ኅዳር 26 ፣ 2015

በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የመመረቂያ ጊዜያቸው የራቃቸው ተመራቂ ተማሪዎች አድማ አደረጉ

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮች

የሚመረቁበት ጊዜ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ሳቢያ የተራዘመባቸው ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርት አንገባም ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ምንም አልተፈጠረም ብሏል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የመመረቂያ ጊዜያቸው የራቃቸው ተመራቂ ተማሪዎች አድማ አደረጉ
Camera Icon

ፎቶ፡ አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ

በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ግቢዎች (ካምፓስ) ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙና በአራት ዓመታት ውስጥ መመረቅ የነበረባቸው ተማሪዎች አንድ ሴሚስተር ወደ ኃላ በመቅረታቸዉ ዘንድሮ አትመረቁም መባላቸዉን ተከትሎ ትምህርት የማቆም አድማ ላይ እንደሚገኙ ተናገሩ።

በተለይ ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸዉን ያቀረቡት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጫሞ፣ ሳዉላ እና ኩልፎ ግቢዎች ትምህርታቸዉን በመከታተል ላይ የሚገኙት ተማሪዎች በየግቢዉ የሚገኙ አመራሮችና መምህራኖች ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ላይ ከተማሪዎች ጋር በነበራቸው ዉይይት “ተማሪዎች ያልተማሯቸዉ ቀሪ ሶስት ሴሚስተሮች በመኖራቸዉና በዚህም ምክንያት በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ተመራቂ የነበሩት በቀጣይ ዓመት ጥር ወር ላይ ትመረቃላችሁ" መባሉን ገልፀዋል።

በዚህ ምክንያት ወደ ክፍል መግባት ካቆሙ ቀናቶች እንደተቆጠሩ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሌሎች ጓደኞቻችን እኩል የክረምት ወራትን ጭምር ተምረን መስከረም ወይም ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. ላይ መመረቅ ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም. ይመረቁ የነበሩ ተማሪዎች በ2014 ዓ.ም. ጥር ወር ላይ የተመረቁ ሲሆን በ2014 ዓ.ም. ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁት ደግሞ በ2014 ዓ.ም. ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ እና መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የምረቃት ስነ ስርዓት ተደርጎላቸዋል። 

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ በጫሞ ግቢ የሶስተኛ ዓመት 2ተኛ ሴሚስተር ተማሪ ለአዲስ ዘይቤ በአዲሱ የትምህርት ስርዓት በ2012 ዓ.ም. ወደ ዩኒቨርስቲ ከገቡት ተማሪዎች መካከል መሆኑን ይናገራል። “አንድ ሴሚስተር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ኋላ ቀርተናል ነገር ግን ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን ክረምት አስተምረዉ ዘንድሮ ያስመርቃሉ፤ እኛ ግን ረጅም ጊዜያትን ቤት እንድናሳልፍ ሆነን አንድ ሴሚስተር ሳንማር ቀርተናል። በዚህ ምክንያት ቀሪ ሶስት ሴሚስተሮችን እንድንጨርስ እና በቀጣይ 2016 ጥር ወር ላይ ትመረቃላችሁ" የሚል የትምህርት ፕሮግራም የሚያሳይ መርሀግብር መዘጋጀቱን ተናግሯል።

በተመሳሳይ በኩልፎ እና ሳዉላ ግቢዎችም ትምህርታቸዉን በመከታተል ላይ የሚገኙና በዘንድሮ የትምህርት ዘመን መመረቅ የነበረባቸው ተማሪዎች “የዩኒቨርስቲዉን ዉሳኔ እንደማይቀበሉ እና የሚቀሩ ሴሚስትሮችን በተከታታይ እንዲወስዱ እንዲደረግ” ጠይቀዋል።

የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በድሩ ሂርጎ የተማሪዎች ቅሬታን አስመልክተው ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት "ተከስቶ የነበረዉ የኮሮና ቫይረስ የትምህርት ስርዓቱን መቀየሩ እና ጊዜዉ እንዲዛባ አድርጎታል” ብለው ከዚህ ዉጪ ግን በመማር ማስተማር ላይ ምንም አይነት የተፈጠረ ክፍተት የለም" ብለዋል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጊዜያቸው ይዘገያል የተባሉት ተማሪዎችም "ተስፋ የመቁረጥ፣ ከሌሎች ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር እኩል ባለመመረቃቸዉ በስራዉ ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ጫና እንደሚፈጥር፣ የዩኒቨርስቲ መዉጫ ፈተና ቀነ ገደብ የተቀመጠ ሲሆን ነገር ግን ተማሪዎቹ ያላለቁ ትምህርቶች በመኖራቸው ፈተናዉን እንዲወስዱ መደረጉ በአዕምሯቸው ላይ ጭንቀት መፍጥሩንም” ይናገራሉ።

ጫሞ ካምፓስ ተማሪዎችን የሚያነሱትን ጥያቄ አስመልክቶ ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በግቢው በለጠፈው ማስታወቂያ እንደገለፀው "የ3ተኛ ዓመት ተማሪዎች የመመረቂያ ጊዜያቸዉ እንዲያጥርላቸዉ ጥያቄ ማቅረባቸውን" በመግለፅና ይህን በማስመልከት ከትምህርት ክፍሎች ጋር ተነጋግረው ስምምነት ማድረጋቸውን አሳዉቋል።

"ከዩኒቨርስቲው የበላይ አካላት ጋርም ተነጋግረው የትምህርት ካላንደር ላይ የሚሰጡ ምላሾችን እናሳዉቃለን" በማለት የገለፀ ሲሆን ተማሪዎች "ትምህርታቸውን መቀጠል" እንዳለባቸዉም አሳስቧል። ይሁን እንጂ ቅሬታ አቅራቢዎቹ "የምርቃት ቀኑ ተቆርጦ የማይነገረን ከሆነ ትምህርት ለመቀጠል እንቸገራለን" ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ የፈጠረዉን ክፍተት ለማስተካከል ዩኒቨርስቲው ስራዎችን እየሰራ ይገኛል የሚሉት የዩኒቨርሲቲው የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ከዚህ ቀደም በየአመቱ አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ተማሪዎች እንዲመረቁ የሚደረጉት ነገር ግን በቫይረሱ ምክንያት ግን ሊዛባ እንደቻለ እና በበፊቱ አሰራር መቀጠል እንዳልተቻለ አክለዋል። 

የ2015 ዓ.ም. የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የትምህርት ፕሮግራም በሚያሳየዉ መርሀግብር ላይ ሐምሌ 8 ቀን 2015 እንዲሁም በሳዉላ ግቢ ደግሞ ሐምሌ 9  ትምህርታቸውን በሰዓቱ የሚጨርሱ ተማሪዎች በመደበኛና በርቀት ዘርፍ በወጣው መርሀግብር ይመረቃሉ ተብሏል።

ዩኒቨርስቲው "አላስመርቅም" አላለም በማለት በተለይ ለአዲስ ዘይቤ የተናገሩት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በድሩ ሂርጎ "ተማሪዎች ሳይማሩ የቀሩትን ትምህርቶች በሚችሉት ደረጃ ከመምህራኖቻቸዉ ጋር ተናበዉ መዉሰድ ይችላሉ በዚህ ሁኔታ ኮርሶቻቸዉ የሚያልቁ ከሆነ መመረቅ ይችላሉ"። አሁን ግን የትምህርት አሰጣጡ እንደቀጠለ ነው ብለዋል።

በአዲሱ የትምህርት ትግበራ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሶስት ዓመት ይጠናቀቁ የነበሩት ትምህርቶች ወደ አራት ዓመት እንዲቀየሩ መደረጋቸዉ ይታወሳል። በዚህ ምክንያት ክረምትን ጨምሮ ተማሪዎቻቸውን ያስተማሩ ዩኒቨርስቲዎች በዘንድሮው የትምህርት ዘመን እንደሚያስመርቁ ባደረግነዉ ዳሳሳ ለማወቅ ችለናል።

አስተያየት