አቶ ሰመረ አበበን 'ፈለገ-አረጋውያን' በተባለው የአረጋዊያን መርጃ ውስጥ በአዳማ ከተማ ነው ያገኘናቸው። ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ በመገናኛ መሳሪያዎች ጥገና ባለሙያነት እና በሌሎችም ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት አቅመ ደካማ በመሆናቸውና ጧሪ ቀባሪ በማጣታቸው በተቋሙ ውስጥ እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛሉ።
የአምስት መቶ ሺህ ሰዎች መኖሪያ የሆነችው አዳማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች የኑሮ ውድነት አሻራውን እያሳረፈባትና እየፈተናት ይገኛል። እንደአዳማ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት መረጃ በአዳማ ከተማ ውስጥ 14 ሺህ አረጋውያን ይገኛሉ። እነዚህን አረጋውያን ለመርዳት በጽ/ቤቱ እውቅና አግኝተው የሚሰሩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች አሉ፤ ከነዚህም ውስጥ ፈለገ-አረጋውያን ፣ ሴዴቂያስ እና ሜቄዶኒያ የተባሉት የአረጋውያን መርጃዎች ይገኛሉ።
ጡረተኞችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህዝቡን እየፈተነ ያለው የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ያለምንም እልባት እና ማሻሻያ እንደቀጠለ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ይፋ ባደረገው የሐምሌ ወር ሪፖርት አጠቃላይ የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ከነበረበት 34 በመቶ የተወሰነ ቅናሽ አድርጎ 33.5 በመቶ መሆኑን ገልጿል። በሪፖርቱ እንደተገለጸው የምግብ ዋጋ ግሽበት ከ38.1 በመቶ ወደ 35.5 በመቶ መውረዱ ለዋጋ ግሽበቱ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል። ሆኖም አሁንም ሀገሪቱ ያለችበት የኑሮ ግሽበት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው።
አረጋውያን ከእድሜ መግፋት እና እርሱን ተከትሎ ከሚመጣ የጤና ችግር ጋር በተያያዘ ለኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው።
የአዲስ ዘይቤ የአዳማ ሪፖርተር የኑሮ ውድነቱ በአረጋውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና እንዲሁም በአረጋውያን መረጃ ማዕከላት ላይ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ዳሷል።
የኢኮኖሚ ቀውሱ እና የአረጋውያን ተጋላጭነት
ፈለገ አረጋውያን መርጃ ተቋም መኖሪያ፣ የምግብ ፣ የንጽህና እና የጤና አገልግሎት እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት አቶ ሰመረ በመንግስት አገልግሎት ዘመናቸው ለቆዩበት የጡረታ ክፍያ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
"የጡረታ ክፍያዬ 1 ሺህ 6 መቶ ብር ነው። የኑሮ ውድነቱ እጅግ ንሯል፤ የቤት ኪራይ ብቻ 1 ሺህ ብር በላይ ነው። የመርጃ አገልግሎቱ ባይኖር ከባድ ሁኔታ ውስጥ እገባ ነበር” ሲሉ ይገልጻሉ።
ፎቶ፡ ተስፋልደት ብዙወርቅ (ፈለገ አረጋውያን መርጃ ማህበር )
ፈለገ-አረጋውያን በአዳማ በአረጋውያን ድጋፍ ላይ ከተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አንዱ ነው። ማዕከሉ በአዳማ ከተማ ሁለት ቅርንጫፎቹ በድምሩ ለ58 አረጋውያን ድጋፍ ያደርጋል። ከዚህ ቀደም ማዕከሉ ለ183 አረጋውያን ቤት ለቤት ድጋፍ ያደርግ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ይህን ድጋፍ በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ከተቋረጠ ዓመት አልፎታል።
