ሐምሌ 11 ፣ 2013

ጎብኝ እና ገቢ የነጠፈባት ባህር ዳር

City: Bahir Darኮቪድ 19ኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

ባሳለፍነው ዓመት የዓለምን ኢኮኖሚ ያደቀቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ህመም፣ የሀገሪቱ አለመረጋጋት ደግሞ ለቱሪዝሙ መናጋት መንስኤ መሆኑ ባህርዳር የቱሪዝም የገቢ ምንጯን በከፍተኛ ሁኔታ እንድታጣ አድርጓል።

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

ጎብኝ እና ገቢ የነጠፈባት ባህር ዳር

የሀገራችን ቱሪዝም በባህሪው የአውደ ዓመት ቱሪዝም ተብሎ የሚመደብ አይነት ነው፡፡ የጎዳና በዓላት እና የህዝባዊ ዝግጅቶች የሚበዙበትን ያህል ዓለምን ያስደመሙ አፍሪካን ጭምር ያኮሩ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት በመሆን ለቱሪዝሙ ዘርፍ ሁነኛ መዳረሻ የመሆን እምቅ አቅም እና ችሎታ እንዳለው ይታመናል፡፡

ከዚህ ዘርፍ ጫማ ጠርገው፣ ገቢ ከሚያመነጩበት እስከ ትላላቅ የሆቴል ዘርፎች እና የሃገር ምንዛሬ ተስፋ የተጣለበት ነው። በተለይም የውጭ ምንዛሬ በማምጣት የንግድ ዘርፉን ሚዛን ለመጠበቅ አይነተኛ ሚናውን ይወጣል ተብሎ ይታመናል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት የዓለምን ኢኮኖሚ ካደቀቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ችግር የኢትዮጵያ የቱሪዝም ህመም፣ የሀገሪቱ አለመረጋጋት ለቱሪዝሙ መናጋት መንስኤ መሆኑን፣ አዲስ ዘይቤ በባህር ዳር ከተማ የቱሪዝም መስክ ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገችው ቆይታ አረጋግጣለች፡፡

በተለይም ወደ ላልይበላ እና ጎንደር እንዲሁም አልፎ አልፎ ባህር ዳር መደበኛ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎት መቋረጡ በከፍተኛ ሁኔታ የጎብኚውን ፍሰት ገድቦታል፡፡ የሐገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚ ካሰበው ስፍራ በእቅዱ መሰረት በጊዜ እና በሰዓቱ መገኘት አለመቻሉ እና የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፏቸው ሪፖርቶች እና የኤምባሲዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሰላም ቀጠናዎችን ሁሉ የጦርነት አውድማ አስመስለው ማቅረባቸው ዘረፉን አቃውሶታል፡፡ አሁን ላይ የሴክተሩ ተዋናዮች ሰራተኞቻቸውን የቀነሱበት ያለባቸውን የብድር እዳ መመለስ ተስኗቸው የማገገሚያ ማበረታቻ የሚሹበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል፡፡

