ሰኔ 8 ፣ 2013

ብሎክቼይን ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ: ተስፋና ስጋቶች

ቴክአስተያየት

ስለ ብሎክቼይን ቴክኖሎጂ አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማስተካከልና ጠናካራ ጎኖቹን ለማሳየት የተፃፈ ፅሁፍ ነው።

ብሎክቼይን ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ: ተስፋና ስጋቶች

ይህንን ጦማር ለመጻፍ መነሻ የሆነዉ ባሳለፍነዉ ወር  በአዲስ ዘይቤ የዩቲዩብ ቻናል ከአይስ አዲስ (IceAddis) መስራች ማርቆስ ለማና ከአይኮግ ላብ (Icog Labs) አመራር ባልደረባ ቤተልሔም ደሴ ጋር የተደረገው ቃለመጠይቅ ነው።  

በቅድሚያ ይህ ጸሃፊ እነዚህ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ በራስ አነሳሽነት ማኅበረሰቡንና ራሳቸውን ዓለም የደረሰበት ለማድረስ ሚያደርጉት ጥረት ያደንቃል ። በዚህ የወጣትነት ዕድሜያቸዉ በቴክኖሎጂዉ ዘርፍ ማህበረሰብብና ሀገርን ለየሚለዉጡ አርዓያነት ያላቸዉ ተግባራት ለይ መሳተፍ ያስመሰግናል፡፡  

ከላይ የተጠቀሰዉ ዉይይት የብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂ በኢትዮጲያ ያለበትን ደረጃና ስለቴክኖሎሎጂዉ ምንነት ዘርዘር ያሉ መረጃዎን የሰጠ ነበር፡፡  ይሁን አንጂ ፀሀፊዉ በዉይይቱ የተነሱ አንዳንድ ነጥቦች የበለጠ ማብራሪያ የሚፈልጉ ሆኖ አግኝቷቿል፡፡ በመሆኑም ጸሀፊዉ በውይይቱ ላይ የተነሱና ከውይይቱ ውጭ ስለ ብሎክቼይን ቴክኖሎጂ አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማስተካከልና ጠናካራ ጎኖቹን ለማሳየት ይፈልጋል።

የተሳሳቱ አመለካከቶች

ብሎክቸይን አሁን ኢትዮጵያ ካላት መሰረተ-ልማት ( infrastructure ) የላቀ ይፈልጋል!

ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው።

ብሎክቼይን ያልተማከለ የመረጃ ስርጭት ስርዓት ነው። ይህ ማለት እያንዳንዱ ብሎክቼይንን ተጠቃሚ የሆነ ኮምፒዩተር ለስራው የሚያስፈልጉትን መረጃዎችና፣ ፕሮግራሞች ሁሉ ኮፒ አድርጎ ጭኖ ያስቀምጣል። ለምሳሌ አንድ ብሎክቸይን ተክኖሎጂ የሚጠቀም ባንክ ገጠራማ ቅርንጫፍ ቢኖረው ይህ ቅርንጫፍ፣ ዋናው መስሪያ ቤት ያለው መረጃ በሙሉ ኮፒ አለው።

ስለዚህ ከዋና መስሪያ ቤቱ ጋር ያለው የኢንተርኔት ግንኙነት ለአንድ ሰዓት ወይም ለአንድ ቀን ቢቋረጥ፣ ዛሬ በብዙ ባንኮች ውስጥ እንደምናየው ለደምበኞች የሚሰጥ አገልግሎት መቋረጥ አይችልም። ይህ በመንግስት ስራም ሆነ በማንኛውም ድርጅት ስራ ተመሳሳይ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ መረጃዎች በሚመጡበት ጊዜ ወይም ከቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ መረጃው በሚላክበት ጊዜ (update ሲሆን) አዲስ የተቀየሩት እንጂ ሁሉ ነገር እንደ አዲስ ስለማይጫን የሚያስፈልገው የመረጃ ማስተላለፍያ  ስፋት (band width) በጣም ትንሽ ነው። ይህ ልክ በኮምፒዩተር የደህንነት ኮፒ (backup)  ሲደረግ incremental backup የሚባለውን የተቀየረውን መረጃ ብቻ መመዝገብ  ወይም ማስተላለፍ አይነት ስለሆነ ፈጣን የኢንተርኔት ግንኙነትን አይጠይቅም።

