ ጸጋዬ ገልጸዋል።
በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የማክሰኚት ከተማ ገጠራማው ክፍል ነዋሪ ወረፋ ሲጠባበቁ ያገኘናቸው አርሶ አደር የሆኑት አቶ ዓይቸው ውባንተ ለመስኖ እርሻ ሥራቸው ነዳጅ ከማደያ መጥፋት የጊዜ፣ የገንዘብ እና ጉልበት ኪሳራ እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ውኃው በጄኔሬተር ተስቦ አትክልት ማጠጣት እንዳለባቸውና ጀነሬተሩ ነዳጅ እንደሚያስፈልገው፣ ሁለት ቀን ውሃ ሳይጠጣ ካደረ ከጥቅም ውጪ እንደሚሆንባቸው ገልጸው የሚመለከተው አካል ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የቶታል ብልኮ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱራህማን ጡሃ እንደሚሉት በዚህ ሁለት ሦስት ቀን ውስጥ ማደያችን በቂ ነዳጅ ያለው ሲሆን ከመኪናዎች ወረፋ ሊጠብቁ ከመደርደር ውጪ እጥረት እንደሌለባቸው ገልጸዋል። ከጥምቀት ባህል ጋር ተያይዞ ለሆቴሎች፣ ለማንኛውም ተሽከርካሪዎች እና ወፍጮ ያላቸውን በመስኖ ስራ ለተሰማሩ ሁሉ የሚሆን በቂ ነዳጅ በማደያቸው እንዳለ ጠቁመዋል።
በማደያዎች አካባቢ በነዳጅ እና ቤንዚን የሚስተዋለው ጥቁር ገበያ ምንጩ ከየት ነው? ችግሩንስ ለመፍታት የጎንደር ከተማ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ቢሮ ምን እየሠራ ነው? ሲል አዲስ ዘይቤ መምሪያውን አነጋግራለች።
ኮንትሮባንድ ወይም በጥቁር ገቢያ እንዲሸጥባቸው የሚያደርገው አንደኛው ምክንያት አጎራባች ዞኖች በቂ ነዳጅ እንደማያመጡና ማዕከላዊ ጎንደር እንደምሳሌ ገልጸው ማክሰኚት፣ ጭልጋ፣ እንፍራንዝ ወገራ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ሥራ ላይ አይደሉም ብለዋል። እነዚህን ችግሮች ጥብቅ ቁጥጥር እየፈቱ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ከነዳጅ እጥረቱ በተጨማሪ የማደያ ባለሃብቶች የገባውን ነዳጅ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የማሰራጨት ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው ጠቁመው የነዳጅ ወረፋ እንይዛለን እያሉ በየማደያው የገቡ ደላሎችን በተወሰነ ደረጃ እያጸዱ እንደሆነና በምሽት የሚካሄደውን የነዳጅ እና ቤንዚን ጥቁር ገበያ ለመከላከል ከምሽቱ አንድ ስዓት እስከ ጠዋቱ አንድ ስዓት ከተፈቀደላቸው ተሸከርካሪዎች በቀር እንዳይሸጥ ክልከላ ተላልፏል ብለዋል። አምቡላንሶች እና የፀጥታ ተሸከርካሪዎች ከሥራዎቻቸው አስቸጋሪነት አንፃር በሌሊትም ቢሆን ሊቀዱ ይችላሉ ነው ያሉት።
ይሁን እንጂ በተለይም በምሽት የሚደረገው ቁጥጥር በበቂ እንዳልተሄደበት እና ችግሮች እንዳሉበት አቶ ቴውድሮስ ጸጋዬ ገልጸዋል። ነደጅ የሚገባው በጅቡቲ መስመር መሆኑ እና ከተማችን የሚገባውን ነዳጅ በጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ከነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች እንደሚረከ ተናግረዋል። ይህንን ክትትል ለማምለጥ የተሽከርካሪ ባለሃብቶች እና ሾፌሮች ወደ ጎንደርከተማ ከመግባት ይልቅ በሌሎች አካባቢዎች መውሰድን የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለ ጠቁመዋል።
በርካታ አካባቢዎች በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ሰበብ አድርገው ለጥቁር ገበያው መበራከት ምክንያት የሆኑ አካላት በመኖራቸው ቁጥጥር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንገ ልጸዋል።
አሁን የሚስተዋለውን የነዳጅ ጥቁር ገበያ ለመከላከልም በርካታ መጠን ያላቸው ማደያዎችን በየአካባቢው መክፈት እና አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን እጥረት መፍታት ተገቢ እንደሆነ ነው ኃላፊው የጠቆሙት።