መስከረም 22 ፣ 2015

የማይታየው የኢትዮጵያ ሲኒማ ሸክም

City: Addis Ababaኪነ-ጥበብወቅታዊ ጉዳዮች

የፊልም ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከወረርሽኙ በኋላ የፊልም ዘርፉ የስራ ውጤቶቹን ለማቅረብ ከሲኒማ ወደ ዩቲዩብ እና የኢንተርኔት መንገዶች ፊቱን አዙሯል

Avatar: Kalayou Hagose
ኻልኣዩ ሓጎሰ

ኻልኣዩ ሓጎሰ የህግ ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን ይፅፋል። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የማይታየው የኢትዮጵያ ሲኒማ ሸክም

የሲኒማ ጥበብ ወደ ኢትዮጵያ የተዋወቀው የመጀመሪያው አለም አቀፍ ፊልም እ.አ.አ በ1895 በፓሪስ ለዕይታ ከበቃ ከሁለት አመት በኋላ እ.አ.አ በ1897 ነበር። የመጀመሪያው ሲኒማ ቤትም እ.አ.አ በ1923 በአዲስ አበባ መገንባት ችሏል። በስክሪን ላይ በሚታየው አስገራሚ ተንቀሳቃሽ ምስል የተገረሙም ቤቱን “ሰይጣን ቤት” ብለው ሊሰይሙት ችለዋል። 

በኢትዮጵያ ፊልም ዕድገት ታሪክ ተጠቃሽ ከሆነውና በሚሼል ፓፓታኪስ እ.አ.አ በ1975 ከተሰራው የመጀመሪያው ባለቀለም ፊልም ጉማ አንስቶ የኢትዮጵያ ሲኒማ በተለያዩ የመንግስታት፣ ባህልና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች አልፎ ዛሬ ያለበት ደርሷል። ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ኢንደስትሪው ባደረገው ጉዞ በ1990 ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ላይ አይነተኛ መነቃቃት አሳይቶ እንደነበር ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። 

የኢትዮጵያ ሲኒማ ለአለም አቀፍ እይታና ተደራሽነት ለመብቃት ረዥም መንገድ እንደሚቀረው ብዙዎች ቢስማሙበትም ከቅርብ አመታት ወዲህ ያለው ጉዞ ግን የኮቪድ ወረርሽኝና ሌሎች ገፊ ምክንያቶች አንፃር በቁቁለት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ በመጥቀስ ፈጣን የማሻሻያ እርምጃዎች ሊደረግበት እንደሚገባ አብዛኛዎቹ ባለድርሻ አካላት ይጠቁማሉ።  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ያሳረፈው ጫና

ኮሮና ቫይረስ በአለም ከታዩ እጅግ አስደንጋጭ ከሆኑ ክስተቶች አንዱ ሲሆን፣ በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የሙያ ዘርፎችና እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጉዳት ሊያደርስ ችሏል። ወረርሽኙ ለመዝናኛ ኢንደስትሪው ሌላ እድል ከፍቷል የሚሉ ክርክሮች ቢነሱም እንደ ኢትዮጵያ ሲኒማ አይነት ገና በማደግ ላይ ያሉ የመዝናኛና የስነ ጥበብ ዘርፎች የኮሮና ተፅዕኖ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ታይቷል። 

በኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሌሎች ሃገራት እንደተደረገው ሰዎች መሰብሰብ እንደማይችሉ እና ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች እንዳይገኙ መንግስት በአዋጅ የከለከለ ሲሆን በዚህም ፊልም አፍቃሪያን በሲኒማ ቤቶች ተሰብስበው ፊልም የሚያዩበት እድል በይፋ ታገደ። 

በመሆኑም በፊልም ኢንዱስትሪው የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከወረርሽኙ በኋላ የፊልም ዘርፉ የስራ ውጤቶቹን ለማቅረብ ከሲኒማ ወደ ዩቲዩብ እና የኢንተርኔት መንገዶች ፊቱን አዙሯል። ይህም የዲጅታል ሚድያው አትራፊና ገንዘብ ማጋበስ የሚቻልበት መድረክ እንደሆነ ፊልም ሰሪዎች እንዲመለከቱ አደረገ። 

ታደሰ አያለ (ስሙ የተቀየረ) የፊልም ባለሙያና በሚዲያ ስራዎች የተሰማራ ባለሙያ ሲሆን “የወረርሽኙ መከሰት የሲኒማ ፊልም እንዲጠፋ፣ ፊልሞች በዩቲዩብ ቻናሎች እንዲጫኑና ወደ ቴሌቪዥን እንዲመጡ አድርጓል” ይላል።