መንግስት የብሎክቸይን ቴክኖሎጂን በተግባር ለማዋል ቢወስን፣ የኢትዮጵያ የወረዳ ኔትና ስኩልኔት በሚባል ከ10 አመት በፊት የዘረገቻቸው ኔትዎርኮች ጥቂቱ ክፍል ሙሉ በሙሉ የዚህን ብሎክቼይን ፋልጎት ሊሸፍን ይችላል።

ምንም አይነት የሞባይል ሽፋን የሌላቸውን አካባቢዎች በወር ከብር 2000 ያነሰ የሳተላይት አገልግሎት በማስገባት የትኛውም የገጠር መንደር ውስጥ ያለምንም ችግር አገልግሎት መስጠት ይቻላል።

ይህ ማለት በማንኛውም አዲስ አበባ የሚገኝ የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም ባንክ የሚሰጥን አገልግሎት በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ቀሰስተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት በሚያገኝ ማንኛውም የኢትዮጵያ ገጠር ውስጥ ምንም ጊዜ ሳይጠፋ መስጠት ይቻላል።

ብሎክቸይንን ለመጠቀም ሁሉም ሰው ኮምፒዩተር ወይም ሞባይል ስልክ ያፈልገዋል።

ይህ ስህተት ነው!

በርግጥ ማንኛውም የራሱ ኮምፒዩተር ወይም ስልክ ያለው ሰው ከቤቱ ሆኖ አብዛኛውን አገልግሎት ማግኘት ይችላል። ነገርግን ማባይልም ሆነ ኮምፒዩተር የሌለው ሰው፣ ኮምፒዩተር ወይም ሞባይል ካለው ጓደኛ ወይም ጎረቤት፣ ኢንተርኔት ካፌ፣ በትምህርት ቤት ወይም ቀበሌው ማዕከል በመሄድ ተመሳሳይ አገልግሎት ማግኘት ይችላል።

በየቀበሌው ሁለትና ሶስት ኮምፒዩተሮችን ለነዋሪዎች በማስቀመጥ በማንኛውም ጊዜ ሰው መጥቶ እንዲጠቀም ማድረግ ይቻላል። ኤለክትሪክ ያልተቀጠለበት ቀበሌ ቢሆን እንኳን ከሁለትና ሶስት የሶላር ፓነል በላይ የማይጠይቅ ነው።

ምናልባት ተወያዮቹ ባያነሱትም፣ በብዙ ሰው አስተሳሰብ ስለብሎክቸይን ያለ አመለካከት፣ ብሎክቼይንን ለመጠቀም፣ መጻፍና ማንበብ ማወቅ ያስፈልጋል።

ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው።

ማወቅ ሁል ጊዜም የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋል። የብሎክቼይን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ግን ማንበብና መጻፍም ሆነ ከሚችሉት ቋንቋ ሌላ ማወቅ አያስፈልግም። በስልክ ለማውራት እንግሊዘኛ ማወቅ ወይም ማንበብና መጻፍ እንደማያስፈልገው ሁሉ። የብሎክቼይንን መጠቀም ስልክን ከመጠቀም ያነሰ ዕውቀት የሚፈልግ ነው። ምክንያቱም የብሎክቼይን አገልግሎቶች በመንግስት ወይም በድርጅት የሚሰጡ ስለሆኑ ተጠቃሚውን ከግምት ባስገባ ሁኔታ አገልግሎቶቹን መቅረጽ ስለሚቻል። ስልክ ግን ባለቤቱ ከገዛ በኋላ እንዴት እንደሚሰራ ራሱ ፈልጎ ማወቅ አለበት።

አብዛኛው በመንግስትም ሆነ በሌላ ድርጅት የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ የስራ ሂደት (process) ናቸው። ይህ ማለት መሟላት ያለባቸው ነገሮች ሁሉ በቅደም ተከተል በሚቀመጡ ጥያቄዎችና ለያንዳንዱ ጥያቄ ከሁለት ያልበለጡ አማራጭ መልሶችን በማቅረብ በመልሱ ላይ ተመርኩዞ ውሳኔ ሃሳብ ላይ መድረስ ማለት ነው። ማንኛውም የኮምፒዩተር ፕሮግራም በተመሳሳይ ነው የሚሰራው።

