ሐምሌ 9 ፣ 2013

ላዳ ታክሲዎችን በአዲስ መኪኖች የመቀየሩ ስራ ከምን ደረሰ?

City: Addis Ababaአካባቢማህበራዊ ጉዳዮች

በተለያየ ጊዜ በመንግሥት በኩል ታክሲዎቻችን ወደ አዲስ ተቀይረው ወደ ሥራው በተሻሻለ መልኩ እንደምንገባ ቢነገረንም ከወሬ ባለፈ ጠብ ያለ ነገር አላየንም ሲሉ የላዳ ታክሲ አግልግሎት ሰጪዎች ቅሬታቸውን ይገልፃሉ።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

ላዳ ታክሲዎችን በአዲስ መኪኖች የመቀየሩ ስራ ከምን ደረሰ?

ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ እንደሆነ የሚገመተው አቶ አባትይሁን አጥናፉ በላዳ ሚናቸው የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላለፉት 23 አመታት ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።

አሁን ላይ ሥራው እንኳን የቤተሰብ አሥተዳዳሪ ለሆነ ሰው ለአንድ ነፍስም ከብዷል የሚሉት አባትይሁን “አማራጭ ማጣት ሆኖብን ነው እንጂ ሥራውስ ከተበላሸ ቆየ ፤ በፊት በፊት ተማሪዎችንም የማመላለስ ስራም ነበረው አሁን ግን ላዳ ከነዚህ ስራዎች እየወጣ ነዉ ” ይላሉ፡፡

“ወጪና ገቢዬ አይመጣጠንም ታክሲዬን እንዳልሸጠው ደግሞ አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ አጥቷል። በተለያየ ጊዜ በመንግሥት በኩል ታክሲዎቻችን ወደ አዲስ ተቀይረው ወደ ሥራው በተሻሻለ መልኩ እንደምንገባ ቢነገረንም ከወሬ ባለፈ ጠብ ያለ ነገር አላየንም ” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ይህንን ምክንያት በማድረግም የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ( ኢ/ር ) ለዚሁ ሲባል የታክሲ ባለቤቶችን ከባንክ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንደሚሰራ የሚያስታዉሱት አዛዉንቱ የታክሲ ሹፌር ዕድሉን እሳቸዉም ለመጠቀም ከአመት በፊት 30 ከመቶ ክፍያ ለባንከ መክፈላቸዉን ይገልጻሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገባዉን ቃል እስካሁን ተግባራዊ ነገር አላየንበትም የሚለዉ ደግሞ ስሞታውን ለኣዲስ ዘይቤ ያሰማው ሌላኛው የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ ወጣት ተስፉ ሸዋለም ይባላል። ‹‹ 30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ከባንክ ጋር በማገናኘት እና ክፍያውን ከፈጸምን በኋላ እንደሚሰጠን ተነግሮን አብዛኞቻችን ከዚችሁ ገቢያችን ላይ የተባልነውን ብር ብናስይዝም መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን ግን ያወቅነው ነገር የለም።›› ሲል ተናግሯል።

“ስለታሰበዉ ነገር በዝርዝር ሾፌሩ እንዲገባው ተደርጎ የተነገረው ነገርም ስለሌለ ለመጠየቅ ራሱ ምቹ አይደለም ”   ሲልም ግልፅነት የጎደለውን አሰራር ይተቻል።  

አዲስ ዘይቤም “በከተማው የሚገኙት የላዳ ታክሲ አሽከርካሪዎች ቀጣይ ሁኔታ ምንድነው? የተገባውስ ቃል ምንደረሰ?” በማለት ጠይቃ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ “ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት ቃል የተገባው እንደ ትራስፖርት ቢሮ ሳይሆን እንደ ከተማ አስተዳደር ነው። እንደ ትራንስፖርት ቢሮ እቅድ ተይዞ የነበረው የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ የትራንስፖርት መጓጓዣዎችን በአዲስ፣ዘመናዊ፣እና ምቹ እዲሁም ለቱሪስቶችም ምቹ ለማድረግሲሆን እሱን በኛ በኩል በመስራት ላይ እንገኛለን። ለባለታክሲዎች ከቀረጥ ነጻ መኪናዎችን ለማስገባት ብድር የማመቻቸት ሥራ ሚሰራው ግን ከተማ አስተዳደሩ ነው።” ሲሉ መልሰዋል።

