ታህሣሥ 4 ፣ 2015

አወዛጋቢው የዘመነ ካሴ የፍርድ ሂደት በጠበቃው እይታ

ዜናወቅታዊ ጉዳዮች

“በዘመነ ጉዳይ ፍርድ ቤቱም ሆነ ፖሊስ ገለልተኛ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ክሱ ፖለቲካዊ እንደመሆኑ የፖለቲከኞችን ተፅዕኖ መቋቋም አልቻሉም” በማለት ጠበቃው ይናገራሉ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

አወዛጋቢው የዘመነ ካሴ የፍርድ ሂደት በጠበቃው እይታ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

የአማራ ክልላዊ መንግስት ከወራት በፊት ሕግ ማስከበር ያለውን ዘመቻ ባካሄደበትና በሺዎች የሚቆጠሩ “ሕገ ወጥ ያላቸውን ታጣቂዎች” በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ሲፈለጉ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ዘመነ ካሴ ነበር። 

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሮ ሲፈልገው እንደቆየ የገለጸውን ዘመነ ካሴን መስከረም 11 ቀን 2015 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 03 በግለሰብ ቤት ከ541 ሺህ ብር ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

ዘመነ ካሴ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል። ከአስተያየቶቹ መካከል ዘመነ ውጥረቱን ለመፍታት ለሽምግልና ተጠርቶ መጥቶ ተክዶ ነው የሚለው በስፋት የተንሸራሸረ አስተያየት መሆኑ ይታወሳል።

የዘመነን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን የታክቲክ ምርመራ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ክንዱ ወንዴ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ "ዘመነ ካሴ በኅብረተሰቡ ጥቆማ በሕግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሔደበት ነው" ብለዋል።

አቶ አዲሱ ጌታነህ የህግ አማካሪና ጠበቃ ናቸው። ከሌሎች ሁለት ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለዘመነ ካሴ ጥብቅና ቆመው በችሎት እየተከራከሩ ይገኛሉ። በዚህ ፖለቲካዊ ነው ተብሎ በብዙዎች ዘንድ በታመበት የዘመነ ካሴ የፍርድ ሂደት ዙሪያ ያላቸውን ሙያዊ አስተያየትና ትዝብት ለአዲስ ዘይቤ አጋርተዋል።

ዘመነ ካሴ በህግ ቁጥጥር ስር በዋለበት ጊዜ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ዘመነ ካሴን "ህገ ወጥ ቡድን በማደራጀት እና ኬላ ዘርግቶ ገንዘብ በመሰብሰብ እንዲሁም በፌስ ቡክ ቅስቀሳ ማድረግ..." በሚሉ ወንጀሎች ጠርጥሬዋለሁ በማለት ለፍርድ ቤቱ እንዳስታወቀ አቶ አዲሱ ይናገራሉ፣ ሂደቱን ከመሰረቱ ሲያስረዱ።

በወቅቱ ፖሊስ ወንጀሎችን ለማጣራት የጊዜ ቀጠሮ በተደጋጋሚ ጠይቋል ያሉት ጠበቃው፣ ነገር ግን ፖሊስ ለወራት ጉዳዩን ያጣራ መሆኑን በመግለፅ እና ሌሎች መከራከሪያዎችን በማቅረብ ጊዜ ቀጠሮ መስጠት ሳያስፈልግ፣ ሌላ ማስረጃ ማቅረብ የማይቻል ከሆነ ዘመነ በዋስ እንዲለቀቅ መከራከሪያ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ ጠበቃና የህግ አማካሪው አቶ አዲሱ።

እንደ ጠበቃው ገለጻ ፍርድ ቤቱ የምርመራ ቡድኑ ያቀረበው ምክንያት በቂ አለመሆኑን ቢያምንም በተለያዩ ቀናት የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ፖሊስ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ምርመራውን እንዲያጠናቅቅ ትዕዛዝ ሲሰጥ ቆይቷል።

የዘመነ ካሴ ጉዳይን በተመለከተ ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ 14 ቀናት ውድቅ ቢያደርግም ዐቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ወይም በተለምዶ የክስ ማዘጋጃ ግዜ የሚባለውን 15 ቀናት ሰጥቷል።

ውሳኔውን በተመለከተ ለዐቃቤ ህግ የተሰጠው 15 ቀናት የክስ ማዘጋጃ ጊዜ አቃቤ ህግ በችሎት ቀርቦ ጥያቄ አቅርቦ የተሰጠው ሳይሆን ተከራካሪዎች ብይን እስኪሰጥ ለመጠባበቅ በወጡበት የተሰጠ ፈቃድ ነው በሚል የዘመነ ጠበቆች ቅሬታቸውን በወቅቱ አሰምተዋል።

አቶ አዲሱ በወቅቱ የነበረውን ሂደት ሲገልፁ ፍርድ ቤቱ ለአቃቤ ሕግ የሰጠውን የክስ ማዘጋጃ የ15 ቀናት ጊዜ (ያውም ካለ ጠበቆች ይሁንታ) ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ በተጠቀሰው ቀን ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በመቅረቱ ክርክሩ ሳይደረግ ቀርቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በዘመነ ካሴ ላይ በ"ከባድ የሰው ግድያ" ወንጀል አዲስ ክስ ተመሰረተ። “ይህ በጣም አሳዛኝ ነው። ይህ ክስ ችሎት ላይ ሲቀርብ ክሱ ፓለቲካዊ ከመሆኑ በተጨማሪ በቂ ማስረጃ ያልቀረበበት ነው” ይላሉ ጠበቃው። 

