ጥር 14 ፣ 2014

የመንገድ ዳር የጀበና ቡና ይታገድ ወይስ ስርአት ይበጅለት?

City: Bahir Darየአኗኗር ዘይቤ

በከተሞች አውራ ጎዳና የጀበና ቡና የሚሸጡ ነጋዴዎችን ማየት የተለመደ ነው።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የመንገድ ዳር የጀበና ቡና ይታገድ ወይስ ስርአት ይበጅለት?
Camera Icon

Photo Credit: Abinet Bihonegn

በቡና መገኛነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ቡናን የሚያዘወትሩ ዜጎች ከሚገኙባቸው ሐገራት መካከልም ትመደባለች። ቡናን በጀበና አፍልቶ በጋራ የመጠጣት ባህሏም ተዘውትሮ ይጠቀስላታል። በከተሞች አውራ ጎዳና የጀበና ቡና የሚሸጡ ነጋዴዎችን ማየት የተለመደ ነው። እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ የጀበና ቡና ንግድ በባህር ዳር ከተማ በእጅጉ እየተበራከተ ይገኛል። መንግሥት በሚደግፈው በመደበኛው የሥራ ፈጠራ ንግድ ዝርዝር ውስጥ የማይገኘው የጀበና ቡና ንግድ በርካታ ደንበኞች እና በርካታ ነጋዴዎች ያሉት የንግድ ዘርፍ ወደ መሆን እየተቃረበ ይመስላል። ከትልልቅ ሕንጻዎች እና ሞሎች እስከ አነስተኛ የመንገድ ዳር የላስቲክ ቤቶች ድረስ የቡና ንግድ ይጦፋል። በተለይ በሥራ መግቢያ እና በምሳ ሰዓት የተጠቃሚዎች ቁጥር ያሻቅባል።

ከቤት አልፎ አደባባይ የረገጠው ተወዳጁ ኢትዮጵያዊ የጀበና ቡና በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች ብቻውን አይቀርብም። በስኒ ከሚቀርበው ቡና በተጨማሪ የቡና ቁርስ (ፈንዲሻ) እና እጣን ያጅቡታል።

ትእግስት ይርጋ ላለፉት ሦስት ዓመታት በባህር ዳር ከተማ መንገድ ዳር ህዝብ በሚመላለስበት አመቺ ሥፍራ የጀበና ቡና አፍልታ የበርካቶችን የቡና አምሮት አርክታለች። እንደ ትግስት ገለፃ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጀበና  ቡና የመጠጣት ፍላጎት ያለው ሰው ቁጥር እየጨመረ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ተጠቃሚዎች የቡና አምሮታቸውን ለማርካት ከካፌ ይልቅ የጀበና ቡና እንደሚመርጡ ታዝባለች። መንግሥት የገበያውን እና የገበያተኛውን ፍላጎት ተመልክቶ ቢደግፋቸው የተሻለ መስራት እንደሚችሉ ነግራናለች።

እንደ ትግስት ገለፃ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ለጀበና ቡና ንግድ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ ሴቶች መንገድ ዳር የሚሰሩ በመሆናቸው ከቦታና ኪራይ ነፃ ናቸው ትላለች። ነገር ግን ከግለሰብ አጥር ስር እና ከድርጅት አካባቢ የሚሰሩ ግን ኪራይ እየከፈሉ እንደሚሰሩ ነግራናለች።

በሌላ በኩል በሚመለከተው አካል ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ችግር እየገጠማቸው እንደሆን የምትናገረው ደግሞ ሳምራዊት ታደሰ ትባላለች። በተለያዩ አካላት ከስራ ቦታቸው እንዲነሱ እንደሚደረጉ ትናገራለች። ለምሳሌ በቅርቡ “ዳያስፖራዎች ይመጣሉ የከተማውን ገፅታ ታበላሻላችሁ” በሚል ሰበብ ከስራ ቦታቸው ተነስተው እንደነበር አስታውሳ። ይህም በተለያየ ግዜ የሚገጥማቸው ችግር እንደሆን ነግራናለች። እንደ ሳምራዊት እምነት ይህ በግላችን የፈጠርነው የስራ እድል በመሆኑ ልንበረታታ ሲገባ ችግር ሊፈጥሩብን አይገባም ትላለች።

