ሰኔ 7 ፣ 2013

የወረቀት ዋጋ መናር የፈተናቸው የሕትመት መገናኛ ብዙኃን

ሚዲያ ወቅታዊ ጉዳዮች

አዲስ ዘይቤ የተለያዩ የሕትመት መገናኛ ብዙኃንን አነጋግራለች።

የወረቀት ዋጋ መናር የፈተናቸው የሕትመት መገናኛ ብዙኃን

ለጋዜጣና መጽሔት ሕትመት የሚጠቀሙት ወረቀት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመጠን በላይ እየጨመረ መምጣት በስራቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠርባቸዉ እንደሚገኝና ከገበያ ውጭ ሊያደርጋቸዉ እንድሚችል አስተያየታችውን ለአዲስ ዘይቤ የሰጡ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። 

የቁምነገር መጽሄት ዋና አዘጋጅ ታምራት ኃይሉ ሳምንታዊ የመጽሄት ሕትመት በወረቀት ዋጋ ሳቢያ ማቆማቸውን ይናገራሉ። ''ማስታወቂያ ስናገኝ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ሕትመት አቁመን ወደ ዲጂታል ጽሑፍ ገብተናል'' ያሉን ዋና አዘጋጁ ለስራቸው እንቅፋት ሆኖ ከገበያው ያስወጣቸውን ምክንያት የዶላር ምንዛሬ እጥረት፣ በወረቀት ላይ የሚጣለው ቀረጥ፣ የኅብረተሰቡ የንባብ ባህል መቀነስ እና በኮቪድ ምክንያት ሰው የወረቀት ንክኪ ማድረግ ባለመፈለጉ መሆኑን ይገልጻሉ።

አዘጋጁ እንደሚናገሩት ለሕትመት ሲያቀርቡ የነበረው የመጽሔት ብዛት የሚወስኑት አዟሪዎች እንሸጣለን ብለው በገመቱት መጠን ልክ እንደነበር እና መጠኑ በቀነሰ ቁጥር ለህትመት የሚወጣው ገንዘብ እንደሚጨምር ይገልጻሉ። በሳምንት 4ሺህ እስከ 5ሺህ ለሽያጭ ይቀርብ እንደነበር እና የ1 መጽሔት ዋጋ 15 መሆኑን ዋና አዘጋጁ ይናገራሉ።

ለሕትመት የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ የታምራት ኃይሉን ሀሳብ የሚጋሩት የጊዮን መጽሔት ዋና አዘጋጅ እና የኢትዮ ሀበሻ ጋዜጣ  ፍቃዱ ማህተመወርቅ ''በወረቀት ዋጋ መወደድ ምክንያት አሁን እየተሸጠበት ካለው 20ብር ላይ ጭማሪ እናደርጋለን ብለን እንገምታለን'' ይላሉ። በዋጋው የግል ሕትመት መገናኛ ብዙኃን የበለጠ ተጎጂ እንደሆኑ ይገልጻሉ። በተመሳሳይ ለአንድ መጽሔት 20 ብር የሽያጭ ዋጋ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ጭማሪ እንደሚደረግ ዮናታን ዮሴፍ (ዶ/ር) የመርፌ መጽሔት ባለቤት ይናገራሉ።

በ1 መጽሔት ሕትመት ላይ የ4 ብር ጭማሪ ማለትም ከ10 ወደ 14ብር ማደጉን የሚናገሩት የመጽሔቱ ባለቤት ይህም ለመገናኛ ብዙኃኑም ሆነ ለአንባቢው ተጸእኖ መፍጠሩን ይገልጻሉ። እንደ መፍትሄ ያስቀመጡት ለሕትመት መገናኛ ብዙኃን ወረቀት ላይ ያለው ቀረጥ ቢነሳ እና በአነስተኛ ዋጋ ለማስተም የመንግሥት ማተሚያ ቤት አገልግሎት ቢሰጡ የሚል ነው።

