ለ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ከተመደቡት ተማሪዎች ዉስጥ የወለዱ እና የነፍሰጡር ተፈታኝ ሴቶች ቁጥር መብዛት በፈተናው ላይ ተጨማሪ ጫና እንደፈጠረ ተገልጿል።
በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ከተመደቡ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል አራት ሴቶች ልጅ ሲወልዱ 82 የሚሆኑት ነፍሰጡር ተማሪዎች ደግሞ የቅድመ ወሊድ ክትትል እያደረጉ ነዉ ተብሏል።
በመጀመሪያ ዙር ለሚሰጠው ፈተና ወደ ዩኒቨርስቲው ተመድበው ከመጡት ተማሪዎች ዉስጥ በአጠቃላይ 174 የሚሆኑት የወለዱ እና በቅርብ ሊወልዱ የሚችሉ ነፍሰጡር መሆናቸዉ አሳሳቢ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ራዲዮ የጤና ባለሞያዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ተማሪዎቹ ከነገ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ መጡበት የሚመለሱ ቢሆንም ማህበረሰብ እና መንግስት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተዉበት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቋሚ መሆኑ ተገልጿል።ለፈተና በጋምቤላ ፣ አርባምንጭ ፣ ድሬዳዋ ፣ወራቤ ፣ ቡሌሆራ እና ወልድያን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ10 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ የተመደቡ ነፍሰጡር ሴት ተማሪዎች መወለዳቸውን ሪፖርት መደረጉ ይታወሳል።