ይህንን በማድረግ ቀዳሚ ስፍራ የሚይዘው የዩቲዩብ ቻናሉ ሶደሬ ቲዩብ እንደሆነ የሚናገረው ባለሙያ እንደሚያስረዳው እንደ ሶደሬ አይነት የፊልም አሰራጮች የኦንላይን ግብይት ለማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ የክፍያ መንገዶች ማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆን በመገንዘብ የሃገር ውስጥ ተመልካቾች እንደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሞባይል ክፍያ አይነት በቅርባቸው ሊያገኟቸው በሚችሏቸው መንገዶች ከሲስተሙ ጋር የማቀናጀት መንገድ እስከመዘየድ ደርሰዋል።  

ይህም በወረርሽኙ ቤታቸው የተቀመጡ ሰዎች በበይነ መረብ የሚቀርቡትን የአማርኛ ፊልሞች ከወረርሽኙ በፊት ባልተለመደ መልኩ በቀላሉ ክፍያ ፈጽመው በፈለጉት ጊዜና ቦታ እንዲመለከቱ አስችሏል። 

በዚህ ረገድ ሌላው ተጠቃሽ የሆነው የEBS ቴሌቪዥን ጣቢያ ተመልካቾች ባሉበት ሆነው የአማርኛ ፊልሞችን የመመልከት የጊዜውን ከፍተኛ ፍላጎት በመረዳት ከዋናው ጣቢያ የተለየ ራሱን የቻለ የፊልም ቻናል (EBS Cinema)ን ከፍቷል። በተጨማሪም ሙሉ በሙሉ የውጭ የስነ ጥበብ ስራዎችን ያቀርብ የነበረው Dstv ከጊዜው ፍላጎት ጋር ራሱን ለማራመድ የአማርኛ ፊልምና ሙዚቃዎችን የሚያቀርብበት የተለየ ቻናል በመክፈት ሶደሬ ቱዩብ እና ebs ሲኒማን ሊከተል ችሏል። እነዚህን እንደ ጉልህ የኢንዱስትሪው አዲስ  ለውጦች ቢጠቀሱም እንደ CANAL+ አይነትና በተመሳሳይ መንገድ መጓዝ የቀጠሉ ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል።

በዚህ ለውጥ ላይ ታደሰ አስተያየቱን ሲሰጥ “የኮሮና ወረርሽኝን ተከትለው የመጡት እነዚህ አዲስ ለውጦች የፊልም ኢንዱስትሪው ለረዥም ጊዜ ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የሲኒማ እንዲሁም የሲዲና ዲቪዲ መንገዶችን ከጨዋታ ውጪ አደረገ። ይህን ተከትሎም የቴሌቪዥንና የዲጂታል ሚድያው በዘርፉ ላይ በአዲስ መልክ ነገሰ” በማለት ይናገራል።  

ሆኖም የፊልም ኢንደስትሪው ወደ ቴሌቪዥንና በተለይ ደግሞ ዩቲዩብ ፊቱን ማዞሩ በዘርፉ የሚመረቱት የፊልም ስራዎች ጥራት ላይ አደጋ እየሆነ እንደመጣና ሙያዊ ብቃትም ኪሳራ ውስጥ እንደገባ ባለሙያዎች አፅዕኖት ሰጥተው ትችት የሚያቀርቡበት ጉዳይ ሆኗል። 

የዩቲዩብ ፊልሞች ከሲኒማ ፊልሞች በምን ይለያሉ?

ከወረርሽኙ በፊት አንድ በፊልም ኢንዱስትሪው የተሰማራ የፊልም ባለሙያ ፊልም ሰርቶ ጨርሶ ወደተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ከማሰራጨቱ በፊት በአንድ ሲኒማ ቤት በማስመረቅ ለእይታ ያበቃል። ከዚያም በኋላ ወደተለያዩ ሲኒማ ቤቶች አሰራጭቶ ገቢም ያገኛበታል፤ በፊልሙ ድርሻ ላላቸው ሰዎችም የሚገባቸዉን ክፍያ ይከፍላል። 

