ሐምሌ 12 ፣ 2013

ሊዝ የበላቸው የመሬት እዳዎች ጩኸት

City: Bahir Darመልካም አስተዳደርዘገባ

የማይቀመስ የመሬት የሊዝ ዋጋ ንረት ደግሞ ሕገ-ወጥነቱን አስፍቶታል፡፡ የመንግሥትን ቀዳዳ ፈልገው ከሚያማክሩ ባለሙያዎች እስከ ጉዳይ ፈፃሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ 24 ሰዓት የፍጥጫ አጀንዳ አንዱ መሬት ነው፡፡

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

ሊዝ የበላቸው የመሬት እዳዎች ጩኸት

“የተሰራሁት ከአፈር ነው… የምኖረው በመሬት ነው፡፡ የምቀበረውም በአፈር ነው፡፡ እኔ መሬት አፈርም ነኝ፡፡”

የእርሻ መሬታቸውን ተነጥቀው ያለበቂ ካሳ በውድ ዋጋ የከተማ አሰተዳደሮች የራሳቸውን ገቢ የሚያደልቡባቸው አርሶ አደሮች ትዝብት ነው፡፡ አርሶ አደር እየተገፋ ወደዳር የመውጣቱን ያህል፣ ከተሜው በመቶሽኛ የቤት ፈላጊዎች መዝገብ ውስጥ ስሙን ፈልጎ ለማግኝት ቢከብደው የሊዝ ጫረታን የሙጥኝ ብሎ ይጠብቃል፡፡ አሁን የማይቀመስ የመሬት የሊዝ ዋጋ ንረት ደግሞ ሕገ-ወጥነቱን አስፍቶታል፡፡ የመንግሥትን ቀዳዳ ፈልገው ከሚያማክሩ ባለሙያዎች እስከ ጉዳይ ፈፃሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ 24 ሰዓት የፍጥጫ አጀንዳ አንዱ መሬት ነው፡፡

በአንድ ወቅት ባህርዳር ከተማ ላይ አንድ ወዳጄ ቤት እንዳለን እና እንደሌለን ጠየቀን፡፡ ሁላችንም እንደሌለን ስንነግረው ተገርሞ “በዚህ ወቅት ሃብታም ማን ነው ብትሉ… ባንክ ብር ያለው ሳይሆን በስሙ አንድ የውሃ ጀሪካን ማስቀመጫ ቦታ ያለው ሰው ነው!” ሲል ያስጠነቀቀን ከዓመታት በኋላም ድምፁ በጆሮዬ ያቃጭላል፡፡ ተወልጄ ባደኩበት ከተማ እንዴት ቦታ ሊኖረኝ እንዳልቻለ እያሰላሰልኩ፣ በመንግሥት የተነጠቅነውን የመሬት ስፋት በዐይነ ህሊናዬ የወደመብንን አትክልት አስታውሼ፣ ከ11 በላይ ሆነን ባደግንበት ቤት አንዳችንም ቤት የሌለን መሆኑን አስቤ፣ እሱ እንዴት መሬት ሊያገኝ እንደቻለ ስጠይቀው “በሊዝ ገዛሁ” የሚል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ ብዙ ጊዜ መሬት በሊዝ የመግዛት ፍላጎት ኖሮኝ ለመሞከር አስቤ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ለሊዝ የሚቀርበውን የዋጋ መጠን መገዳደር አልቻልኩም፡፡

“መሬትን እያወኩት በመጣሁ ቁጥር እየጨመረ እየራቀኝ እንደሄደ ይሰማኛል” ይላል ባለፉት ሰባት ዓመታት የቤት ሥራ ማኅበር ውስጥ ተደራጅቶ ወረፋ የሚጠብቀው ፈቃዱ በላይ “ሁሌም የሊዝ እና የመሬት ባለቤቶች ውስን እና ጥቂት ከበርቴዎች እንደሆኑ ይሰማኛል” የሚለው የባህርዳር ከተማ ኗሪ አስተያየት ነው፡፡ ሌላዋ እየሩሳሌም ዓባይ በበኩሏ “በከተማዋ ያለው የመሬት ሊዝን ሽፋን ያደረገ ሚስጥር ጊዜ ይፍታው ምንያቱም አሻጥረኛው አመራሩ እና ባለሙያው ጭምር ነው” ስትል አስተያየቷን ባህርዳር ከተማ ውስጥ የከተማ ቦታዎች በሊዝ የመያዝ አፈፃፀም ጉዳይ እንዴት እንደምትመለከተው አስተያየቷን የጠየኳት ኗሪ ሃሳብ ነው፡፡