አዲሰ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የላዳ ታክሲ አሽከርካሪዎች በአሁን ሰዓት የላዳ ታክሲ ሻጮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱንና በተለይም በአሁን ወቅት የነዚህ መኪናዎች ዋጋ በጣም መውረዱን ገልፀው የታክሲዎቹ ዓይነት ይለያይ እንጂ ትንሹ እስከ 100 ሺህ ብር ሲሆን በጣም ከፍተኛ የሚባለው ዋጋ ደግሞ እስከ 300 ሺሀ ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል። አክለውም “መኪናውን ይዞ መቆየቱን የመረጥነው መኪናውን እስከ መጨረሻው ለያዙት ብቻ በአዲስ እንደሚቀየርላቸው ስለተነገረን ነው። የተለያዩ ድርጅቶች በጋራ በኪሎ ሜትር ለመስራት ጥያቄ ቢያቀርቡልንም የእኛ መኪናዎች አሮጌ በመሆናቸውና የነዳጅ ፍጆታቸው ከፍተኛ በመሆናቸው አያዋጣንም” በማለት ችግራቸውን ለአዲስ ዘይቤ አሳውቀዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የላዳዎች ታክሲ ማኅበራት ኮሚቴ አባል ደግሞ "እስካሁን በመንግስት በኩል የተገባልን ቃል አልተፈጸመልንም ታክሲዎቻችንን በምን መንገድ መቀየር እንዳለበን ምንም የተገለጸልን ነገር የለም ከዚህ ተጨማሪ የሆኑ ዝርዝር ነገሮች ባይገለፁልንም በእኛ በኩል ግን አባላቶቻችን ቁጠባቸውን እንዲቀጥሉ ከማድረግና ከመናገር እና የሚሆነውን ከመጠባበቅ ሌላ አማራጭ የለንም" ብለዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን በቀጥታ ይመለከተዋል የተባለው የአዲስ አበባ መስተዳድር አመራር ምን እየሠራበት እንደሆነ ለማወቅ አዲስ ዘይቤ በተደጋጋሚ ባደረገችው ሙከራ “ዋና ትኩረት መሠጠት ያለበት የአገልግሎት ዘርፍ እንደሆነ ታምኖበት ነው ቃል የተገባው ሆኖም ሰፊ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑና የከተማ መስተዳደሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራበት ስለሆነ መልሱ ዘግይቶ ሊሆን ይችላል ግን በቅርቡ ስራው ተጠናቆ ሁሉም አካላት ምላሹን ይሰጠዋል” ከሚል ምላሽ ባለፈ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት አልቻለችም።

በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው መኪናዎችን በማስመጣት ከታክሲ ማህበራት እና ከንግድ ባንክ ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑ የሚታወቀው ታክሲዬ የትራንስፖርት አገልግሎት ማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ ዲቦራ እንደነገሩን እስካሁን ድረስም የታክሲዬ መተግበሪያ በመጫን ከድርጅቱ ጋር የሚሠሩ የላዳ ታክሲዎች ቁጥር ብዛት 2700 እንደሆነና አሮጌ የላዳ ታክሲዎች በአዲስ ለመተካትም ከላዳ ታክሲዎች ጥያቄ ሲቀርብ 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም መኪናዎችን እንደሚስያረክቡ ገልጸዋል። አሮጌ ላዳ ታክሲዎችን በተመለከተም በእኛ በኩል መኪናዎችን የምንረከብበት ምንም ዓይነት ኹኔታ የለም ያሉት ዲቦራ እኛ በቁጠባቸው መሠረት እና የማህበሩን ጥያቄ ተከትለን መኪናዎችን እናስረክበቸዋለን ብለዋል። አክለውም የታክሲዬ አሰራር ከተማ መስተዳድሩ ከዚህ ቀደም ቃል ገብቶ ከነበረው ጋር የማይገናኝ መሆኑንና ገለልተኛ መሆኑን አስረድተው ከመስተዳድሩ ጋር እየሰራ ያለው ድርጅት ታክሲዬ እንደሆነ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ልክ አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአሁን ሰዓት መቀየር አለባቸው ተብለው ተመዝግበው የሚገኙ ያገለገሉ ላዳ ታክሲዎች ሥምንት ሺህ 95 መሆናቸውን ከትራንስፖርት ባለስልጣን ቢሮ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክት ሲሆን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ “አሁንም ድረስ የላዳ ታክሲዎች ማኀበር ጥያቄያቸውን ወደ እኛ እያመጡት ነው ታኪሲዎቹን ወደ አዲስ ለመቀየር በሚሠራው ሥራ ለአብነት ያህል እንኳን ብድር የማመቻቸት እና ታክሲዎችን ከቀረጥ ነጻ የማስገባት ስራ በከተማ አስተዳደሩ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው። በእኛ በኩል የከተማ አስተዳደሩ በሚያስተላልፍልን መመርያ መሰረት የሚጠበቅብንን እንሰራለን ስለዚህ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ከከተማ አስተዳደሩ ነው።” በማለት አስረድተዋል።

አስተያየት