የፊልሙ ባለቤት በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ፊልሙን ለእይታ ካበቃ በኋላ ከፈለገ በራሱ ዩቲዩብ ላይ ይጭነዋል፣ ካልሆነም ለቻናል ባለቤቶች (ዩቲዩበሮች) ይሸጥላቸዋል። ይህንን በማድረግ በፊልሙ ለተሳተፉ አካላት የሚገባቸውን ክፍያ እንዲከፍል ከማስቻል ባሻገር አነሰም በዛም ለሙያው የሚመጥንና ጥራት ያለው ስራ እንዲሰራ አድርጎ ቆይቷል። 

ሆኖም ከኮቪድ በኋላ ሲኒማ ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ የፊልም ስራው ልምድ ለዩቲዩብ የሚሆኑ ፊልሞችን ወደ ማምረት አዘንብሏል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በተለያዩ በዩቲዩብ ቻናሎች የሚጫኑ ፊልሞች በአነስተኛና ወጪ ቆጣቢ ፕሮዳክሽን እስከ በ2 እና 3 ቀናት ብቻ ባለ ጊዜ የሚሰሩ ስለሆኑ ጥራት ይጎድላቸዋል ይላሉ። 

በተጨማሪም በዩቲዩብ ቻናሎቻቸው ላይ ፊልሞችን ለመጫን የሚገዙት የቻናል ባለቤቶች ለፊልሞች የሚያቀርቡት ክፍያ በፍጹም ፊልሞችንም ሆነ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎቹን የሚመጥን እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

ታደሰ የዩቲዩብ ፊልም በ pop art የሚመደብ የስነ ጥበብ ስራ አይነት ነው በማለት አስተያየቱን ይሰነዝራል። “pop art ማለት ደግሞ ርካሽ የጥበብ ይዘት ያለው፣ ቶሎ እይታ እንዲኖረው ብቻ የተቀመረ፣ እንዲሁም ሰዎች በቀላሉ እንዲቀበሉት ብዙ ቁምነገር ያላዘለ ነው። ይህም የአሰራር ባህል ችሎታ የሌላቸው በድፍረት እንዲሳተፉበትና ሙያው እንዳያድግ ያደርጋል” ይላል። 

ያብስራ ታዬ የፊልም ፕሮዲዩሰር፣ የካሜራ ባለሙያ እና ፕሮሞተር በመሆን በፊልም ዘርፉ የዳበረ ልምድ አለው። ያብስራ እንደባለሙያ ያለውን ትዝብት ሲያጋራ “የዩቲዩብ ፊልሞች ፊልም ለመስራት የሚያስፈልጉ ሂደቶችን ስለማይከተሉ፣ በቅናሽ ብር ስለሚገዙ፣ በቸልተኝነትና በለብ ለብ እንዲሁም ለትርፍ ብቻ ታስበው ስለሚሰሩ ዘበርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚገባቸው ክፍያ እንዳያገኙ ከማድረጉ በተጨማሪ የፊልም ኢንዱስትሪው እንዲያሽቆለቁል በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው” ይላል።

ብርሃኑ ፊልም የማየት የቆየ ልምድና ፍቅር እንዳለው በመግለጽ “አሁን አሁን የሚሰሩ ፊልሞች በጥራታቸው ሆነ በይዘታቸው በጣም የወረዱ እና ለፊልም ኢንዱስትሪው የማይመጥኑ ስራዎች እንደሆኑ” ይናገራል።

“በተለይ ከኮሮና መምጣት በኋላ በዩቲዩብ የሚለቀቁ ፊልሞች የድምጽና የምስል ጥራት የሌላቸው፣ የማጀብያ ሙዚቃዎቻቸው ብዙም የማይጥም፣ ወጥ የሆነ ቃለ ተውኔት የማይታይባቸውና ክህሎት የሌላቸው ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የፊልም አሰራርን የተከተሉ ናቸው” ይላል።

በዩቲዩብ ቻናሎች ላይ የሚጫኑ ፊልሞች እንዴት እይታ ሊያገኙ ቻሉ? 