የሐበሻ ወግ ኤዲተር ቴዎድሮስ ካሳ በበኩላቸው የሕትመት ዋጋ 8ብር ከ50 ሳንቲም የነበረው ወደ 13 ብር ከፍ ማለቱን ጠቅሰው ሽያጩም ከ15 ወደ 20 ማደጉን ተናግረዋል። ይህም ''ትውልዱ እንዳያነብ የሚያደርግ ነው'' የሚሉት ኤዲተሩ መንግሥት ድጎማ ቢያደርግ እና ቀርጥ ላይ ቅነሳ ቢደረግ በማለት እንደመፍትሄ ያስቀምጣሉ። ''ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ሲመረቁ መንግሥት ማበረታቻ ለማድረግ ከቀረጥ ነጻ የሚያደርግላቸው ሁኔታዎች አሉ'' የሚሉት ኤዲተሩ የህትመት መገናኛ ብዙኃን ካለው ሀገራዊ አስተዋጽኦ አንጻር ድጋፍ አለመደረጉ ቅሬታ ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራሉ።

መጽሔት ለሕትመት ሲገባ 15 ከመቶ እና ለሽያጭ ሲቀርብ 15 ቀረጥ መጣሉን የሚናገሩት ኤዲተሩ አንባቢው ላይ ጫና እንደፈጠረ ይገልጻሉ። ለዚህም እንደማሳያ የጠቀሱት የመጽሔቱ አንባቢ ቁጥር ከ8 ወይም 9 ሺህ ወደ 3 እና 2 ሺህ መቀነሱን ነው።   

በቴዎድሮስ ካሳ ሀሳብ ጋር የማይስማሙት እንዳለ መኮንን የኢኤምጂ ሕትመት እና ማስታወቂያ ባለቤት ሲሆኑ ''የሕትመት ዋጋ የጨመረው ሚታተመው ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ ነው። መፍትሄው ደግሞ አንባቢ የሚፈልገው ዓይነት ጽሑፍ በመጻፍ ቁጥሩን በማብዛት ሕትመቱን መጨመር ነው'' ይላሉ። አክለውም መጽሔት እና ጋዜጣ ሲያትሙ ብዙ ትርፍ እንደማያገኙበት የተቋሙ ጥቅም ''በኢኤምጂ የታተመ'' ተብሎ በመጽሔቶቹ ላይ የሚወጣው ጽሑፍ ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም ህትመት ከሚደረግበት ዋጋ ላይ የ2 ብር ጭማሪ መድረጋቸውን የሚገልጹት አቶ እንዳለ ምክንያታቸው ከ1ወር ገደማ በፊት የቀለም፣ ወረቀት እና ፕሌት ዋጋ ጭማሪ መሆኑን ይናገራሉ። ይህም 1ፕሌት (ገጽ) ከ120 ወደ 160 ብር፣ 500 ወረቀት ከ1,100 ወደ 1,350 ብር እና የቀለም ዋጋ ከ800 ወደ 1,200 ብር ከፍ ማለቱን በማብራራት ነው። የሕትመት እና ማስታወቂያው ተቋም ባለቤት ለህትመት የሚያገለግሉት ቁሳቁሶች ጭማሪ በዶላር ምንዛሬ እጥረት እና ከዚህ ቀደም ቁሳቁሶቹ ሲገቡ በዲያስፖራ አካውንት ይደረግ የነበረው አሰራር በመቀየሩ ሳቢያ መሆኑን ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ነገር ግን እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ የመጽሔቶቹ እና ጋዜጦች መሸጫ ዋጋ ከፍተኛ የሚባል አይደለም ''ጥሩ ጽሑፍ ከሆነ ይገዛል'' ሀሳብ አላቸው።ወረቀት ወደ ኢትዮጵያ የሚገባበት ዋጋ፣ የሚጣልበት ቀረጥ፣ ለሕትመት ሲገባ እና ለሽያጭ ሲቀርብ ገዢው ላይ የሚጣለው የቀረጥ ዋጋ እንዲሁም ከሕትመት መገናኛ ብዙኃን የሚነሳውን ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት ለጉምሩክ ኮሚሽን በተደጋጋሚ በስልክ፣ በደብዳቤ እና በአካል ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። 

አስተያየት