ሲስተር ሜሮን ተመስገን የፈለገ-አረጋውያን የአረጋውያን መርጃ ማዕከል መስራች እና ዳይሬክተር ናት። በ2008 ዓ.ም ህጋዊ እውቅና ያገኘው ይህ ተቋም የታሰበውን ያክል እንዳይሰራ የዋጋ ግሽበቱ ፈተና እንደሆነበት ትናገራለች።
"ከማዕከሉ ውጪ ቤት ለቤት የምናግዛቸውን ሌሎች 183 አረጋውያን መደገፍ ካቆምን 1 ዓመት ከ3 ወራት ሆኖናል" የምትለው ሲስተር ሜሮን ይህ የሆነው በኑሮ ውድነቱ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ እንደሆነ ትናገራለች። ለተከታታይ አራት ዓመታት በየወሩ 9 መቶ ብር የሚያወጡ የመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ከለጋሽ ግለሰቦች በተገኘ ገንዘብ ያቀርቡ እንደነበር ትናገራለች። አሁን ግን ይህ ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል እንደ ሲስተር ሜሮን ገለጻ።
“በማዕከላችን ሰባት አረጋውያን ከጤና አንጻር በቋሚነት የዳይፐር ተጠቃሚዎች ናቸው፤ በፊት በቀን 3 ጊዜ እንቀይርላቸው ነበር አሁን ወደ 2 ጊዜ ዝቅ አድርገነዋል" የምትለው ሲስተር ሜሮን ቀድሞ 24 ብር የነበረው ዳይፐር አሁን 102 ብር እንደገባ ትናገራለች።
የምግብ ሸቀጦች ላይ እጥፍ የሚጠጋ የዋጋ ለውጥ መኖሩን የምትናገረው መቅደስ ደግሞ የማዕከሉ ግዢ ክፍል ሰራተኛ ነች።
ዘይት ከ350 ብር ወደ 1 ሺህ ብር፣ ዱቄት በኪሎ ከ45 ብር ወደ 75 ብር፣ ጤፍ በኪሎ ከ38 ብር ወደ 57 ብር መጨመሩን ለአብነት ትገልጻለች። የአረጋውያኑን ንጽህና ለመጠበቅ የንጽህና ቁሳቁሶችም ልክ እንደምግብ ቁሳቁሶች ሁሉ በእጥፍ መጨመራቸውን ትጠቁማለች።
በማዕከሉ ውስጥም ይህ ሀገር አቀፍ ተጽዕኖ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ እንደሆነና ከአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ የቤት ኪራይ ጨምሮ የመብራት፣ የውሃ ፍጆታ፣ እና ሌሎች ወጪዎች የስራቸው ፈተና እንደሆነ ሲስተር ሜሮን ትናገራለች።
ፈለገ አረጋውያን ካሉት ሁለት ማዕከላት የመጀመሪያው በወር 15 ሺህ ብር የሚከፈልበት የኪራይ ቤት ሲሆን ሁለተኛውና አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ የሚገኘው ማዕከሉ ደግሞ በበጎ ፍቃደኛ የተሰጠ ነው።
"በ2011 ዓ/ም በአዳማ ከተማ ማዕከል ለመገንባት 5516 ካሬ ስፋት ያለው መሬት ተፈቅዶልን ነበር ነገር ግን ተፈጻሚ አልሆነም” ትላለች ሲስተር ሜሮን።
አቶ በሱፍቃድ ኤልያስ የ “ምሳሌ አዳማ መልካም ዜጋ ወጣቶች ማህበር” የበጎ አድራጎት ማህበር መስራች እና አስተባባሪ ነው። በማህበራቸው ውስጥ በተለያዩ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ተሰማርተው አረጋውያንን በመርዳት ላይ ይገኛሉ።
እንደ መስራቹ ገለጻ ማህበራቸው በዋነኝት ለ12 አረጋውያን እናት እና አባቶችን የሚረዳ ሲሆን በየወሩ በነፍስ ወከፍ 800 ብር የሚያወጣ የምግብ ድጋፍ ያደርጋል። ሆኖም እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት የለጋሾችንም አቅም የፈተነ በመሆኑ ለመልካም ስራቸው እንቅፋት ሆኗል።
በ1991 እ.አ.አ በወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአረጋውያን መርህ ውስጥ 5 ዋነኛ ሀሳቦች ተጠቅሰዋል። መርሆቹም ራስን መቻል፣ ተሳታፊነት፣ እንክብካቤ፣ በራስ መተማመን እና ክብር ይገባቸዋል ሲል ይገልጻል።
ነገር ግን በተቃራኒው በአሁን ወቅት በተለያየ ምክንያት የሚገባንን ቦታ እና ክብር እያገኘን አይደለም ይላሉ አረጋውያን ሁኔታው የግዜው ትልቅ የኑሮ ውድነት ፈተና እንደሆነ ውጤት እንደሆነ በማንሳት።
