ጥር 2 ፣ 2015

በጤና እና በአካባቢ ላይ ጉዳቱ የከፋው የሊድ አሲድ ባትሪ አስተዳደር በኢትዮጵያ

City: Adamaጤናኢኮኖሚ

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባትሪዎች ከውጭ የሚመጡ ሲሆኑ በሀገር ውስጥ ጠግኖ ወደ ምርት የሚመልሰው ብቸኛው አዋሽ ባትሪ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ አይገኝም።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በጤና እና በአካባቢ ላይ ጉዳቱ የከፋው የሊድ አሲድ ባትሪ አስተዳደር በኢትዮጵያ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ድረገፅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ላለፉት 150 ዓመታት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የሊድ አሲድ ባትሪ አሁንም አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው የሚገኘው። አሁን ዓለም በደረሰበት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የእውቀት ልክ ከሆነ ከዚህ በኋላም ለብዙ ዓመታትን ጥቅም ላይ እንደሚውል ይገመታል። 

እያደገ የመጣው የፀሐይ ኃይል አማራጭ ምንጭም የሊድ አሲድ ባትሪን የሚጠቀም መሆኑ እና የሊድ አሲድን ይተካል ተብሎ የሚታሰበው የ'ሊትየም አይረን ፎስፌት' ቴክኖሎጂ ዋጋ በጣም ውድ መሆን የሊድ አሲድ ባትሪ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ ሊውል እንደሚችል ማሳያ መሆን ይችላሉ። 

'ሊድ' ከተባለ ከባድ ብረት (Heavy Metal) ንጥረ-ነገር እና ለሰዎች ጎጂ የሆነው ሰልፈሪክ አሲድን በማጣመር አገልግሎት የሚሰጠው የሊድ አሲድ ባትሪ በአካባቢ ላይ እያደረሰ የሚገኘው ጉዳት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች በተደጋጋሚ ይወተውታሉ።

ፔስቲሳይድ ኔክሰስ አሶሴሽን ወይም ፓን ኢትዮጵያ ፀረ-ተባይ እና ሌሎች አደገኛ ኬሚካሎች በሰው ጤና እና በአካባቢ ላይ የሚያርሱትን ጉዳት ለማስወገድ እና ለመቀነስ የሚሰራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜም በኢትዮጵያ ውስጥ በሊድ ውስጥ የሚገኝን የሊድ መጠን አጥንቶ በመንግስት እርምጃ እንዲወሰድ የሰራ ድርጅት ነው።

“ሊድ በሰው ልጅ ጤና ላይ በተለይም ህጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል” የሚሉት የፓን ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ታደሰ አመራ፣ ሊድ አሲድ ባትሪን በተመለከተ ቴክኖሎጂው ጥቅም እየሰጠ በመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ እና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ላይ ማተኮራቸውን ይናገራሉ።

የሊድ አሲድ ባትሪን የሚሰበስቡ፣ የሚያጓጉዙ፣ የሚያድሱ እና የሚያመርቱ ድርጅቶችን አሰራር በተመለከተ ገዢ ህግ እንዲወጣ ከመንግስት እና ከተለያዩ አካለት ጋር መስራታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ታደሰ በአሁን ወቅት የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ቁጥጥር አዋጅ 1090/2010 ዓ.ምን ተከትሎ በሊድ አሲድ ጉዳይ መመሪያ እየተረቀቀ መሆኑን ገልፀውልናል።የብክለት መጠንን በተለመከተ የተደረገ ጥናት ስለመኖሩ የጠየቅናቸው ዶ/ር ታደሰ በግልጽ  የሚታወቅ የተጠና የብክለት ደረጃ አለመኖሩን ገልፀው የአወጋገድ እና አያያዝ ችግር ስለመኖሩ ግን እንደሚታወቅ ይናገራሉ። አዲስ በሚወጣው መመሪያ አንዲካተት የምንፈልገው ህግ፣ አንድ ባትሪ ያስገባ ድርጅት ባትሪዎቹን ወደ ውጪ መላክ ካለበትም ሆነ ለድጋሜ ጥቅም (ሪሳይክል) እንዲደረግ ሁኔታዎችን ማስተካከል አለበት የሚሉት ዶ/ር ታደሰ ይህ የባትሪ አስተዳደሩን ቀልጣፋ ለማድረግ እና ብክለቱን እንደሚቀንስ ይናገራሉ።

ፅዮን ደረጀ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ (ኢንቫይሮመንታል መሃንዲስ) ናት። በቅርቡ በአንድ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ስር የሊድ አሲድን በተመለከተ የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ምርምር ለመስራት በዝግጅት ላይ ትገኛለች። የጥናት እና ምርምሯ ትኩረትም የሊድ አሲድ አጠቃቀምና በሚያስከትለው ችግር ዙሪያ በማህበረሰብ ግንዛቤ ላይ እንደሆነ ፅዮን ትናገራለች።

ሊድ አሲድ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እና ብክለትን ከአየር፣ ከውሃ እና ከአፈር ብክለት አኳያ ማየት እንደሚቻል የምትገልፀው የአካባቢ ጥበቃ መሃንዲሷ ፅዮን ደረጀ በሰው ልጅ ላይ የነርቭ ስርዓት፣ የኩላሊት እንዲሁም የደም ማነስ በሽታዎችን ያስከተላል ትላለች። በእፅዋት ላይም የምርታማነት ችግር እንደሚፈጥር ባለሙያዋ አፅንዖት ሰጥታ ተናግራለች።