የዘረፉን መቃውስ የሚያሳዩን በባህር ዳር ከተማ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያ የሆኑት  ወ/ሮ ማሪቱ አበበ  አንደነገሩን የኢትዮጵያ ቱሪዝም አፈፃፀም በውጭ ሀገር ቱሪስት ረገድ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእጅጉ ያሽቆለቆለበት እና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር “የለም” ለማለት የሚያስደፍርበት ሁኔታ ላይ ይገኛል ይላሉ፡፡  “የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ሀገር ውስጥ መምጣት አቁመዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች እንቅስቃሴ በእጅጉ ተዳክሟል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴውም በጣም የደከመ ነው፡፡ ከዘርፉ ያጣነውን በተመለከተ የባህር ዳር ከተማ የ2013 ዓ.ም. አፈፃፀም እንደሚያሳየን በበጀት ዓመቱ ከመዳረሻ የውጭ ሀገር ጎበኝዎች የእቅዳችንን 96 በመቶ አላሳካንም፡፡ ይህም አፈፃፀማችን ዜሮ ነበር እንደማለት ነው” ይላሉ፡፡ በተመሳሳይም በሀገር ውስጥ ቱሪስቱ ውስጥ ታሳቢ ይደረግ የነበረው በሚልየኖች የሚቆጠር ጎብኝ በዚህም ዓመት በተፈጥሮ እና በበዓላት የበለጸገችውን ባህር ዳር በቱሪስትነት የጎበኙት ከ3,4000 የማይበልጡ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህ ትልቁ ምክንያት በሐገሪቱ ያለው አለመረጋጋት እና የኮረና ወረርሽኝ ነው፡፡ በተለይም አለመረጋጋቱን መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ “ሰላም ከሌለ ቱሪዝም የለም” የሚለውን አበክረው ወ/ሮ ማሪቱ አሳስበዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የሐገራዊ ኢኮኖሚዋን ለመቀየር ተስፋ ከሰነቀችባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በ10 ዓመት የሀገሪቱ መሪ እቅድ አስመልክተው በተደረገ ውይይት ላይ እንደተናገሩት በኮሮና ሳቢያ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ኢትዮጵያ አጥታለች፡፡ 

በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ስሟ እየተነሳ የሚገኘው ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ክስተት ተጨምሮ ካቀደችው በታች እንድትፈፅም አድርጓታል፡፡ ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ በዓመቱ ታገኝው የነበረው ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን ነው፡፡

ቱሪዝም ኢትዮጵያና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ያደረጉት የ10 ዓመት መሪ እቅድ ሰነድ እንደሚያሳየው ከ10 ዓመት በኋላ 7 ሚሊዮን ‘ቱሪስት’ ኢትዮጵያን ይጎበኛል የሚል መሪ እቅድ ያነገበ ነው፡፡ ክስተቱ የእቅዱን ተፈጻሚነት ገደል የከተተ ነው፡፡ ለአብነትም በባህር ዳር ከተማ ከ3,000 በላይ በቀጥታ በቱሪዝሙ ዘርፍ ህይወታቸውን ይደጉሙ የነበሩ ወገኖች ስራ ፈት ሆነዋል፡፡

እንደ የባህር ዳር ከተማ አሰተዳደር ባህል ቱሪዝም እና ወጣት መምሪያ ባለሙያ ወ/ሮ ማሪቱ ገለጻ በተለይ አሁን ባለው ሐገራዊ አለመረጋጋት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የዘርፉ መሪ ተዋንያን ተጎጅ ሆነዋል፡፡ ለአብነትም መኪና አከራዮች፣ የትራንስፖርቱ ዘርፍ፣ አስጐብኚዎች፣ የመኪና አከራዮች፣ በመስህብ ቦታዎች ላይ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች፣ ባለቤቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት… ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪ ብሄራዊ ፓርኮች፣ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ አቢያተ መንግስታት፣ የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ እምነት ጥለው ይሰሩ የነበሩ የተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት በተለይ ሆቴሎች፣ አስጐብኚ ድርጅቶች፣ የስጦታ እቃ መደብሮች፣ ባህላዊ ምግብና መጠጥ ቤቶች እንዲሁም ተያያዥ የንግድ ድርጅቶች በአሁኑ ሰዓት በሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ እና ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ተቀዛቅዘዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በቢዝነስ ተቋማቱ ውስጥ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩት ሁሉ ስራ ፈተዋል፡፡

ከ37 በላይ የጣና ሐይቅ ደሴቶች ዛሬ እንደቀድሞው የውጭ ሐገር ጎበኝዎች አይመላለሱበትም፡፡ እረፍት አልባ ጀልባዎች ከጣና ደቡባዊ እስከ ሰሜናዊ ክፍል ሲከንፉ ዐይታዩም በሐይቁ ከመቸውም ጊዜ የባሰ ፀጥታ ነግሷል፡፡