እነዚህን ጥያቄና መልሶች በጽሁፍ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚው በሚገባው ቋንቋ በቃል ማድረግና መልሶቹንም በሚያውቁት ቋንቋ በቀላሉ በቃል ወይም በምልክት (ምልክት እንዲጫኑ በማድረግ) እንዲመልሱ  ማድረግ ይቻላል፡፡

ሌላው ተደጋግሞ የሚሰማ ጥያቄ የብሎክቸይን ተክኖሎጂ አዲስ በመሆኑ ሊታመን ይችላል ወይ? የሚለው ነው።

ለዚህ ጥያቄ በጣም ጥሩ መልስ የሰጡት አሁን በስራ ላይ ያሉት የትምህርት ሚኒስቴር ዶር ጌታሁን መኩሪያ ናቸው። በአንድ ቃለመጠይቅ ላይ “አንድ መሳሪያ ወይም ስርዓት በገንዘብ ከታመነ በሌላ ሁሉም ነገር ይታመናል” ብለው ነበር ያሉት። ይህ በጣም ትልቅና ትክክለኛ አባባል ነው።

የሰው ልጅ ዋጋ ከሚሰጣቸው፣ በጥንቃቄ ከሚጠብቃቸው ነገሮች፣ ገንዘብ በመጀመሪያ ተራ ይቀመጣል። ለዚህ ምክንያቱም ገንዘብ በቀላሉ ሊሰረቅ፣ ሊተላለፍ፣ ቶሎ በጥቅም ላይ ሊውል የሚችል በመሆኑ ለስርቆት ያመቸ ሃብት ነው። አንድ ጆንያ ጤፍ፣ በሬ ወይም፣ መኪና ያለጠባቂ ውጪ ሁለት ሶስት ቀን ማደር ይችላል። ተመሳሳይ የሚያወጣ ብር ግን አምስት ደቂቃ ውጪ ቢቀመጥ ዱካው ሳይታወቅ ይጠፋል። 

ዛሬ የብሎክቸይን ቴክኖሎጂ ከፈረንሳይ ኢኮኖሚ ዝቅ ብሎ ከካናዳ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጣሊያን፣ ከራሺያና ብራዚል ከፍ ብሎ በዓለም 8ኛ ትልቁን ኢኮኖሚ (ሃብት) በማስተዳደር ላይ ነው።  

እነዚህ አገሮች፣ ሃብታቸውን ለመጠበቅ፣ የምድር ጦር፣ የባህር ሃይል፣ የአየር ሃይል፣ አንዳንዶቹም ኒውክለርና፣ የተወሳሰቡ የሕግ ስርዓቶች ሲያስፈልጋቸው፣ ብሎክቼይን ይህንን ህሉ ሃብት ሳይጠፋ፣ ሳይሰረቅ፣ ጉልበተኞችና አምባገነኖች ልንጠቅ ሲሉ ሳይሸነፍ የሚያስተዳደረው ኮምፒዩተር ላይ በተጻፉ ኮዶች ብቻ ነው። ለዚህ ነው በብሎክቼይን ዓለም “ኮድ ሕግ ነው” የሚባለው።

በብሎክቼይን ላይ የእገሌ ተብሎ የተመዘገበን፣ ቤትም፣ ሆነ መኪና፣ ገንዘብም ሆነ ስዕል፣ ሙዚቃም ሆነ ሃሳብ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ካልሆነ ማንም ጉለበተኛ ሊነጥቅ አይችልም። ድምጽም ቢሆን እንዲሁ። ብሎክቼይን ላይ መታወቂያ ያለውን ሰው ማስመሰል አይቻልም፣ ወይም ሰውዬው ሌላ ሰው ነኝ ቢል ኮዱ አይፈቅድለትም። ጉልበተኛ አቅሙን የሚሞክረው እውነቱን የመቀየር እድል ካለው ነው። የብሎክቼይን ቴክኖሎጂ አዲስ አይደለም።

በውስጡ ያሉት የተለያዩ አስተሳሰቦችና፣ ቴክኖሎጂዎች ዘመናዊ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ አስተሳሰብ ከተፈጠረ ከ18 መቶዎቹ አመታት ጀመሮ የነበረ፣ ከዛም ቀደም ብሎ ከዛሬ 2000 ሺህ ዓመት ባቢሎናውያን ከጀመሩት የመዝገብ አያይዝ ጀመሮ በስራ ላይ የዋለ፣ የተፈተሸና ውጤታማነቱ የታየ ነው።