እንደባለሙያዋ ገለፃ የድሮ የቤት ቀለሞች፣ የማዕድን ማውጫ ቴክኖሎጂዎች እና የተሽከርካሪ ጥገና (ጋራጅ) አካበቢዎች በስፋት ለሊድ አሲድ ብክለት የተጋለጡ ናቸው። ይህ ነው የሚባል የጠራ የሊድ አሲድ ባትሪ ብክለት መጠንን የሚያስረዳ የኢትዮጵያ ጥናት እስካሁን እንዳልገጠማት የምትገልፀው ባለሙያዋ ይልቁንም የባትሪዎቹ አያያዝ ላይ ያተኮረ ጥናት እንደሚበዛ ትናገራለች።

በሌላ በኩል የመኪና ቁጥር መጨመር እንዲሁም ጀነሬተሮች እና የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት መጨመር የሊድ አሲድ ባትሪ ተፈላጊነትን እየጨመረ እንደሚገኝ የሚናገረው ደግሞ አቶ አቤል ዘርፉ በታዳሽ ኃይል ላይ የሚሰራው የግሪን ሆፕ ታዳሽ ኃይል ስራዎች ባለቤት ነው። 

እንደ አቶ አቤል ዘርፉ ገለፃ ሊድ አሲድ ባትሪን የሚተካ የሊትየም አይረን ፎስፌት ቴክኖሎጂ ቢኖርም የዋጋ ውድነቱ አሁንም የሊድ አሲድ ባትሪ ተፈላጊነት እንዳይቀንስ አድርጓል። ሊድ አሲድ ባትሪ ተሽከርካሪዎች እና የተለያዩ ማሽኖችን ለማስነሳት (ክራንኪንግ) ስለሚጠቅሙ ተፈላጊነተታቸው ከፍተኛ ነው የሚለው አቤል በተቃራኒው እነኚህ ባትሪዎች ከቅርብ ጊዜ ቴክኖሎጂው ሊትየም አይረን ፎስፌት ጋር ሲነፃፀር የሊድ አሲድ ባትሪዎች ያላቸው ብቃት አነስተኛ እንዲሁም በአካበቢ ላይ የሚያስከትሉት ብክለት ከፍተኛ ቢሆንም በዋጋ ርካሽ መሆናቸው አሁንም በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጓል ብሏል።

ዋነኛ መፍትሄው የሊድ ባትሪዎችን በሊትየም አይረን ፎስፌት መተካት ነው የሚለው አቤል ዘርፉ “ይህ ዘላቂ መፍትሄ እስኪበጅ ድረስ ግን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እና በአግባቡ ማስወገድ ብክለትን ለመከላከል አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው” ሲል በአፅንዖት ይናገራል። 

ከአጠቃቀም፣ አወጋገድ እና አያያዝ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ የሆነ የእውቀት ክፍተት አለ ሲልም በዘርፉ ያለውን ችግር ባለሙያው ይገልጻል።

በጉዳዩ ላይ ጥናት እየሰራች የምትገኘው ፅዮን ደረጀም የሊድ አሲድ ባትሪ ብክለትን ስለመቆጣጠር የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ጠቅሳ እስከ 95 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆን የሊድ አሲድ ልቀትን መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉ ሀገራት አሉ ብላ “በተቃራኒው በእኛ ሀገር ይህን መሳይ ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች ባለመኖራቸው ዘርፉ ለአነስተኛ መጠን ስራዎች ተጋላጭ እንዲሆን በር ከፍቷል” ትላለች።

በኢትዮጵያ  ውስጥ የሚገኙ ባትሪዎች ከውጭ የሚመጡ ሲሆኑ በሀገር ውስጥ ጠግኖ ወደ ምርት የሚመልሰው ብቸኛው አዋሽ ባትሪ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ አይገኝም። በተለያዩ ምክንያቶች አዋሽ ባትሪ ስራውን ማቆሙን የነገረን ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ የቀድሞ የድርጅቱ ባልደረባ፣ “ያገለገሉ ባትሪዎች ተሰብስበው የተወሰኑ ግብዓት ተጨምረው ዳግም ወደ ገበያ ይቀርቡ እንደነበር” ይናገራል። 

በወቅቱ ከስራው ባህሪ አንፃር የጤና ስጋት መኖሩን የሚያስታውሰው ሰራተኛው የሰራተኞችን መከላከላያ ቁሳቁስ በተመለከተ ተደጋጋሚ እሰጣ ገባ እንደነበረም ያስታውሳል። አዋሽ ባትሪ ለምን ስራውን አቆመ ያልነው የቀድሞ የድርጅቱ ባልደረባ “ከፍተኛ የስክራፕ እጥረት ነበረብን” ይላል። 'እስክራፕ' ማለት የአገልግሎት ጊዜውን የጨረሰ የሊድ አሲድ ባትሪ ማለት ሲሆን ለእጥረቱ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ህገ-ወጥ የስክራፕ ወይም የአሮጌ ባትሪ ዝውውር እንደሆነ ይናገራል።

ወደ ኬኒያ በህገ-ወጥ መንገድ በገፍ መጋዙ የጥሬ እቃ እጥረት በተደጋጋሚ አንዲፈጠርና የምርት መቆራረጥ እንዲኖር እንዲሁም ተጨማሪ ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን የቀድሞ የድርጅቱ ሰራተኛ እንደክፍተት ያነሳል።

በኢትዮጵያ በ3 መንገዶች አሮጌ የሊድ አሲድ ባትሪዎች ይሰበሰባል። ከተጠቃሚዎች በቀጥታ ሽያጭ፣ በአሮጌ እቃ ሰብሳቢዎች (ቁራሌው) እና ከድርጅቶች በጅምላ ይገኛሉ። በእነኚህ ሂደቶች ውስጥ ስለባትሪው ባህሪ ባለማወቅ ምክንያት በአሰባሰብ፣ አያያዝ እና አወገጋድ ላይ ከፍተኛ ሆነ የጥንቃቄ ጉድለት እንደሚታዩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

አስተያየት