ወጣት ይሄነው ላለፉት 10 ዓመታት በጣና ደሴቶች ውስጥ በአስጎብኝነት ይሰራል፡፡ በዘጌ እና አካባቢው ያሉ የጣና ውስጥ ገዳማትን በማስጎበኝት ከጓደኞቹ ጋር ሁኖ በመሰረተው ማህበር በቀን እስከ 20,000 ብር ድረስ ያስመዘገቡ ነበር፡፡ ላለፉት አንድ ዓመት ግን ገበያ የሚባል በመጥፋቱ ምንክያት አብዛኛዎች የስራ ዘርፋቸውን ለቀው በሌላ ለመሰማራት አልያም፣ በስራ አጥነት ቤታቸው እንዲውሉ ተገደዋል፡፡

“አከርካሪያችንን ነው የበጠሰው!” የሚለው ሌላው የጀልባ ባለቤት ጣናን ለማቋረጥ እና በሐይቁ ጊዜ ለማሳለፍ ያለሞተር ጀልባዎች የማይታሰብ መሆኑ እሙን ቢሆንም እንደ ወጣት ትዕግስቱ ገለፃ ቀኑን ሙሉ እረፍት አልባ የነበረው የጀልባዋ ሞተር አሁን የሚቀሰቀሰው በሳምንት አንድ ቀን ያውም ዕድል ብሎ ከተሳካ እንዳውም ለወራት ሸራ የለበሰ ጀልባውን ገልጦ ለማየት አለመቻሉን በመግለፅ በደህናው ቀን ያጠራቀመውን ተመግቦ ወደመጨረስ ማምራቱን ይናገራል፡፡

መንግስት ተማምነው ግዙፍ ባለኮከብ ሆቴሎችን የገነቡ የባህርዳር ሆቴሎች ላለፉት ዓመታት ክፉኛ በተጎዳው የሆቴል አገልግሎት ከግማሽ ባላይ ሰራተኞቻቸውን ቀንሰዋል፡፡ ከመንግስት የወሰዱትን ብድር በመመለስ እና ባለመመለስ ውዝግብ ላይ ናቸው፡፡

የባህር ዳር ሆቴሎች ማኅበር ከመንግሥት ጋር ተደጋጋሚ የደብዳቤ ልውውጦች ከማካሄድ አንስቶ፣ መንግስትን ይግባኝ ከጠየቁ ወራት  ያለፋ መሆኑን በባህር ዳር ሆቴሎች አገልግሎት ባለሙያ አቶ ሲሳይ በለጠ ነግረውናል፡፡

በተለይ በቱሪስት መገኛ አካበቢዎች አነሰተኛ የስጦታ እቃዎችን ሽጠው የሚያድሩ የጢስ ዓባይ አካባቢ እደጥበብ ባለሙያዎች እንደነገሩን ያነጠሯቸውን ኢትዮጵያዊ ይዘት ያላቸው የብር እና የነሐስ ቅርፃ ቅርፆች፣ የሰፏቸውን ሙዳይ፣ አገልግል፣ ሞሰበ-ወርቅ የሚወስድላቸው በማጣታቸው ብድራቸውን ለመመለስ ተቸግረዋል፡፡ “ኮቪድ ወረታችንን በላው” የምትለው ዓለምፀሐይ ቢያዝን ‘ቱሪስት’ ካየን 1 ዓመት ሆነን ስትል የሁኔታውን ክብደት ታስረዳለች፡፡

“እስካሁን ገቢያችን መጨመር ወይም መቀነስ ካልሆነ በቀር ነጥፎ አያውቅም” የምትለው ዓለምጸሐይ “አሁን ግን ህይወታችን አደጋ ላይ ወድቋል” ትላለች፡፡

