መስከረም 29 ፣ 2015

ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ከገቡት ተማሪዎች 16 ሴቶች የልጅ እናት ሆነዋል

City: Hawassaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ወደ ዩኒቨርስቲዎች ለፈተና ከገቡ ተማሪዎች በአጠቃላይ 16 ሴቶች የልጅ እናት መሆናቸዉ ታውቋል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ከገቡት ተማሪዎች 16 ሴቶች የልጅ እናት ሆነዋል
Camera Icon

ፎቶ፡ ከማህበራዊ ሚድያ

የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመዉሰድ ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከገቡት ተማሪዎች መካከል 16 ነፍሰ ጡር ተማሪዎች በሰላም ልጆቻቸውን መገላገል መቻላቸው ተነግሯል።

የትምህርት ሚኒስትር የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት በሚል የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች እንዲሰጥ መወሰኑን ተከትሎ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኝ ተማሪዎች ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ ተደርጓል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከመጣችው ተማሪ ፅጌረዳ አበራ ወንድ ልጅ የመዉለዷ ዜና ከተሰማ ወዲህ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት መስከረም 29 ቀን ድረስ ለፈተና ዩኒቨርስቲ ከገቡት ተማሪዎች 16 ነፍሰ ጡር ሴት ተማሪዎች መውለዳቸው ተሰምቷል።

ከነዚህ ነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል በቡሌሆራ ዩኒቨርስቲ መንታ ልጆችን ከተገላገለችው ተማሪ በተጨማሪ ሶስት ሴት ተማሪዎች ወልደዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የተመደበችው ተማሪ መድሃኒት መንታ ልጅ ታቅፋለች።

በአማራ ክልል ከምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ ዋብር መሰናዶ ትምህርት ቤት ለፈተና ወደ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የመጣችዉ ባለትዳር ተማሪ ደብረማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሴት ልጅ እንደተገላገለችም ታውቋል።

አምስተኛዋ ተማሪ ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጅማራሬ ወረዳ ጎዳ ቢሎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ የመጣችው ጌጤ በቀለ አምቦ ከተማ ከደረሰች በኋላ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ልጅ መዉለዷ ተነግሯል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ መንታ ልጅ የተገላገለችዉን ተማሪ ጨምሮ 4 ነፍሰጡር የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲሁም በቦረና፣ በወራቤ፣ ጋምቤላ፣ ሚዛንቴፒ እና በወልድያ ዩኒቨርስቲዎች ለፈተና ከገቡ ተማሪዎች 16 ሴት ተማሪዎች የልጅ እናት መሆናቸዉ አዲስ ዘይቤ ከዩኒቨርሲቲዎቹ የመረጃ ምንጮች ማወቅ ችላለች።

ከመስከረም 30 ጀምሮ በሚሰጠዉ የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ976 ሺህ ተማሪዎች በላይ ለፈተና የሚቀመጡ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርስቲ ተጠቃለዉ መግባታቸው ተገልጿል።

አስተያየት