ሰኔ 9 ፣ 2013

ዲጅታል ማህደር የተሰኘ ኦን ላይን የመረጃ ቋት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ቴክ

የግለሰብም ሆነ የድርጅቶችን መረጃዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለረዥም ጊዜ ለማስቀመጥ የሚያስችል 'ዲጂታል ማህደር' የተሰኘ ኦን ላይን የመረጃ ማስቀመጫ ቋት ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት ጀመረ

 ዲጅታል ማህደር የተሰኘ ኦን ላይን የመረጃ ቋት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የግለሰብም ሆነ የድርጅቶችን መረጃዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለረዥም ጊዜ ለማስቀመጥ የሚያስችል 'ዲጂታል ማህደር' የተሰኘ ኦን ላይን የመረጃ ማስቀመጫ ቋት ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

የአስኳላ ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር በተባለ ተቋም የሚተዳደረው ድረ ገጽ በወረቀት ያሉ ማናቸዉንም ሰነዶች ስካን በማድረግ መረጃዎችን ለማስቀመጥ አንደሚያገለግል የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ፋንቱ ነግረውናል፡፡ “አገልግሎቱ በወረቀት እና በሌሎችም ጊዜያዊ የመረጃ ማከማቻዎች ተዘበራርቀው የተቀመጡ መረጃዎችን ስርአት ከማስያዙ በተጨማሪ ‘ጠፋብኝ’ የሚል ስጋትን ያስወግዳል” የሚሉት የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ  በማይክሮሶፍት ወርድ ፒዲኤፍ፣ በምስል፣ በድምጽ፣ በቪድዮ እና በመሳሰሉት የተዘጋጁ መረጃዎችን ለወደፊት የማካተት እቅድ መኖሩንም አክለዋል።  

ማንኛውም 'ስካን' የተደረገ የግለሰብ፣ የድርጅት እንዲሁም ሀገራዊ ሰነድ ያስቀመጠው አካል ብቻ የሚጠቀምበት እንደ ማህደር እንደሚያገለግለው የተነገረለት ይህ ድረገጽ ወደ ስራ ከገባ ወደ ሁለት ወር ገደማ ሲሆን በቅርቡ የሞባይል መተግበሪያ ተዘጋጂቶለት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡

አገልግሎቱ ክላዉድ ስቶሬጅ ከሚባሉት ከሚባለዉ ቴክኖሎጂ ጋር ተመሳሳይነት አለው የሚሉት ሀላፊው ከሌሎች መተግበሪያዎች የሚለየው ለአጠቃቀም አመቺ እና ቀላል በመሆኑ ነው ይላሉ። እንዲሁም ሰነዱን ለሌሎች ሰዎች ለማጋራት (ሼር) እና ማሻሻያ (አፕዴት) ለማድረግ አመቺ መሆኑንም አክለዋል።

የዲጂታል ማህደር 'ሰርቨር'  አገልግሎቱን በጥረት አንዲሰጥ ተደርጎ የተሰናዳና ደረጃዉን የጠበቀ ሲሆን ሰርቨሩ በሀገረ አሜሪካ አንደሚገኝ ተገልጧል። እንዲሁም የተሰራበት የኮምፒዩተር ፕሮግራም(ሶፍት ዌር) ደህንነቱ መቶ በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ ነው የተነገረው። 

ተጠቃሚዎች ድረ ገጹን ለ14 ቀናት ያለ ምንም ክፍያ ከተጠቀሙ በኋላ አገልግሎቱን በቋሚነት ለማግኘት 5ሺህ 700 ብር ዓመታዊ የአገልግሎት ክፍያ መክፈል አንደሚጠበቀባቸዉም ከድርጅቱ ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጲያዊያ ባለሙያዎች በልጽገዉ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ተመሳሳይ የመረጃ ማጠራቀሚያ ቋቶች መኖራቸዉ የሚታወቅ ሲሆን ስለቴክኖሎጂዉ ያለዉ ግንዛቤ አናሳ መሆንና የቴሌኮም የመሰረተ ልማቶች በሚገባዉ ደረጃ አለመዘመን ለስራቸዉ አንቅፋት እየፈጠረባቸዉ አንደነበር አዲስ ዘይቤ ታዝባለች፡፡

ዲጂታል የመረጃ ቋት መረጃዎችን በቋሚነት ለማስቀመጥ ከማገዙም ባሻገር የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማዘመን ተጨማሪ አማራጭ ተደርጎ አንደሚወሰድ የሚያስረዱት የዘርፉ ባለሙያዎች አንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ለተለያዩ የደህንነት ስጋቶች የተጋለጡ በመሆኑ ክፍተኛ የጥንቃቄና የደህንነት ጥበቃ አንደሚፈልጉ ይናገራሉ፡፡  

በዓለም ላይ አንደ ጉግል ድራቭ፥ ድሮፕ ቦክስ፥ አይ ክላዉድ የመሳሰሉ የክላዉድ ስቶሬጅ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁ ድረ ገጾች መኖራቸዉ ይታወቃል፡፡

አስተያየት