ጢስ ዓባይ ፏፏቴ ከተማዋ የቱሪስቶች መቆያ ብትሆንም አሁን ግን ሁሉም ሙሉ ለሙሉ ሥራው ቁሟል፡፡

አሁን የያዝነው ወረት አልቆ፣ የተበደርነው ወለድ ጨምሮ ኪሳራ ውስጥ ወድቀናል። ይህን ተከትሎ ወጣቱ የተቻለው ስደት፣ ያልቻለው ተቀምጦ የሚለወጥበትን ጊዜ የሚናፍቅ ሆኗል፡፡ ቤተሰብ አሰተዳዳሪ የሆኑ ወጣቶች ዛሬ ቤታቸውን መደጎም አልቻሉም ስትል ታስረዳለች ዓለምጸሐይ።

በተለይም አዝማሪዎች የቀውሱ ገፈት ቀማሽ ሁነዋል፡፡ ያለጤና እና ሰላም ተዝናኖት የለም የሚለው የባህር ዳሩ ድምፀ-መረዋ ፋሪስ ምሬቱን በመሰንቆው ጭምር እየገጠመ አጫውቶናል፡፡

አዝማሪ ፋሪስ ማስንቆው እና ተፈጥሮ የሰጠችው ድምፁ የቤቱ ኑሮ ደጋፊ ናት፡፡ በባህል ምሽት የምትደምቀው ባህር ዳር እንደቀድሞው በቱሪስቶቿ ኢትዮጵያን ለመቅመስ በሚመጡ ወዳጆቿን አታዝናናም፡፡ በምሽት ከመስንቆው ጋራ በባህል ቤቶች የኢትዮጵያን ጭፈራ እያሳየ ሙዚቃውን የሚያቀርብበት ቤት እንደድሮ ዶላር አያገኝም፡፡ ነገሩ ሁሉ እንኳን ‘ቱሪስቱ’ ሰርግ ከናፈቀን ቆየ የሚል መልስ ነው የሚሰጠው፡፡ 52 አባላት ያሉት አዝማሪዎች ማኅበር ሰብሳቢ ሊቀመኳስ ፋሪስ “መስንቋችንን እንዳንሰቀል ልጆቻችንን ምን እናብላ… እንደውም ስለኮረና እማ አንዱን በማስቆ ልበልልህ”

መሰንቆውን ቃኝቶ፣ ባማረ ድምጹ፣ በውብ ዜማ እንዲህ አንጎራጎረ

“ኮረና ከመጣ ጎዳናው ጠፋን

ሰላምም ከራቀን ሆዳችን ከፋን

ኢትዮጵያ ሐገሬን ኮረናን አጥፍቶ ሰላም ያርግልን”

“እኛ ደሞዛችን ‘ቱሪዝሙ’ ነው፡፡ አሁን ደግሞ እንደምታየው ሰላም ከራቀን እና ኮረና ከገባ ወዲህ ደመወዝ ቁሟል ብልህ ይገልፀው ይሆን?” 

ሌላው አዝማሪ አበባው “ድሮ ህይዎታችንን ያለችግር እንሞላ ነበር:: እንኳን ሰው ወንዝ እናጫውት ነበር፡፡ አሁን ምንም የለም:: ወዳጄ ስንቱ አዝማሪ ቤት ነው ደጁን መልሶ መሰንቆውን ሰቀሎ የተቀመጠው እኛ እርሻ የለን ወይ አዘምነውን በክሊፑ ስራ አልገባን የሰው ደጅ እና ፊት እያዝናናን ላይቭ ነው የኖረነው”

“አብዛኛዎቹ የዓለም ሐገራት ቤታቸው መሰብሰብን በመምረጣቸው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከውጭ አገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ቱሪዝሙም ስፖርት ቱሪዝሙን ጨምሮ ተጎድቶ ቆይቷል፡፡ ባህር ዳር ያላትን ስቴዲየም ዘግታ የሐገር ውስጥ ጨዋታዎችን የምትመለከተው በቴሌቪዥን መስኮት በዲኤስቲቪ ነው” ያሉት  የባህር ዳር ከተማ ባህል ቱሪዝም ወጣቶች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ስለሺ ቢኒያም ናቸው።

አስተያየት