ጥቅምት 1 ፣ 2015

ግብር የመክፈል ግዴታ ተፈፃሚ የተደረገባቸው የአማራ ክልል የድለላ ሰራተኞች

City: Bahir Darማህበራዊ ጉዳዮችንግድ

ሁለቱ ወገኖች በደላላ መገበያየታቸውን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከደረሰበት ደላላው ይከፍል የነበረውን ግብርና ታክስ እጥፍ ሻጭና ገዥ እንዲከፍሉ ይደረጋል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ግብር የመክፈል ግዴታ ተፈፃሚ የተደረገባቸው የአማራ ክልል የድለላ ሰራተኞች
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚድያ

አቶ ይትባረክ ታደሰ በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 የሚገኘውን ባለሁለት ወለል ህንፃቸውን በአስራ አምስት ሚሊዮን ብር ሸጡት። ሽያጩ የተከናወነው በደላሎች አማካኝነት በመሆኑ ሁለት በመቶ የኮሚሽን ክፍያ ማለትም ሶስት መቶ ሺህ ብር ለደላሎቹ ከፈሉ።

“አማራጭ ስለሌለ ነው እንጅ ለደላላ ሁለት በመቶ መክፈል አዋጭ አይደለም” ይላሉ አቶ ይትባረክ። ምክንያቱን ሲያስረዱም “እኔ ከሽያጩ ላይ ለመንግስት ተገቢውን ግብር ከፍያለው። ደላሎች ግን ምንም አይከፍሉም። ይህ ትክክል አይደለም” ሲሉ ፤ሰው ለሰራበት ክፍያ መቀበሉ ተገቢ ቢሆንም ከገቢው ላይ አስፈላጊውን ግብር የመክፈል ግዴታ እንዳለበት ይጠቁማሉ።

እንደ አቶ ይትባረክ ታደሰ ገለፃ ያለ ደላሎች ሽያጭ እና ግዢ ማከናወን ከባድ ነው። “ከለፉበት በላይ ብዙ ብር ቢያገኙም ገዢ ከማፈላለግ ጀምሮ ስምና ንብረት ዝውውር ደረስ ያለውን ሂደት በደንብ ስለሚያውቁት ያቀላጥፉታል” ይላሉ።

በአማራ ክልል በድለላ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች ግብር እንዲከፍሉ የሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያ ተዘጋጅቷል። የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በደንብ ቁጥር 162/2010 መሰረት ማንኛውም በክልሉ የድለላ ስራ የሚሰራ ሰው ከሚያገኘው ገቢ 30 በመቶ ግብር እንዲከፍል መደንገጉ ይታወቃል። 

ደንቡን ለማስፈፀም በያዝነው 2015 ዓ.ም ጀምሮ ደላሎች ግብር እንዲከፍሉ የተዘጋጀ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 19/2015 ጸድቆ ተግባራዊ አንዲሆን ተወስኗል።

በባህር ዳር ከተማ ከመንግስት ማዘጋጃ ቤት ቀጥሎ እጅግ ወረፋ የሚበዛበት ቦታ ቢኖር ቀበሌ 5 ሜላት ካፌ አካባቢ የሚገኘው “ማርታ ፎቶ ኮፒ ቤት” ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ፎቶ ኮፒ ቤቷ አነስተኛ የብረት ቤት /ኮንቴይነር/ ብትሆንም በውስጧ በርካታ ደላላ ሰራተኞች ገዥና ሻጭ እንዲሁም አከራይና ተከራይን ውል በማዋዋል ስራ ተጠምደው ይውላሉ። 

በድርጅቱ ተቀጥራ የምትሰራና ስሟን መግለፅ ያልፈለገች ሰራተኛ በቀን እስከ መቶ ሃምሳ ሰው እንደሚያስተናግዱ ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች። በዚህ የድለላ የስራ ሂደት በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ሃብትና ንብረት ውል ይፈጸማል። በአገልግሎቱም ምንም ዓይነት ግብር የማይከፍሉት ደላሎች በመቶ ሺዎች የሚገመት የኮሚሽን ክፍያ እንደሚያገኙ ይነገራል። 