ብሎክቼይን ያደረገው እነዚህን የተለያዩ፣ የተፈተኑ ቀደም ሲል በተለያየ ክፍል ተቀምጠው ሰው በመሃል ሆኖ እያገናኘ የሚያሰራቸውን ቴክኖሎጂዎች፣ አንድ ላይ ሆነው እየተናበቡ፣ በመሃል ሆኖ ከሚያሳልጣቸው ሰው በተሻለ ጥራትና፣ ፍጥነት እንዲሰሩ ነው።

ሰው አውቆም ይሁን ሳያውቅ የሚሰራቸው ስህተቶች/ጥፋቶች ስለሚኖሩ፣ ያንን የሚዳኙ ሕጎችም፣፣ የጦርመሳሪያዎች፣ መርከቦችና አውሮፕላኖች ያስፈልጋሉ። ብሎክቼይን ግን ይህ አያስፈልገውም። ሕጎቹ ሁሉ በኮዱ ላይ የተጻፉ ስለሆነ፣ በሰከንዶች ውስጥ ስህተቶች ሳይሰሩ ይፈጸማል። ስለዚህ በሙግት፣ በክስ፣ በሙስና፣ ለደላላ የሚባክን ገንዘብና ጊዜ አይኖርም።

ብሎክቼይን የተወሳሰበ አሰራር ወይም አስተሳሰብም አይደለም። ያልተማከለ፣ ስርዓቱን  ጠብቆ የሚሻሻል፣ ሊሰረዝ ሊደለዝ የማይችል የመዝገብ አያያዝ ነው።

 በኢትዮጵያ በትምህርት ሚኒስቴር እየተሞከረ ያለው ብሎክቼይን

የመጀመሪያ ዝርያ ብሎክቼይን የሚባሉት ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰው ባህሪ ሁሉ ቢኖራቸውም፣ ብዙ ሕዝብን በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ችግር ነበረባቸው።  የመጀመሪያው ዝርያ ብሎክቼይኖች ሊያስተናግዱ የሚችሉት በሰከንድ ከ3 እስከ 7 ደምበኛ ብቻ ነበር። ተጠቃሚው እየበዛ ሲሄድ አገልግሎት ለማግኘት የሚፈጀው ጊዜ እስከ 15 ደቂቃ ይፈጅ ነበር። ብዙ ተጠቃሚ በመጣ ቁጥር አገልግሎት የማግኘት ጊዜ እያሻቀበ ይሄዳል። በዚህ ረገድ ባለፉት 10 ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ምርምርና ጥናት በመደረጉ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የገባውና በትምህርት ሚኒስቴር ስራ ላይ የዋለው ካርዳኖ የሚባለው ብሎክቼይን እስከ 1 ሚሊዮን ደመበኞችን በሰከንድ ማስተናገድ ይችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከሱ እንደቀደሙት ብዙ ሰው በገባ ቁጥር ፍጥነቱ ከመቀነስ ይልቅ ይጨምራል። 

ይህ ትምህርት ሚኒስቴር በስራ ላይ ያዋለው ብሎክቼይን ከሌሎቹ የሚለይበትም ሌላም ነገር አለው። ይኸውም የተሰራው በኮምፒዩተር ሳይንስ High Assurance Software Development በሚባል ዘዴ ነው። ቢሰበሩ፣ ቢበላሹ ብዙም ኪሳራ የማያመጡ እንደ የኮሞፑተር ጨዋታ (gaming) ፣ የጽሁፍ ማቀናበሪያ(word processing)፣ የዌብ አሰሳ(web browsing) የመሳሰሉ መሳሪያዎች የሚጻፉባቸው ፕሮግራሞች አስራር ብዙም ጥንቃቄ አይጠይቁም። ከተበላሸ መልሶ ማስነሳት ይቻላል።