በተለያዩ የዩቱብ ቻናሎች የሚጫኑ ፊልሞች ብዙ እይታ እንደሚያገኙ ብዙዎች ይስማሙበታል። 

ሆኖም በእነዚህ ዩቲዩብ ቻናሎች የሚጫኑ ፊልሞች ጥራት ከሌላቸው እንዴት እይታ እንዳገኙ የጠየቅነው በዘርፉ የዳበረ ልምድ ያለው ባለሙያ “በአሁኑ ሰዓት ብዙ ፊልም ተመልካቾች አሉ፣ አንድ ፊልም በዩቲዩብ ብዙ እይታ አገኘ ማለት ጥራት አለው ማለት አይደለም፤ ሰዉ ፊልም በዩቲዩብ የሚያየው እንደቀድሞው ጥራት ያለው የፊልም አቅርቦት ስለሌለና አማራጭ ስለሌለው ብቻ ነው” በማለት ይመልሳል።

የኮቪድ ወረርሽኝ እንደገባ ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎት ዋጋ ላይ በግማሽ (50%) ቅናሽ አድርጓል። በዚያን ጊዜ ሰዎች መሰባሰብ የማይችሉበት፣ ትምህርት ቤቶች የተዘጉበት፣ ወላጆችና ወጣቶች ከስራ ገበታቸው የተፈናቀሉበት ወቅት ስለነበረ ከኢንተርኔት አገልግሎት ዋጋ መቀነሱ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚ እጅግ ከፍ እንዳለ ብዙዎቹ የሚስማሙበት ነው። 

ይህም ሰዎች እንተርኔት በየቤታቸው አስገብተው በዩቲዩብ የሚጫኑ የአማርኛ ፊልሞችን ማየት እንደአማራጭ እንዲጠቀሙ የበለጠ እድል ፈጥሯል ይላል ታደሰ። 

የባለሙያዎቹ ችግርስ ምንድን ነው?

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሙያው ስነ ምግባር ተከትለው እንዱስትሪው እንዲያድግ እና በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ተግተው የመስራት ሀላፊነት እንዳለባቸው እሙን ነው።

ሆኖም በፊልም ስራ ላይ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች በተለይ የዩቲዩብ ፊልሞች ከመጡ በኋላ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሰነ ምግባር ክፍተት እንደሚታይባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። 

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ያጋሩን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ እንደሚሉት “በፊልም ኢንዱስትሪው የተሰማሩ ባለሙያዎች የዲስፕሊን ችግር እንዳለባቸው ግልጽ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

አርቲስቶችን እንደምሳሌ የሚያነሳው የፊልም ባለሙያው ያብስራ “ለዚህ የስነ ምግባር ችግር እንደ ምሳሌ ማንሳት የምንችለው ባለሙያው አንድ ፊልም ለመስራት የሚያስፈልግ ከፍተኛ ዝግጅት ካደረገ በኋላ ማለትም እቃ ከተከራየና ሌሎች ወጪዎች ካወጣ በኋላ  በአብዛኛው ጊዜ ተዋንያኑ በሰዓታቸው ስለማይገኙ እነሱን የምትጠብቅበት ጊዜ ላልተፈለገና ክፍተኛ ለሆነ ኪሳራ ይዳርጋል” ይላል።

የፊልም ባለሙያው ጋር ደግሞ የእቃ እጥረት ሰላለበት በቀረፃ ጊዜ የዘርፉ የሙያ ስነምግባር በማይፈቅደው መንገድ እና በማጭበርበር ስራው የተፈለገውን ጥራት እንዳይኖረው ያደርጋል በማለት ያብስራ ያስረዳል። 

በተጨማሪም አንዳንድ ባለሙያዎች ከቀረፃ በኋላ ሀርድ ዲስክ ጠፍቷል፣ ተበላሽቷል እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች በመደርደር በፊልም ኢንዱስትሪው መዋዕለ ነዋዩን ለማፍሰስ እና ከዘርፉ ለመጠቀም የመጣን ሰው ያለአግባብ ገንዘቡ፣ ጊዜው እና ጉልበቱ እንዲባክን 

የሚያደርጉ እንዳሉ ያብስራ ይገልፃል። “ይህንን በማድረግ ፊልም ላይ ኢንቨስት ሊያደርግ የመጣን ሰው የስቱዲዮ ምርኮኛ ያደርጉታል” ሲል የችግሩን ግዝፈት ይገልፃል። 

ሌላው የስነ ምግባር ችግር ስርቆት እንደሆነ የሚናገረው ያብስራ ፊልሞች በብዙ ዉጣ ውረድ አልፈው ከተሰሩ በኋላ ሊሰረቁ እንደሚችሉ ይናገራል። 

የፊልም ስርቆት?