በባህር ዳር እና አካባቢዋ ቤት፤ መሬት፣ መኪና የመሳሰሉት መሸጥ እና መግዛት የፈለገ ሰው በከተማዋ እድሜ ጠገብ ከሆነው ሜላት ካፌ አጠገብ ማርታ ፎቶ ኮፒ መገኘቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ፎቶ ኮፒ ቤት የህግ አንቀፆችን ያዘሉ የተለያዩ የሽያጭ እና የቀብድ ውሎች በወረፋ ይሸጡበታል።

በዚህ አካባቢ በእግር ወይም በተሽከርካሪ ለሚያልፍ ሰው በርካታ ደላሎች፣ ሻጭና ገዢዎች እንዲሁም አከራይና ተከራይ ተሰብስበው በወረፋ ወረቀት ሲያገላብጡ መመልከት ለከተማው ነዋሪ የተለመደ ተግባር ነው። 

ደላሎች በዋነኝነት ቤት፤ መሬት፣ መኪና እና ቁሳቁሶችን ማሻሻጥና ማከራየት፤ ሰሪና ሰራተኛ ማገናኘት ስራዎች ላይ ተጠምደው ይውላሉ። እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልፅ ባይሆንም የፍቅር ወይም የትዳር አጋርም ያገናኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ እህል፣ ከብት፣ ወርቅ፣ ቡናና ሲሚንቶ በመሳሰሉ የሸቀጦች ግብይት ላይ ዋጋ እስከ መወሰን ደርሰዋል።

እንደ ሌሎች የሀገራችን ከተሞች ሁሉ በባህር ዳር ከተማ በየሰፈሩ ያሉ ትንንሽ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ የስልክ እና የመብራት ቋሚ ምሶሶዎች ላይ የድለላ ማስታወቂያ በብዛት ይታያል። አሁን አሁን ደግሞ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ጭምር የድለላ ማስታወቂያ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

አቶ ይበልጣል (ስሙ የተቀየረ) በባህር ዳር ከተማ ለበርካታ ዓመታት እራሱን እና ቤተሰቡን በድላላ ስራ አስተዳድሯል። አቶ ይበልጣል እንደሚለው በባህር ዳር እና አካባቢዋ የድለላ ስራ “በአየ በሰማ” በመሆኑ በብዛት የቀብድ ወይም የሽያጭ ውል በሚፈፀምባቸው ቦታዎች ጊዜውን ያሳልፋል። “በአየ በሰማ” ማለት ስራው ሲሳካ ያየ እና የነበረ ደላላ የበኩሉን የኮሚሽን ክፍያ የሚያገኝበት አሰራር ነው።  

እንደ አቶ ይበልጣል ገለፃ እሱም ሆኑ ጓደኞቹ የንግድ ፍቃድ የላቸውም። “በከተማዋ የሚገኙ አብዛኞቹ ደላሎች እኔን ጨምሮ ማህበር አለን። በማህበራችን በኩል በሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት የተለያየ ድጋፍ አድርገናል። ነገር ግን ምንም አይነት ግብር አንከፍልም” ይላል። 

“ስራው አልፎ አልፎ የሚሳካ ሰራ ነው። ከብዙ ድካም በኋላ ሁሉ ላይሳካም ይችላል” በማለት በዚህም ምክንያት እሱም ሆነ ጓደኞቹ የንግድ ፍቃድ የማውጣትም ሆነ ግብር የመክፈል ሃሳብ እንደሌላቸው አቶ ይበልጣል አልሸሸገም። 

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አጉማስ ጫኔ በበኩላቸው ለአዲስ ዘይቤ በሰጡት ማብራሪያ “ማንኛውም ሻጭ ወይም ገዥ እንዲሁም አከራይ ወይም ተከራይ የድለላ ክፍያ የሚፈፅመው ደላላው ህጋዊ ንግድ ፍቃድ እና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ካለው ብቻ መሆን አለበት” ይላሉ። 

የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ማንኛውም ሻጭና ገዥ ወይም አከራይና ተከራይ ጉዳዩን ሲፈፅም ያገዘውን ደላላ በሚመለከተው አካል ሲጠየቅ በአፈፃፀም መመሪያው መሰረት የማቅረብ ግዴታ አለበት። ይህም የድለላ ባለሙያዎችን ወደ ህጋዊ የአስራር መስመር ያስገባል ተብሎ ታምኖበታል።