እንደ አቶ አዲሱ ማብራሪያ በክሱ መሰረት ለፀጥታ ስራ የተሰማራን የፖሊስ አባል ዘመነ መግደሉ የተገለፀ ሲሆን በተጨማሪም በቂ ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም። “ለምሳሌ ሟቹ ምን ሊያደርግ ወደ ዘመነ ሄደ? መሳሪያ ታጥቆ ነበር? በትክክል በክሱ ላይ በተገለፀው መሰረት ሟች መሞቱን ሊያሳይ የሚችል ማስረጃ አልቀረበም። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ይህን መከራከሪያ ተቀብሎ ክሱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ሰጥቷል” በማለት ጠበቃው ይናገራሉ።

ጠበቃው በፍርድ ሂደቱ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ሲገልፁ “በክሱ ላይ እንደተገለጸው በምስክርነት የቀረቡት ህግ ማስከበር ላይ የነበሩ ናቸው የተባሉ የፀጥታ አካላት ዘመነ ሟችን በትክክል ሲገድለው አይተዋል የሚለው በራሱ አጠያያቂ ነው። የፀጥታ አካላት እንደመሆናቸው አብሯቸው የተሰማራ የፀጥታ ባልደረባቸው ላይ ጥቃት ሲደርስበት ምን እርምጃ ወሰዱ? ተከታትለው ኃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው ሊጠየቁ ይገባ ነበር። ምክንያቱም ከሌላው ዜጋ በተለየ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ግድያ ተፈፀመ በተባለበት ወቅት ኃላፊነታቸው አልተወጡምና” ይላሉ።

እንደ ጠበቃው ገለፃ የባህር ዳር እና አካባቢው ፍርድ ቤት ከላይ በተገለፀው ምክንያት ክሱ እንዲሻሻል እና እንዲቀርብ ለህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ቢሰጥም በዕለቱ ዘመነ ካሴ "ክሱ ግልፅ አይደለም፣ ችሎት ለመቅረብም የደህንነት ስጋት አለብኝ" በማለት ፍርድ ቤት ለመቅረብ እንቢተኝነቱን ገልጿል። 

የዘመነን ስጋት በተመለከተ ጠበቃው እንደሚሉት በችሎት ወቅት በበርካታ ልዩ ሀይሎች እንደሚታጀብ እና መንገድ ከመዘጋቱ በተጨማሪ ችሎት መታደም ተከልክሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የዘመነ ካሴ የችሎት ቀናት የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ መመልከት እንደቻለው ቀይ ቦኔት ለባሽ ኃይሎችና የከተማ ፖሊሶች ወደ ፍርድ ቤት የሚወስዱ በአራቱም አቅጣጫ ያሉት ሁሉም መንገዶች ይዘጉ ነበር።

ዘመነ ካሴ ፍርድ ቤት አልቀርብም ብሎ ምክንያት ሲያቀርብ ችግሩን ፈትቶ ክርክሩ እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ ማድረግ አለበት የሚሉት ጠበቃው ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ በፅሁፍ መልስ እንዲሰጥ ማዘዙ ተገቢ አይደለም ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። “ማረሚያ ቤቱም ቢሆን የተከሳሽን ስጋቶች ቀርፎ ተከሳሽን ማቅረብ ይገባዋል” ይላሉ ጠበቃና የህግ አማካሪው አቶ አዲሱ።

“ዘመነ ካሴ  በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፖሊስ “ህገ ወጥ ቡድን በማደራጀት እና ኬላ ዘርግቶ ገንዘብ በመሰብሰብ እንዲሁም በፌስ ቡክ ቅስቀሳ ማድረግ..." በሚሉ "ወንጀሎች" ጠርጥሬዋለሁ ብሎ ክስ መስርቶበታል። ነገር ግን ክሱን ለማስቀጠል የሚያስችል በቂ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም ስለዚህ ሲፈልግበት የነበረው ጉዳይ አብቅቷል ማለት ነው” ይላሉ አቶ አዲሱ ኃሳባቸውን ሲያስረዱ።

“ነገር ግን እንደገና 'ከባድ ሰው መግደል ወንጀል' የሚል ክስ መመስረት ጉዳዩ ፖለቲካዊ ለመሆኑ ሌላኛው ማሳያ ነው” በማለት ጠበቃው ይገልፃሉ።

አቶ አዲሱ የዘመነ ካሴ ችሎትን በተመለከተ የተገኙባቸውን ችሎቶች በመጥቀስ “በዘመነ ካሴ ችሎት ጉዳይ ፍርድ ቤቱም ሆነ ፖሊስ ጉዳዩን በገለልተኝነት ለማየት ጥረት ሲያደርጉ ታዝቤለሁ። ነገር ግን ክሱ ፖለቲካዊ እንደመሆኑ መጠን የፖለቲከኞችን ተፅዕኖ መቋቋም አልቻሉም” ይላሉ ለአዲስ ዘይቤ ትዝብታቸውን ሲያጋሩ።

አስተያየት