ከዓመት በፊት ተደጋጋሚ የግጭት ዜናዎች ሲሰሙበት የነበረው “ገንደ ገራዳ” ከድሬዳዋ የመኖርያ ሰፈሮች አንዱ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች የመኖሪያ መንደሩ ሰላም መረበሽ የጀመረበትን ቀን ሲያስታውሱ በ2012 ዓ.ም. ጥር ወር ላይ የሆነውን ያነሳሉ፡፡ በወቅቱ በነበረው ሁከት ወጣቶች ጎራ ለይተው ድንጋይ ይወራወራሉ፡፡ በእግረኛ እና በተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ እንደ ጎማ ያሉ ተቀጣጣይ ላስቲኮችን ያቃጥላሉ፡፡ ግርግሩን የፈሩት ነጋዴዎች ሱቃቸውን ዘግተዋል፡፡ በረደ ሲባል እየተባባሰ፤ አሁን የለም ሲባል እየጨመረ ለሳምንታት የቀጠለው ግጭት ብዙ ጉዳቶችን ማስከተሉ ይታወሳል፡፡ ክስተቱ በሰዎች የተሞላውን መንደር ጸጥታ እንዲወርሰው ያደረገ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡ በተለይ በምሽት በምትደምቀው ድሬዳዋ “ገንደ ገራዳ” ለብቻዋ ትደበዝዛለች፡፡ የወቅቱ ግጭት በአብዛኛዎቹ የድሬዳዋ ከተሞች የተዛመተ ቢሆንም እንደ ጎሮ፣ ለገሀሬ፣ ጀርባ፣ ገንደ ገራዳ ባሉ ሰፈሮች ግን ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቷል፡፡
ከወራት በፊት ያጋጠመው ክስተት በመንደሮቹ ላይ አሻራውን ጥሎ ያለፈ ይመስላል፡፡ በአሁን ሰዓት ከአካባቢው የግጭት ዜናዎች ባይደመጡም፣ ሰላም የሚነሱ አስጊ ሁኔታዎች ባይኖሩም፣ ነዋሪዎቹ አስቀድሞ ወደነበሩበት እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ገብተዋል የሚባልበት ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ “ገንደ ገራዳ” ላይ አሁንም ሰዎች እንደልብ አይጓዙም፣ አሁንም የምሽት ስጋታቸው አልለቀቃቸውም በአካባቢዎቹ ተዘዋውረን የሁኔታውን ምክንያት ለማጣራት ሞክረናል፡፡
“ገንደ ገራዳ”ን ጨምሮ አለመግባባቶች ሁሉ ወደ ብሔር ወይም ሐይማኖት ግጭቶች የሚያመሩባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አማራጭ ፈልገዋል፡፡ በቤት ኪራይ የሚኖሩትም ሆኑ የግል እና የቀበሌ ቤት ያላቸው ሰዎች ሰላም አለበት ወደሚሉት አካባቢ ተከራይተው ሄደዋል፡፡ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ቤታቸውን ትተው ሌላ ሰፈር መኖር ጀምረዋል፡፡ ይህ የወቅቱ ሁኔታ በዚያን ጊዜ ለሚስተዋለው ክስተት በበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የተሰጠ ምላሽ ነበር፡፡ አሁን ነገሮች ሁሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴአቸው በተመለሱበት ጊዜም እንደቀጠለ መሆኑ ግን ለጥያቄ ይጋብዛል፡፡ በክስተቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጫና የሚያስከትለውን ውሳኔ ተገደው የወሰኑት የ“ገንደ ገራዳ” የቀድሞ ነዋሪዎች ለምን ወደሰፈራቸው አልተመለሱም? የሚል መልስ ፈላጊ ጥያቄን ያጭራል፡፡
አዲስ ዘይቤ የአካባቢውን ነዋሪዎች ጠይቃ መልስ ለማግኘት ሞክራለች፡፡ ነዋሪዎቹ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ያልተመለሱበትን ምክንያት አስመልክቶ ሲናገሩ ሰፈራቸውን ያስለቀቃቸው ግጭት ምክንያቱ እና መነሻው አለመታወቁ አንዱ ሰበብ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ግጭቶቹ መነሻቸውም መጨረሻቸውም አይታወቅም ነበር፡፡ ጥቂት የማይባሉት ግጭቶች ደግሞ ከሌላ ቦታ በመጡ ጸብ ጫሪዎች አማካኝነት የሚጀመሩ ናቸው፡፡ አነስተኛ የሚባል የጓደኞች ጥል ሳይቀር በብሔር እንድንጋጭ አነሳሽ ምክንያት ሆኖ ያውቃል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በ“ገንደ ገራዳ” ሰፈር በልዩ ስሙ “ቁጠባ” በሚባለው አካባቢ መኅበራዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክር እንደ እድር ያለ እንቅስቀሰሴ ቢኖርም እድሩ እንደተለመደው ከአካባቢው ራቅ ብሎ በፊት በግጭት ውስጥ ወደነበሩ አካባቢዎች በመጓዝ የሚያጽናናበት አሰራር እየቀነሰ መምጣቱንም ተረድተናል። ለዚህ በምክንያትነት የተጠቀሰው ከግጭቱ በተጨማሪ የእድሜ ባለጸጋ የነበሩት የእድሩ አመራሮች ለማሀበራዊ መስተጋብሮች ልምድ በሌላቸው ወጣቶች መተካታቸው ነው፡፡
“ገንደ ገራዳ” ውስጥ በአሁኑ ሰዓት አንፃራዊ ሰላም ላይ የምትገኝ ቢሆንም፤ ነዋሪዎቿ ወደቀያቸው ተመልሰው በፊት የነበራቸውን የእርስ በእርስ መስተጋብርና ማኅበራዊ ኑሮ ማስቀጠል አልቻሉም፡፡ አሁን በሰፈሩ ውስጥ የሚገኙት ነዋሪዎቻም ውስጣቸው ፍርሀት እንዳለና በገደብ እንደሚንቀሳቀሱ የመጀመሪያ ፍቅራቸው እንደ ደፈረሰ እንዲሁም በተለይ አዛውንቶች በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ሌላ ሰፈር ከሄዱ ሳይጨልም ለመግባት እንደሚጣደፉ የገለጹልንም በርካታ ናቸው፡፡
ነዋሪዎቹ ወደ ሰፈራቸው የማይመለሱበት ምክንያት የዳግም ግጭት ስጋት ስላለባቸው እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎቻችን እድሜአቸው ከ16 የማይበልጥ ወጣቶች ግጭቶቹን ያስነሱ እንደነበር አስታውሰው ልጆቹ የሌሎች ጉዳይ አስፈጻሚ እንደነበሩ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የአብዛኞቹ ሐሳብ ጸቡ የኛ ስላልነበረ እኛ ብንኖርም ባንኖርም ለውጥ አይኖርም ግጭቱ ዳግም ላለመመለሱ ምንም ማረጋገጫ የለንም የሚል ነው፡፡