አቶ አትንኩት በላይ የቱሪዝም ባለሙያ ናቸው። በባህርዳር ከተማ የጀበና ቡና ለመርካቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ ያለውን ምቹ አጋጣሚ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። እንደ ባለሙያው ስራው ተመሳሳይነት ኖሮት በበለጠ ጥራት ቢሰራ የከተማዋ ብሎም የሐገራችን መለያ የመሆን ዕድል ይኖረዋል። “ይህ እንዲሆን በቡናው ንግድ ላይ የሚሰማሩት ሴቶች ተመሳሳይ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ይቻላል። ተመሳሳይ ረከቦት፣ ስኒ፣ ጀበና፣ አልባሳት፣ ተመሳሳይ የመቀመጫ ወንበሮች (ሐገር በቀል መሆን ይኖርባቸዋል) ያስፈልጋሉ። “ነገሩ የሻጮቹን ሕጋዊነት ከማረጋገጥ ባሻገር የምርቱን ጥራት ለመጨመር ያግዛል። ውበትም ነው። ልዩነትም ነው” የሚሉት ባለሙያው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ከመሆን ባለፈ የቡና አጠጣጥ ስርአቷንም ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ያምናሉ።

“ኢትዮጵያ የተለያዩ የቡና ቃናዎች ባለቤት እንደመሆኗ የሚቀርበው ቡና በዘፈቀደ ሳይሆን ዐይነቱን ያማከለ ቢሆንም የበለጠ ግዝፈት ይሰጠዋል። የጅማ፣ የዘጌ፣ የይርጋ ጨፌ፣ የወንበራ እና የመሳሰሉት እያሉ ተጠቃሚው በሚወደውና በሚፈልገው ቃና እንዲያዝና እንዲያጣጥም ቢደረግ” የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በጀበና ቡና ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች በራሳቸው ከፈጠሩት የስራ ዕድል በተጨማሪ እንደ ችግር የሚነሳባቸው ነገሮች አሉ። ከነዚህም መካከል በእያንዳንድ የከተማው አካባቢ የእግረኛ መንገዶች መዘርጋታቸው በኗሪዎች እንቅስቃሴ ዕክል እየፈጠሩ ነው የሚለው አንዱ ነው። የንፅህናቸው ሁኔታም ሌላው እንከን ነው። በየጊዜው በባለሙያዎች እንዲፈተሽ ማድረግ፣ ስርአትና መልክ ኖሯቸው የከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ስለመሆኑ ባለሙያው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በራሳቸው ተነሳሽነት የተፈጠረው የስራ ዕድል ወደ ምቹ አጋጣሚ ለመቀየር በስራው የተሰማሩ ሴቶች የራሳቸው አደረጃጀት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው። በዚህም የጀበና ቡና ንግድ በእያንዳንዱ የከተማዋ አካባቢዎች  የእግረኛ መንገዶችን ዘግተው የተቀመጡ በመሆናቸው የሚመለከተው አካል ትኩረት ይሻል።

“በባህር ዳር ከተማ የጀበና ቡና ነባራዊ ሁኔታ ለሌሎች የሀገራችን ከተሞች መገለጫ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ሀገራችን በቡና በዓለም ገበያ ያላትን ተጠቃሚነት ወደ ሀገር ውስጥ የስራ እድል ፈጠራ እና ተጠቃሚነት ሊቀየር ይገባል። አጋጣሚውን ከመጠቀም በተጨማሪ በስራው ሙሉ በመሉ በሚባል ደረጃ የሚሳተፉበት ሴቶች በመሆናቸው ሊበረታቱ ይገባል። ባህር ዳር ከተማ ሆነ ሌሎች የሀገራችን ከተሞች ያሉ የጀበና ቡና ንግድ ወደ ምቹ አጋጣሚ ለመቀየር የሚመለከተውን አካል ትኩረት አብዝቶ ይፈልጋል” የሚሉት ደግሞ የሥራ ፈጠራ ባለሙያው አቶ ሳሙኤል ናቸው።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የፅዳት እና ውበት የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ አወቀ ፈንቴ ከጀበና ቡና ንግድ ጋር ያለውን ሁኔታ በተቃራኒው ይረዱታል። እንደ አቶ አወቀ ገለፃ የጀበና ቡና በጎዳና የሚሰሩ ሴቶች  አንድም በእግረኛ መንገዱ ላይ ስለሚሰሩ እክል እየፈጠሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ የከተማውን አረንጓዴ ቦታ መርጠው ስለሚቀመጡ ችግር እየፈጠሩ ነው ይላሉ። እንደ አቶ አወቀ ገለፃ በጀበና ቡና ንግድ የተሰማሩ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሴቶች በጎዳና ላይ ሳይሆን በኮንቴነር ወስጥ እንደሚሰሩ ይናገራሉ። አቶ አወቀ ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩ የሕግ ማስከበር ጉዳይ እንጂ የከተማው ገፅታ እያበላሹ በመሆኑ ከአረንጓዴ ቦታ መነሳት አለባቸው ይላሉ።

አስተያየት