ጥቅምት 5 ፣ 2015

የአዳማ ከተማን የ20 ዓመታት የውሃ አቅርቦት ያሟላል የተባለለት ፕሮጀክት ውል ተቋረጠ

City: Adamaየከተማ ልማትዜና

የአዳማ ከተማ የቀጣዮቹ 20 ዓመታት የውሃ አቅርቦት ያሟላል ተብሎ 2.4 ቢልየን ብር በጀት የተጀመረው የሞጆ-አዳማ የውሃ ፕሮጀክት በ18 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም እስካሁን ሂደቱ 23 በመቶ ላይ ይገኛል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአዳማ ከተማን የ20 ዓመታት የውሃ አቅርቦት ያሟላል የተባለለት ፕሮጀክት ውል ተቋረጠ

የአዳማ ከተማ እና በአቅራቢያ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለለት የሞጆ-አዳማ የዉሃ ፕሮጀክት መዘግየቱ ተገለፀ።

በሐምሌ 2013 ዓ.ም የተጀመረው እና በ18 ወራት ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት እስከ አሁን ያለው አፈጻጸም 23 በመቶ ላይ እንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ ከአዳማ ውሃ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ከአቶ አህመድ አብዱልጀሊል ተረድታለች።

ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የ48 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ ከኦሮሚያ ክልል በተመደበ 500 ሚሊዮን ብር እና የአዳማ ከተማ አስተዳደር በመደበው 150 ሚሊዮን በድምሩ 2.4 ቢሊዮን ብር የተጀመረው ፕሮጀክቱ የአዳማ ከተማ የቀጣይ 20 ዓመታት የውሃ አቅርቦት እንደሚያሟላ የታቀደ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ለፕሮጀክቱ መጓተት “ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር የተፈጠረ አለመግባባት ነው” ያሉት አቶ አህመድ በሳምንት ጊዜ ውስጥ አዲስ አማካሪ ድርጅት ጋር ውል ተፈርሞ ወደ ስራ ሊገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን በቀጣይ 16 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅምም ተናግረዋል።በአሁን ወቅት በአዳማ ከፍተኛ የውሃ አቅርቦት መቆራረጥ እንዲሁም የውሃ ጥራት ችግር የሚታይባት ከተማ ስትሆን ይህን ይቀርፋል የተባለው የሞጆ አዳማ የውሃ ፕሮጀክት መጓተት በኗሪዎችን ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ እየዳረገ ይገኛል።

ይህንን ፕሮጀክት በተመለከተ ባሳለፍነው ግንቦት ወር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መጎብኘቱና ዝቅተኛ አፈጻጸሙ እንዲታረም ምክረ ሀሳብ የተሰጠበት መሆኑም ይታወቃል።

አዳማ ከተማ ከ400 ሺህ ነዋሪዎች በላይ እንደሚገኙባት የሚገመት ሲሆን የውሃ አቅርቦትም በተደጋጋሚ ከነዋሪዎች የሚነሳ ጥያቄ ነው።

አስተያየት