በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መገባደጃ ላይ በዩኒቲ አካዳሚ ቀራንዮ ቅርንጫፍ ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች በሚቀጥለው የ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሂደት እንደማይቀጥል የትምህርት ቤቱ አስተዳደር መግለፁን ተከትሎ በተማሪ ወላጆች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል።
ትምህርት ቤቱ ውሳኔውን ሲያስተላልፍ ለት/ቤት ይውል የነበረው ቦታ የኪራይ ጊዜ መጠናቀቁን ለወላጆች ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማሳወቁን ቢገልፅም ወላጆች ግን በውሳኔዉ ደስተኛ የሆኑ አይመስልም። ዉሳኔዉ ትክክል አይደለም በማለት ልጆቻቸው ከሚማሩበት ቦታ እንዳይለቁ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
''ገንዘብ መጨመር ካለብን እንጨምራለን እንጂ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ት/ቤቶች የተማሪ ቁጥር እየገደቡ ባለበት በዚህ ጊዜ ለልጆቻችን ት/ቤት ለመፈለግ ተቸግረናል'' በማለት ወላጆች ተሰባስበው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ሙከራ እያደረጉ እንደሚገኙም ነግረውናል።
ይህም ት/ቤቱን የመልቀቅ አስገዳጅ ሁኔታ እንኳን ቢኖር ሊነገረን የሚገባው በዚህ ጊዜ አይደለም የሚሉት የተማሪዎቹ ወላጆች ት/ቤቱን የከፈቱትን የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤት ከሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን አዎንታዊ ምላሽ ለማግኘት ተስፋን ሰንቀዋል።
አቶ ነጻነት ደጉ በዩኒቲ አካዳሚ 4ኛ እና 5ኛ ክፍል የሚማሩ ልጆች ያሏቸው ሲሆን ት/ቤቱ በሚቀጥለው ዓመት የመማር ማስተማር ሂደት እንደማይቀጥል የገለጸበት መንገድ ልክ አይደለም ይላሉ። ውሳኔው በደብዳቤ ለተማሪዎች መሰጠቱን የሚያነሱት እኝህ ወላጅ ጉዳዩ በቀጥታ ለወላጆች መነገር ነበረበት ብለዋል። ‘'ልጆቻችን ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን የሚማሩበትን ቦታ ባለማወቃቸው በስነልቦና ተጎድተዋል በዚህም ምክንያት የዓመቱን ማጠቃለያ ፈተና ተረጋግተዉ መዘጋጀት አልቻሉም'' ይላሉ።
አቶ ነጻነት እንደሚናገሩት ለልጆቻቸው ት/ቤት ለማፈላለግ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸዉ ግን አልቻለም። "ወቅቱ በኮቪድ ምክንያት ተማሪዎች በፈረቃ የሚማሩበት እንደመሆኑ ት/ቤቶች አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ፍቃደኛ አይደሉም " በማለት ይገልጻሉ፡፡
ሌላኛዋ የወላጆች ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሳባ ሀ/ማርያም እንደ አቶ ነጻነት ልጆቻቸዉን ለማስመዝገብ ሌሎች ት/ቤቶች ሊቀበሏቸዉ አለመቻላቸውን ነዉ የተናገሩት። አብዛኛው ወላጅ በት/ቤቱ አከባቢ መኖሪያውን እንዳደረገ የሚናገሩት ወይዘሮ ሳባ ምክንያቱ ደግሞ በተቋሙ በመተማመን እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ በዚሁ ት/ቤቱ ለማስተማር በማሰብ ነው ይላሉ።
"በአስተዳደር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የልጆች የትምህርት ህይወት መጎዳት የለበትም" የሚሉት እኚህ እናት ጉዳዩ በአስተዳደር መካከል መፈታት ካልተቻለ ወላጆች በቀጥታ ለሚድሮክ ክፍያውን በመክፈል የትምህርት ሂደቱ መቀጠል ይችላሉ የሚል ሀሳብ አላቸው።
የዩኒቲ አካዳሚ ቀራንዮ ቅርንጫፍ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ዳይሬክተር ፍሬህይወት ገዛኸኝ ውሳኔ የተላለፈበት ደብዳቤ ሰኔ አንድ እና ሰኔ ሁለት ለወላጆች ከመድረሱ አስቀድሞ የት/ቤቱ የኪራይ ጊዜ መገባደዱን ከ2 ወራት አስቀድሞ የወላጆች ኮሚቴ መረጃው እንደነበራቸው ይገልፃሉ። ለዚህም እንደ ማሳያ የጠቀሱት የኪራይ ጊዜ በተገባደደ ወቅት ውሉን ለማስቀጠል የተማሪ ወላጆች ኮሚቴ በሽምግልና ጥረት ማድረጋቸውን ነው።
ነገር ግን በወላጆች ተማሪዎች እና መምህራን (ወተመ) የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ያለውን ሁኔታ ማለትም በ2014 ዓ.ም ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደማያስተምር መግለፁን ያስታውሳሉ ዳይሬክተሯ። በሌሎች የዩኒቲ ት/ቤት ቅርንጫፎች ተማሪዎቻቸውን ማስመዝገብ እንደሚችሉም አክለው ገልፀዋል።
በደብዳቤው ላይ ዩኒቲ አካዳሚ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ለ5 አመታት ተከራይቶ የቆየውን ስፍራ አከራዩ ቦታውን ለሌላ ተግባር ስለፈለገዉ ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቲ እንዲለቅ ወስኖ ማሳወቁን ፣ ት/ቤቱ በአቅራቢያ ባሉ በአከባቢው ለመከራየት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ገልጿል፡፡
የት/ቤቱ አስተዳደር ይህንን ጉዳይም በወቅቱ ለት/ቤቱ የወላጅ ተማሪ መምህራን (ወ.ተ.መ) ኮሚቴ በወቅቱ ማሳወቁንና በኮሚቴው በኩል የተደረጉ ጥረቶች አለመሳካታቸውን እና ለ2014ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባም አንደማይኖር አሳውቋል።
አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸዉ የህግ ባለሙያ ኪዳኔ መካሻ ደብዳቤው የተሰጠው ትምህርት ከሚጀመርበት መስከረም ወር 3 ወራትን ቀድሞ ሰኔ ላይ በመሆኑ ትምህርት ቤቱ ተጠያቂ የሚሆንበት አግባብ አይታየኝም በማለት መልሰዋል።
የህግ ባለሙያ ላምሮት ታምራት በበኩላቸው ወላጆች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ከህግ አንጻር ሊታይባቸው የሚችሉ መንገዶች መኖራቸውን ጠቅሰው ባለሙያዋ እንደሚሉት የት/ቤቱ መዘጋት የተማሪዎቹን በአቅራቢያ የመማር መብት እና አከባቢ ሲቀይሩ ሊደርስባቸው የሚችለው ተፅእኖ እንዲሁም በወላጆቹ ላይ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ችግር በክስ ሂደት ታሳቢ ሊደረጉ የሚችሉ ጉዳዮች ይሆናሉ።