በ1952 ዓ.ም የወጣውን የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ የተካው አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንግድ ሕግ ምዕራፍ አምስት አንቀጽ 54(1) “ደላሎች ማለት ውል የሚዋዋሉ ሰዎችን በተለይም እንደ ሽያጭ፤ ኪራይ፤ ኢንሹራንስ፤ የማመላለሻ ውል እንደዚህ ያሉትን ውሎች የሚዋዋሉ ሰዎችን ፈልገው የሚያገናኙና የሚያዋውሉ፤ ራሱን የቻለ የሙያ ተግባራቸው አድርገው ጥቅም ለማግኘት የሚሠሩ ሰዎች ወይም ይህንኑ የደላላነት ሥራ የሚሠራ የንግድ ማኅበር ነው” ይላል።

በሌላ በኩል “ሻጭና ገዢ የስምና የንብረት ዝውውር ሲያደርጉ በመካከላቸው ደላላ ከሌለ ምንም ክፍያ ለመክፈል አይገደዱም” ያሉት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ነገር ግን በደላላ መገበያየታቸውን ተቋሙ (የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ) ከደረሰበት ደላላው ይከፍል የነበረውን ግብርና ታክስ እጥፍ ሻጭና ገዥ እንዲከፍሉ ይደረጋል።

በተጨማሪም ሻጭና ገዢ በደላላ አለመገበያየታቸውን ተቋሙ በራሱ ኢንተለጀንስ እና ክትትል የማረጋገጥ ስልጣን እንደተሰጠውም የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አጉማስ ጫኔ ነግረውናል።

ሻጭ ወይም ገዥ እንዲሁም አከራይ ወይም ተከራይ የድለላ ክፍያ በባንክ እንዲከፍል ከተጣለበት ግዴታ በተጨማሪ የንግድ ፍቃድ እና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ለሌለው ደላላ ክፍያ ፈፅሞ የተገኘ ተገልጋይ ግብር እና ታክሱን እራሱ የመፈፀም ግዴታ እንዳለበት የተዘጋጀው አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 19/2015 በግልፅ አሰቀምጧል።

በሌላ በኩል በአዲሱ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ምዕራፍ አምስት አንቀጽ 54(2) “ደላሎች አስማሚ ሆነው የሚያስፈጽሟቸው ውሎች ዓይነትና ግብ ወይም የሚያገናኙዋቸው ሰዎች ማንነት ወይም ሁኔታ ሳይታይ ነጋዴዎች ይባላሉ” ይላል።

በአዲሱ የንግድ አዋጅ መሰረት የድለላ ስራ የሚስራ ሰው በግልጽ “ነጋዴ” እንደሚባል ይገልጻል። በመሆኑም የንግድ ፍቃድ የማውጣት እና ይህን ተከትሎም የሚመጡ ግዴታዎችን መወጣት እንዳለባቸው ይታመናል። ነገር ግን በባህር ዳር እንዲሁም ሌሎች የሀገራችን ከተሞች የሚገኙ ደላሎች ንግድ ፍቃድ ሲያወጡም ሆነ ግብር ሲከፍሉ አይታይም።

በሀገራችን ጥቂት የድለላ መስኮች በሕጋዊ መልኩ እየሰሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። ከነዚህም መካከል የመድህን ዋስትና ደላሎች በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሚሰጣቸው እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሆናቸውን በአዲሱ የንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ተደንግጓል፡፡

የድለላ አበልን በተመለከተ አዲሱ የንግድ አዋጅ አንቀፅ 57(1) እንደሚያስቀምጠው ተገልጋዩ “በደላላው አስማሚነት ውሉን ካስጨረሰ የውሉ ግዴታ ቢፈፀምም ባይፈፀምም ደላላው አበሉ ይከፈለዋል”።

በሌላ በኩል ተዋዋዩና ደላላው የአበሉን መጠን ቢስማሙም እንኳን የተስማሙበት አበል ከፍተኛ መስሎ ህጉ ከታየው ወይም ደላላው ከሰጠው አገልግሎት ጋር ተመዛዛኝ አለመሆኑን ካመነበት የንግድ ሕጉ በአንቀፅ 57 (3) ላይ የክፍያ መጠኑን የመቀነስ ስልጣን ለፍ/ቤት ተሰጥቶታል።

አስተያየት