ወቅታዊው የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከ6.8 ሚሊዮን የኢትዮጵያ አረጋውያን መካከል የጡረታ አበል ተከፋዮቹ ከ7 መቶ ሺህ አይዘሉም። የሚደርሱባቸው ሌሎች ጉዳቶችን እንኳን ወደጎን ቢተዉ 90 በመቶ አረጋውያን የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ አይደሉም። ይህንን ጽሑፍ በምናዘጋጅበት ወቅትም የሁሉ አቀፍ ጡረታን (Universal Pension) ተግባራዊ ለማድረግ በብሔራዊ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ሰምተናል።
'አረጋዊ' ማለት ምን ማለት ነው? አለማቀፉ እና የኢትዮጵያ ህጎችስ ምን ይላሉ?
አንድ ሰው 60 ዓመት ከሞላው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድንጋጌ መሠረት አረጋዊ ለመባል ይበቃል።
ድርጅቱ ከወራት በፊት እንዳወጣው መረጃ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ባሉ ግጭቶች እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በአሁኑ ወቅት 5.1 ሚሊዮን ሰዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ከ8 መቶ 44 ሺህ በላይ የሚሆኑ አለማቀፍ ስደተኞች እንደሚገኙ ይገልጻል። ከነዚህ የጦርነት ሰለባዎች መካከል የሚገኙ አረጋውያን የሚጋፈጡት ፈተናም እጅግ ከባድ ይሆናል።
የኢፌደሪ ህገ-መንግስት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባሕል መብቶች በሚገልጽበት አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 5. ላይ
"መንግስት የአካል እና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንንና ያለወላጅ ወይም ያለአሳዳጊ የቀሩ ሕጻናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ያደርጋል" ሲል ይገለጻል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋውያን ጉዳይ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳምጠው አለሙ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጹት “በኢትዮጵያ 6.8 አረጋውያን ይገኛሉ፤ ከነዚህም 23 በመቶዎቹ በድህነት ውስጥ የሚገኙና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው”። ይህም ማለት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ አረጋውያን ቀጥተኛ ድጋፍ እንደሚያሻቸው መረጃው ያሳያል።
አቶ ዳምጠው እንደሚያስረዱት “የአረጋውያንን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት የተበጣጠሰ እና ቅንጅት የሚጎድለው ከመሆኑም ባሻገር በሴፍቲ ኔት እና በሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚደረጉት ጥረቶች በቂ አይደሉም”። ለአብነትም ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው 1.5 ሚሊዮን አረጋውያን ሴፍቲ ኔት 2 መቶ 60 ሺውን ወይም ከ18 በመቶ በታች ለሆኑት ብቻ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ይናገራሉ።
የጡረታ ክፍያ በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ከ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ እስከ 1950ዎቹ መጀመሪያ ድረስ በመንግሥት አገልግሎት ለተሰማሩ ሰዎች እንደ አገልግሎት እና የጡረታ ክፍያ መሬት ይሰጥ እንደነበር ድርሳናት ያሳያሉ።