ፊልም እንደማንኛዉም ንብረት በባለቤቱ ሊሸጥ የሚችል ነገር በመሆኑ እንደማንኛዉም እቃ ሊሰረቅ የሚችልበት አጋጣሚ አለ።

ፊልም ብዙ ጊዜ እንዳይጠፋ በሚል ስጋት በአንድ ኮምፒውተር ተጀምሮ በዛችው ኮምፒውተር ስራው እንዲያልቅ ባለሙያዎች የሚገደዱበት ሰዓት አለ። 

ለስርቆት የሚያመች አንድ “የስቱዲዮ ባህል” የሚባል ነገር እንዳለ ታደሰ ይገልፃል። የስቱዲዮ ባህል ማለት በአንድ ስቱዲዮ በጣም ብዙ ሰዎች ይሰበሰባሉ፤ ከነሱም ዉስጥ የማይታወቁ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚመጡ አሉ። እነዚህ የማይታወቁ ሰዎች ምንም ስራ ባይኖራቸውም ከስቱዲዮው አይወጡም። 

እነዚህ ሰዎች ከስቱዲዮ ስለማይወጡ ባለሙያዎቹ የሚያደርጓቸውን ነገሮች፣ ማለትም መቼ ስቱዲዮ እንደሚገባ፣ መቼ ለቀረጻ እንደሚወጣ ወይም እንደሚመለስ በመከታተል አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አልፎ የተሰራ ፊልም የተቀመጠበትን ሃርድ ዲስክ ይወስዱታል። ከዚያም በኋላ ፊልሙ የተቀመጠበት ሃርድ ዲስክ ወይም ፍላሽ ይዘው ፊልም ወደየሚጭኑ የዩቲዩብ ቻናል ባለቤቶች ያመራሉ” ይላል ታደሰ

ይህ በሚፈጠርበት ጊዜ የዩቲዩብ ባለቤቶች (ዩቱዩበሮች) ፊልሙ ይዞ የመጣን ሰው የባለቤትነት ጥያቄ፣ ከአርቲስት ጋር ያደረገው ዉል እና የፕሮዱዩሰር ማህበር ፍቃድ ሊጠይቀው ሲገባ ይህንን ሳይጠይቅ ንግድ ፍቃድ ብቻ አይቶ በርካሽ እና ለሙያውም ሆነ ለባለሙያው በማይመጥን ዋጋ እንደሚገዛው በአንድ ስቱዲዮ ውስጥ በዚህ ሁኔታ የተሰረቀን ፊልም በማንሳት ሁለት ባለሙያዎች አጫውተውናል።  

ከ100ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጎ የሰራው ፊልም እንደተሰረቀበት የሚናገረው አንድ ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ የፊልም ባለሙያ “ፊልሙን የሰረቀው ሰው ስራ ባይኖረዉም ከስቱዲዮ የማይወጣና የጓደኛው ጓደኛ እንደሆነ” ይናገራል።

ባለሙያው አክሎም “ብዙ የለፋህበት አንድ ፊልም ከእቅልፍ ስትነሳ በዩቲዩብ ማስታወቂያ ተሰርቶበት በቅርብ ጊዜ ይለቀቃል፤ ጠብቁ የሚል ነገር ከመስማትና ከማየት በላይ ምን የሚከብድና የሚያበሳጭ ነገር አለ” በማለት ምሬቱን ይገልፃል። 

“ፊልሙ ከ100ሺህ ብር በላይ ወጪ የወጣበት ቢሆንም የሰረቀው ሰዉዬ ግን በ80ሺህ ብር ሽጦታል፣ ይህም ከባድ የሙያ ስነ ምግባር መጣስ ነው” ሲል ሁኔታው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የስነምግባር ችግርን ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ ያስረዳል። 

ሌሎች ክፍተቶች 

የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ የፊልም ስራ እቃዎች (equipments) ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥመዉም በስራው ላይ ያሉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል። 

ፊልም ለመስራት የሚያስፈልጉ ሁሉንም እቃዎች ተከራይቶ እንደሚሰራ የሚናግረው ያብስራ “ፊልም ለመስራት የሚያስፈልጉ እቃዎችን ከውጭ ለመግዛት ብትፈልግ እንኳ የእቃዎቹን እና የቀረጡን ወጪ ለመሸፈን ከባድ ነው” ይላል። 

የኢትዮጵያ ፊልም ኢንደስትሪ በዚህ ፅሁፍ ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች የገዘፉ አያሌ ችግሮች ተጋርጠውበታል። የፊልም ኢንዱስትሪው ማደግ በሀገር የስነልቦና፣ ታሪክና ስነ ጥበብ እድገት ላይ የራሱ የሆነ ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው በመረዳት መንግስት ዛይዘገይ የፖሊሲ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ። 

አስተያየት