ነገርግን የኒውክለር ጦር መሳሪያ፣ ወይም ሃይል ማመንጫን፣ የአውሮፕላን ማብረሪያ፣ የመንኮራኩር መላኪያ፣ ከፍተኛ የገንዘብ ድርጅቶችን፣ ባንኮችን፣ የመከላከያና ደህንነት ጉዳዮችን፣ የአገር ከፍተኛ ሚስጢሮችን፣ ሕክምና...ወዘተ የመሳሰሉ ስራዎችን የሚሰሩ ፕሮግራሞች አንድ ስህተት ቢሰሩ የሚደርሰው ጥፋት በገንዘብ የሚተመን አይደለም። ስለዚህ እነዚህ የስራ ሂደቶች የሚከወኑባቸው ፕሮግራሞች የሚሰሩት ከላይ የተጠቀሰው High Assurance Software Development በሚባለው ዘዴ ነው። 

የካርዳኖ ብሎክቼይን የተጻፈው ይህ የኒውከለር የጦር መሳሪያዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ጥቅም ላይ በዋለ የኮምፒዩተር  አሰራር ስርዓት ነው። በዚህ ምክንያት ነው የSingualritynet አረተፊሻል ኢንተለጀንስ ከሌሎች ተመሳሳይ ቀደም ሲል ከነበሩ ብሎክቸይኖች ወደ ካርዳኖ ለመሸጋገር የወሰኑት።

የወደፊት ስጋት!!

ከኮምፒዩተር ደህንነት ጋር በተያያዘ እንደ አሜሪካና ቻይና አይነት ተቀናቃኝ ሃያላን አገሮችን ከፍተኛ ስጋት ላይ የከተተ፣ መፍትሄ ለማግኘት እየተሯሯጡ ያሉበትና የሚፈራው  የኳንተም ኮምፒዩተር በስራ ላይ መዋል ነው። የኳንተም ኮምፒዩተር  ምን እንደሆነ ለማወቅ ማስፈንጠሪያውን ይከተሉ። 

አገሮች ኮምፒዩተር መጠቀም ከጀመሩ ጊዜ ወዲህ ያላቸውን መረጃ ሁሉ በዲጂታል መልክ ነው የሚያስቀምጡት። ይህ ዲጂታል መረጃ በክሪፕቶግራፊ ተቆልፎ ስለሚቀመጥ መረጃው ቢሰረቅም፣ ኮፒ ቢደረግም በቀላሉ ምን እንደሆነ ማወቅ አይቻልም።

አሁን በአለም ላይ አለ የሚባል ኮምፒዩተርን ተጠቅሞ የአንድ ክሪፕቶራፊ ቁልፍን ለመስበር የሚፈጀው ጊዜ እንደ ቀማሪዎቹ 27 trillion trillion trillion trillion trillion ዓመታት ነው። ለማሰብ እንኳን አስቸጋሪ የሆነ ቁጥር ነው። ለማነጻጸር ግን የዩኒቨርስ እድሜ 15 ቢሊዮን ዓመት ብቻ ነው።

አንድ ኳንተም ኮምፒዩተር ግን እነዚህን ቁልፎች በ6 ወር ውስጥ ይሰብራል። ይህ ማለት የአገሮች የጦር፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ሚስጢሮች ሁሉ ሊወጣ፣  ከፍተኛ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል።

ይህ አይነት ችግር ስጋት የሌለው የኮምፒዩተር ስርዓት ብሎክቼይን ነው።  ለዚህ ምክንያቱም ብሎክቼይን በስራ ላይ መዋል የተጀመረው የኳንተም ኮምፒዩተር ስጋት ከታወቀ በኋላ በመሆኑ ይህንን ስጋት ለማስወገድ የሚችል ሁኔታን እሳቤ ውስጥ በማስገባት የታቀደ በመሆኑ ነው። አንድን ቤት ሲገነቡት በትክክል ካልተሰራ ከተገነባ በኋላ ከማስተካከል  አንዳንዴ አፍርሶ አዲስ መስራት አዋጭ ይሆናል። ቤቱ ውስጥ ግን ብዙ ስራ እየተሰራበት ከሆነ አፍርሶ መስራቱ አስቸጋሪ ይሆናልና፣ ከተበላሸው ቤት ጋር ለመኖር ሰው ይገደዳል። ዛሬ አብዛኛዎቹ ያደጉ አገሮች ችግር ይሄ ነው።