ከጣሊያን ወረራ ማግስት በሀገሪቱ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመንግስት ሰራተኞች መበራከትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጡረታ ክፍያ ጋር ተዋወቀች።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጡረታ ክፍያ ስራ ላይ የዋለው በ1955 ዓ.ም ነበር። ይህ የጡረታ ክፍያ የሚያካትተው የመንግስት ሰራተኞችን ብቻ የነበረ ሲሆን የግል ሰራተኞች ጡረታ ለመጀመር ግማሽ ክ/ዘመን የሚጠጋ ጊዜ ፈጅቶ በ2011 ዓ.ም ነው ተግባራዊ የተደረገው።
በ2014 ዓ.ም በተደረገ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሽግሽግ የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትና ተጠሪነቱን ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተዘዋውሯል።
በ1993 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ አረጋውያን እና ጡረተኞች ማህበር በመላው ሀገሪቱ 1326 ማህበራትን ጥላ ሆኖ ያቀፈ ሲሆን 6 ሚሊዮን አባላት አሉት። የማህበሩ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ እና የአዲስ አበባ ኃላፊ አቶ ሽፈራው ክንፈ እንደሚሉት በተደጋጋሚ ስለአረጋውያን ቢጮህም ትኩረት አላገኘም።
“በቀድሞ ጊዜ ጡረታ የወጣን ጡረተኞች እጅግ አነስተኛ በሆነ ክፍያ ነው ጡረታ የወጣነው” የሚሉት አቶ ሽፈራው ክፍሉ ጡረተኛው ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ጀምሮ ፍላጎቱን ለማሟላት ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኝ ይገልፃሉ።
እስካሁን በኢትዮጵያ በህግ የተደነገገ ዝቅተኛ የጡረታ አበል ክፍያ የለም፤ ነገር ግን በመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የተቀመጠው ዝቅተኛ ክፍያ 1257 ብር ነው እንደ አቶ ሽፈራሁ ገለጻ። ነገር ግን ከዚህ የሚያንስበት አጋጣሚ እንዳለም ይናገራሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ “ባለጡረታው ሲሞት ለትዳር አጋር የሚሰጠው ክፍያ ከዚህ ያንሳል” ሲሉ አክለው ይናገራሉ።
በቀድሞው ጊዜ የጡረታ ክፍያ ማስተካከያ በየአምስት ዓመቱ ነበር የሚደረገው ያሉት አቶ ሽፈራው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ሲመጣ በሀገሪቱ ከፍተኛ የተባለውን ማሻሻያ እስከ 69 በመቶ መደረጉን እና በሒደት የጡረታ ክፍያ ማሻሻያ ግዜውም ወደ ሶስት ዓመት ዝቅ መደረጉን ይገልጻሉ።
የኢፌዴሪ የተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ በ1267/2014 መውጣቱ ይታወቃል።
በአዋጁ የቀድሞ አሰራር ወደ ሚኒስትሮች ም/ቤት እና ተወካዮች ም/ቤት የሚሄደው አሰራር ቀርቶ በራሱ ቦርድ እንዲመራ መደረጉን በማስታወስ ይህም የኑሮ ውድነትን ያገናዘበ ከአንድ እስከ ሶስት ዓመት ማሻሻያ እንዲደረግ የሚያስችል እንደሆነ አቶ ሽፈራው ይገልጻሉ፤ ነገር ግን ይህ እስከአሁን ድረስ ተግባራዊ አልተደረገም።
“የወጣው አዋጅ ተግባራዊ ይሁን፤ ያለው ሁኔታ ያስገድዳል” ሲሉ አቶ ሽፈራው የተግባራዊነቱን አስፈላጊነት አፅዕኖት ይሰጡታል።
በተጨማሪም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በም/ቤቱ ስብስባዎች ላይ በሚያነሱት ሀሳቦች ሁሉንም ያለማማከል በተለይም አረጋውያንን አለማስታወስ እንዳለ የኢትዮጵያዊ አረጋውያን እና ጡረተኞች ማህበር ም/ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ክፍሉ ትዝብታቸውን ያጋራሉ።
ሀገሪቱ ውስጥ ገዝፎ የሚታየው የኑሮ ውድነት ጫና የብዙሃን ዜጎችን ትከሻ የፈተነ ቢሆንም ሀገር ያቀኑ ቀደምት አረጋውያን በተለያዩ የቅርብ ሰዎቻቸው ከሚደርስባቸው የሀብት ንጥቂያ፣ አካላዊ ጉዳት እና ጾታዊ ጥቃት በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱ በሚያደርስባቸው ጫና በቃላት ሊገለፅ የማይችል ከፍተኛ ችግርና ፈተና ውስጥ ይገኛሉ።