“ባለቤትህ እንዳትሰማ?” ይላል ባልየው አቶ ውብሸት ስልክ የሚያናግር በመምሰል ድምጹን ጮክ አድርጎ።
“ምን አባቷ አገባት?! አትደሪ እያልኳት ሰርግ ቤት ካደረች ጀምሮ ያንቺ ብቻ ሆኛለሁ፤ መሲ ሙች” ይላል መልሶ በቀጭኝ ግድግዳ ለሁለት በተከፈለው ሳሎን ውስጥ ሆኖ ወደ እዛኛው ክፍል ድምጹ እንዲሰማ እየጣረ።
ባልየው በወዲያኛው ሳሎን ያለችው ሚስቱን (ትዝታን) ለማስቀናት ብዙ ይጥራል። ከሌላ ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት እንደጀመረ አስመስሎ ድምጹን ከፍ አድርጎ ያወራል። ሴት ይዞ በመምጣት ተወዳጅነቱን ትዝታ እንድትሰማ እና እንድትቀና የማያደርገው ነገር የለም። ሚስትየውም በበኩሏ የእሱን ፈለግ በመከተል ባሏን ለማስቀናት ትፍጨረጨራለች።
በዚህ መልክ ባልና ሚስቱ አንዳቸው ሌላውን ለማስቀናት በነገር ቢሸነቋቆጡም መፈላለጋቸውና መዋደዳቸው ጎልቶ የሚታይበት ቴአትር ነው፤ ባቢሎን በሳሎን። ትያትሩ በድንቅ የትወና ብቃት ተመልካቹን በሳቅ እያዋዛ የትዳርን ሌላ ገፅታ የሚያሳይ ነው። በተለይ ዋና ገጸ ባህሪዎቹን (የባልና የሚስቱን) የሚጫወቱት ተዋንያን ዓለማየሁ ታደስና ሉሌ አሻጋሪ የትወና ብቃት ድንቅ እንደነበር ቴአትሩን ያዩ ተመልካቾች ይመሰክራሉ።
የኮሜዲ ዘውግ ያለው ባቢሎን በሳሎን ቴአትር ላለፉት 22 ዓመታት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ሲታይ ቆይቷል። በተለያዩ ጊዜያት ተቋርጦ እንደገና ወደ መድረክ ተመልሶ እንደተወደደ ለረዥም ጊዜ ዘልቋል። ብዙ የቴአትር አፍቃሪዎች ባቢሎን በሳሎንን በተደጋጋሚ መመልከታቸውን ሲናገሩ ይሰማል።
ከነዚህም መካከል አቶ ዓለማየሁ ግርማ የተባሉ ግለሰብ ቴአትሩን ለ69 ጊዜ መመልከታቸውን ለፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ባቢሎን በሳሎን በደራሲ ውድነህ ክፍሌ ተፅፎ በተስፋዬ ገብረሀና እና ከዚህ ዓለም በሞት በተለየው አርቲስት ሰለሞን ሙላት ተዘጋጅቷል። አለማየሁ ታደሰ፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ራሄል ተሾመ፣ ሰላማዊት በዛብህ፣ እመቤት ወ/ገብርኤል፣ ህንፀተ ታደሰ፣ እንድሪስ አህመድ፣ ሉሌ አሻጋሪ እና ሌሎችም በትወና ተሳትፈውበታል።
በ1992 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለመድረክ የበቃው ባቢሎን በሳሎን በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ለረዥም ዓመታት በመታየት ባለክብረ ወሰን እንደሆነ ይነገርለታል።
ቴአትሩ ለመጨረሻ ጊዜ መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም በርካታ የጥበብ ባለሙያዎችና ታዳሚዎች በተገኙበት በብሔራዊ ቴአትር ለተመልካች ቀርቦ ከመድረክ ተሰናብቷል።
በስንብት መርሃ ግብሩ ብዙዎች ቴአትሩን ለመጨረሻ ጊዜ ለመመልከት በቴአትር ቤቱ ደጃፍ ቢሰለፉም አዳራሹ በመሙላቱ ከበር ተመልሰዋል። በእለቱ የነበረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች ቴአትሩን ለመጨረሻ ጊዜ ለመመልከት ከነበረው ፍላጎት የተነሳ የቴአትር ቤቱ መግቢያ በር መስታወቶች እስከመሰባበር መድረሳቸውም ተዘግቧል።