ሌላው የክሪፕቶግራፊክ ቁልፍ አቆላላፉ ላይ ነው። አሁን ባለው የኮምፒዩተር መረጃ አቀማመጥ ስርዓት፣ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ መረጃዎች   አንድ ላይ ሆነው በአንድ ቁልፍ ተቆልፈው ነው የሚቀመጡት። ይህ ማለት ይህንን ሁሉ መረጃ ለመስረቅ የአንድ ኮምፒዩተር ስርዓትን ቁልፍ መስበር ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ብሎክቼይን ግን እያንድንዱን መረጃ በራሱ ቁልፍ ተቆልፎ ነው የሚቀምጠው። የቁልፉ ባለቤት ካልሆነ ማንም ልከፍተው አይችልም።

የኳንተም ኮምፒዩተር ቢመጣ ከአንድ ቢሊዮን መረጃዎች አንዱን በስድስት ወር ሊሰብር ይቻላል። የተሰበረው ምናልባት የገበያ ማስታወሻ የግሮሰሪ ሊስት ብቻ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ብሎክቼይን ውስጥ የተቀመጠን መረጃ ቁልፍ ለመስበር ማሰብ አዋጪ አይደለም።

ታዲያ ይህ ከሆነ ያደጉት አገሮች መረጃዎቻቸውን ለምን በብሎክቸይን አያስቀምጡም?

ብዙዎቹ አገሮች ማሰብ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማፍሰስ ምርምር እያደረጉ ነው። ነገግን  እንደ ኢትዮጵያ ወይም ሌላ ደሃ የአፍሪካ አገር ቀላል አይሆንላቸውም።

ምክንያቱም አሁን ያላቸው ስርዓት ሙሉ በሙሉ በኮምፒዩተር ላይ የሚሰራ በመሆኑ፣ ይህንን ሁሉ ስርዓት ወደ ብሎክቼይን ለመቀየር ሃያ ሰላሳ ዓመት ሊፈጅባቸው ይችላል። ለዓመታት ያጠራቀሙት አሰስ ጎሰስ በቀላሉ ወደ አዲሱ ስርዓት እንዲሄዱ አይፈቅድላቸውም። አሮጌ ቤትን ከማደስ አዲስ መስራት ይቀላል።

ኢትዮጵያና ብሎክቼይን!

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር በወረቀት ባለበት ወይም ጭራሽ ምንም ስርዓት የሌለበት አገር ዛሬውኑ፣ያለውን መረጃ በዘምቢል ይዞ ገብቶ፣ ዘመናዊ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣን ስርዓት መገንባት ይቻላል። ለዚህ ጊዜ እንኳን ቢሆን ኋላ ቀርነታችን ጠቅሞናል። ለመጠቀም ከደፈርን።

ይህ ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአገር እድገት ላይ ያላቸውን አቅምና፣ እውቀት ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ ያስችላል። ብድር ከመለመን የብሎክቼይን ቴክኖሎጂ እንዴት በቀላሉ ኢንቨስትመነትን እንደሚያመቻች በሌላ ጊዜ የምንመልስበት ይሆናል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በአገር ውስጥ ባለፈው 30 ዓመት በተገነባው ኢፍትሃዊ ስርዓትና የውጪ ጠላቶች በሚያደርጉት ጫና በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነው ያለችው።

ይህ ቀን ያልፋል ብለን ሁላችንም ተስፋ ብናደርግም መቼ ሊያልፍ እንደሚችል ግን ርግጠኛ መሆን አንችልም። ጠላቶቻችን በዚህ በኩል ስንደፍን በዚህ በኩል እየቆፈሩ እንቅልፍ አሳጥተውናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምናልባትም ለሁሉም ግልጽ እየሆነ የመጣው የአገራችንን ኋላ ቀር የሆነ የመረጃ አያያዝና አሰረጫጨት ክፍተትን በመጠቀም የተደረገውን በማጋነን ያልተደረገውን ፈጥረው ከፍተኛ የስነልቦናና፣ ከዚህም ባለፈ አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ጥቃት እየሰነዘሩ ነው።

ከዚህ ችግር አገራችን ትወጣ ዘንድ ሊረዳ የሚችል በቀላሉ በተግባር ላይ ልናውለው የምንችለው መሳሪያም ሆነ ስርዓት ብሎክቼይን ነው።

ስለዚህ በዚህ በኩል መንግስት፣ ምሁራን፣ ድርጅቶች፣ በአጠቃላይ ህዝቡ የቴክኖሎጂውን ትሩፋቶች በመረዳት በተግባር ላይ ለማዋል መሞኮር ያስፈልጋል።

አስተያየት