ሰኔ 7 ፣ 2013

የመንገድ መሰረተ ልማቶች የጥራት ችግር

City: Jigjigaዜናዎች

በሶማሌ ክልል የተዘረጉት የመንገድ መሰረተ ልማቶች የጥራት ችግር እንዳለባቸው በፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለአዲሰ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የመንገድ መሰረተ ልማቶች የጥራት ችግር

በሶማሌ ክልል የተዘረጉት የመንገድ መሰረተ ልማቶች የጥራት ችግር እንዳለባቸው በፍሳሽ ማስወገጃ ተቦዎች አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለአዲሰ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡ የጅግጅጋ ሪፖርተራችን ያነጋገረራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በዘፈቀደ የሚጣል ቆሻሻ የጎርፍ ማስወገጃዎችን አበላሽቷቸዋል፡፡

ሪፖርተራችን የተንቀሳቀሰባቸው አንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች መንገዶች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ባለመገንጋታቸው ባለመሰራታቸው ጎርፍና ቆሻሻ በመኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ ተመልክቷል፡፡

በአካባቢዉ የሚገኙ ነዋሪዎችም የመንገድ መሰረተ ልማቶች መዘርጋታቸዉ መልካም ሆኖ ሳለ በሚገነቡበት ወቅት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ስለማይሰራ ዓመት ሳይሞላ እየፈራረሰና መኖርያ አካባቢዎችን ቆሻሻ እያበላሸ መሆኑን ነግረውናል፡፡

ሀሰን አህመድ ሀሰን የጅግጅጋ ከተማ ነዎሪ ናቸው "ለፍሳሽ መውረጃ ተብለዉ የተገነቡ ቦዮች ጠባብና የሚመጣውን ጎርፍ ማሳለፍ ስለማይችሉ የእንስሳት ተረፈ ምርቶችን ጨምሮ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ቆሻሻዎች አካባቢያችንን እየበከለ ለጤና ችግር እየዳረገን ነዉ።"  ይላሉ፡፡

መሰረተ ልማቶች በሚገነቡበት ወቅት የታለመላቸውን ጊዜ ለማገልገል እንዲችሉ በተገቢው ጥራት ለትውልድ እንዲተላለፉ ተደርገዉ በከፍጠኛ ጥንቃቄ መገንባት ሲገባቸዉ በጅግጅጋ ከተማ የሚሰሩ አብዛኛዎቹ የውስጥ ለውስጥ ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍና ዋና አስፋልት መንገዶች ላይ ዕየታየ ያለዉ ብልሽት በእጅጉ እንዳሳዘናቸውም የተናገሩት ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወ/ሮ ዩሰራ አሊ ናቸዉ፡፡

"በግንባታ ወቅትም አስተያየት ስንሰጥ ተቀብሎ ከማስተካከል ይልቅ ያልተፈለገ ቁጣ ደርሶብን ያውቃል" የሚሉት ወይዘሮ ዩስራ የተሰራዉ መንገድ ገና በክረምቱ መግቢያ ላይ እንደዚህ በመሆኑ ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠረባቸዉና የሚመለከተው አካል ፈጣን መፍትሄ እንዲያመቻችላቸዉም ጠይቀዋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የመሰረተ ልማት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ኢብራህም አሊ በከተማዉ የሚገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ሕጋዊ የጨረታ ሂደትን ተከትለው የሚፈፀሙ ቢሆንም በግንባታዎች ጥራት ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡

ግንባታዎች በሚካሄዱበት ወቅት በዲዛይኑ መሰረት በባለሙያዎች ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግ ሲሆን አብዛኛዎቹ ግንባታዎች በጨረታ ሂደትና ምክንያት እየተጓተቱ ምቹ ባልሆነ ወቅት መሰራታቸዉ ለግንባታዎች ጥራት መጓደል ዋነኛዉ ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ኢብራሂም ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ የሚተዩ ችግሮች ደግሞ ለማፋሰሻ ቦዮች መዘጋት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ አመላክተዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የሚዘጉ የማፋሰሻ ቦዮችን ለማስጠረግ ከ7 መቶ ሺህ ብር በላይ በጀት መያዙን የገለፁት ባለሙያዉ ሕብረተሰቡም ቆሻሻን በቦዮች ውስጥ ከመጣል ተቆጥቦ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

አስተያየት