የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች ከህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. የጀመሩትን የስራ ማቆም አድማ ማቆማቸውን አስታወቁ።
ለአዲስ ዘይቤ በመምህራኑ የስራ ማቆም አድማ ዙሪያ መረጃ ያደረሱ የአድማው አስተባባሪዎች እንደገለፁት "የመጀመሪያ ዙር የስራ ማቆም አድማዉ ከዛሬ ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተጠናቋል" የሚል መግለጫ ማውጣታቸውን አስታውቀዋል።
ከሰኞ ጀምሮ ለአምስት ቀናት የተደረገው የስራ ማቆም አድማ የተቋረጠበት ምክንያትም “መንግሰት ለጥያቄዎቻችን ምላሽ እንዲሰጥ የሶስት ሳምንታት የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት” መሆኑን አስተባባሪዎቹ ገልፀዋል። ከዚህ ቀደም ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲ መምህራንና አስተባባሪዎች ጥያቄዎቻቸው እስከሚመለሱ ድረስ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚቀጥልና ያለፉት ቀናት አድማም ውጤታማ የሚባል እንደነበረ ሲገልፁ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፍ እስከማድረግ ድረስ ሊገደዱ እንደሚችሉ መምህራኖቹ ሲገልፁ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ከሚቀጥለው ሳምንት ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚመለሱ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ምላሽ ሳይገኝ የስራ ማቆም አድማው መቋረጡ ያበሳጫቸው መምህራን መኖራቸውን ማወቅ ተችሏል።
ለአዲስ ዘይቤ አስተያየታቸውን የሰጡት መምህራኖች "በድንገት ከዛሬ ጀምሮ አድማዉ አብቅቷል" መባሉ መጀመሪያዉን ለምን ተጀመረ የሚል ጥያቄ ይፈጥራል ብለዋል። “ከእኛ ጋር ዉይይት ሳያደርጉ ዉሳኔዉን ተቀበሉ ማለት አግባብ አይደለም” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ መምህራን “በአንድነት የተጀመረዉን ትግል ምላሽ ማግኘት እስከሚቻል ድረስ አድማዉ መቀጠል ሲገባዉ ነገር ግን ምንም ምላሽ ባልተገኘበት ወደ ስራ መመለሱ አግባብ አይደለም” ሲሉም ያስረዳሉ።
ከስራ ማቆም ጋር ተያይዞ የተለያዩ እንግልትና እስር የገጠማቸው መምህራኖች እንዳሉ እየታወቀ አድማዉ “ቢያንስ እስከ ሁለት ሳምንት መቀጠል ነበረበት” ብለው “መምህራንን ያላማከለ መግለጫ ተቀባይነት የለዉም” ሲሉ የአድማውን መቆም ተቃውመዋል።
መምህራኖቹ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ያነሳሳቸው "የደመወዝ ጭማሪ ፣ የደረጃ እድገት የስራ ክብደት ምዘና ጥያችት ተግባራዊ ይደረግ ፣ የቤት ኪራይ ዉሎ አበልና ሌሎች ተያያዥ ጥቅማጥቅሞች" እንዲከበሩላቸው በማለት እንደሆነ አዲስ ዘይቤ አስተባባሪዎቹን ዋቢ አድርጋ መዘገቧ ይታወሳል።
ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአድማዉ አስተባባሪ መምህራን ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት "ከታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራዉ እንደሚቀጥል እና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መንግስት ለጥያቄዎቹ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ በተለየና ከነበረው በተሻለ ስልት ወደ እርምጃ ይመለሳሉ"።
ለአምስት ቀናት በተካሄደው የስራ ማቆም አድማ በ38 ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ ተግባራዊ እንደተደረገ ቢገለፅም የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ አስተዳድሮች እና የዘርፉ አካላት የትምህርት አሰጣጡ በተገቢው መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ያሳወቁበት ሁኔታም ነበር።
በህጋዊነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለህዳር 26 የተጠራዉ የስራ ማቆም አድማ እዉቅና እንዳልሰጠዉ እና የዉሸት እንደሆነ ሲገልፅ መግለጫውን ያወጡት መምህራን ደግሞ በበኩላቸው ማህበሩ "እኛን አይወክለንም" ማለታቸው ይታወሳል።
የመምህራኑ የስራ ማቆም አድማ መነሻ "የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገት የስራ ክብደት ምዘና ተግባራዊ እንዲደረግ፣ የቤት ኪራይና የዉሎ አበል እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጥቅማጥቅሞች" እንዲከበሩላቸው ለመጠየቅ እንደሆነ አዲስ ዘይቤ ከአስተባባሪዎቹ መረዳት ችላለች።