በአነስተኛ ካሳ ተገፋን ብለው ቅሬታ ከሚያሰሙት የከተማዋ ዙሪያ አርሶ አደሮች እና ከተማው በሰፋ ቁጥር እየተነሱ ወደዳር የሚወጡት ባለይዞታዎች መሬታቸውን በሊዝ የተላለፈበትን ዋጋ በነሱ ጊዜ “ሰውነቴን ተቀማሁ” ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀውታል፡፡ ያልዘመነው የከተማ ልማት እና የቤቶች ልማት መርሃ-ግብር ለአንዱ መኖሪያ ለሌላው መፈናቀያ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ እንደነ እማሆይ ጥላነሽ ተፈራ ዓይነቶችን ባለይዞታ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጭምር ሆኖ ይደቀንባቸዋል፡፡ ለዚህም ፍትሕም ሕግም በአዋጅ የታሰረ፣ በከተማ አሰተዳደሮች ሥልጣን የሚፈፀም ፍርድ ቤቶች የማያዩት ሆኖባቸው የሚያሰሙት የመሬት ባለቤትነት ብቻ ሳይሆን ባለይዞታነት፣ ባለመብትነት ጥያቄ ጭምር ነው፡፡

ይህ ለመሬት ባለቤቶች፣ ለከተማ አልሚዎች፣ ለቤት ገንቢዎች፣ ለመሬት አሰተዳዳሪዎች የማያግባባ የከተማ አጀንዳ ነው፡፡ ለመሆኑ በባህርዳር ከተማ የሊዝ መሬት ማጭበርበሮች፣ አፈፃፀሞች እና ኗሪውን ግራ ያጋባው ሂደታቸው ምን ይመስላል በሚል በዚህ ጽሑፍ የተፈፀሙ ብልሹ አሰራሮችን እና ማሳያዎችን አጣቅሰን ሂደታቸውን ቃኝተን መልካም ንባብ ብለናል፡፡

የሊዝ ሕግ

ለመሆኑ “ሊዝ” ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ስል የሃሳቤን ማበከሪያ ለሕግ ባለሙያው አቶ ወዳጀ መኮንን ጥያቄን አቀረብኩ፡፡ እርሳቸውም ሊዝ ማለት በጊዜ በተገደበ ውል መሠረት የከተማ ቦታ የመጠቀም መብት የሚገኝበት የመሬት ይዞታ ስሪት ነው፡፡

መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ሆኖ የመሬት አጠቃቀም በሕግ እንደሚወሰን በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 40 ተደንግጓል፡፡ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ ቁጥር 721/2004 እንደሚያትተው በመላ ሀገሪቱ በሁሉም ክፍላተ-ኢኮኖሚዎችና ክልሎች ያለው ሥራ መሬት የሚፈልግ፣ በመሬት ላይ የቆመ በመሆኑ ይህም ሁኔታ  ብቃት በተላበሰና ለፍላጎቱ ተገቢ የመሬት ሀብት አቅርቦት ምላሽ ሊሰጥ በሚችል አስተዳደር በአግባቡ መመራት ያለበት በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 2 (ሀ) መሰረት መሬት በሊዝ መሸጥ እንዲቻል ተደንግጓል፡፡

ሊዝ እና ባህር ዳር

የባህርዳር ከተማ የሊዝ አሰራር ችግር የተዳፈነ፣ የሰነድ አሰራሮችም ለማየት የተሰወረ መሆኑ ብዙዎችን ለጥርጣሬ የዳረገ ነው፡፡ እኔም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አንዳንድ ባለሙያዎች የሊዝ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እነሱም

“የባህርዳር የሊዝ ጨረታ አስገራሚ ነው፡፡ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ከወጡ ቦታዎች መካከል አንዱ አሸናፊ በካሬ 80,500 ብር በ2013 ዓ.ም. በግንቦት ወር በወጣው ጨረታ አቅርቧል። ይህም ማለት… ቦታው 100 ካሬሜትር ቢሆን አጠቃላይ የሊዝ ዋጋው 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ይሆናል ማለት ነው። ይህ ብር አሁን ባለው ወቅታዊ የባህርዳር የመሬት ዋጋ በሕጋዊ ሁኔታ ከግለሰቦች የመሬት ሽያጭ ዋጋ ሲሰላ ከ8 በላይ ባለ 100 ካሬ ሕጋዊ ቦታዎችን ይገዛል፡፡ በዚህ ባለው ዋጋ ያሸነፈው ተጫራች እጁ ላይ ካሽ ስለሌለውና የሊዝ ክፍያውን በረዥም ጊዜ መክፈል አስቦ ነው ብለን እንይና አንድ ስሌት ደግሞ እናስቀምጥ… ተጫራቹ እንዳሸነፈ መክፈል የሚጠበቅበት 10% ቅድሚያ ክፍያ ሲሰላ ከ800ሺ ብር በላይ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ አሁን ባለው ዋጋ እራሱ ሕጋዊ 100 ካሬሜትር ቦታ በርካሽ ከግለሰቦች ሊያስገዛ የሚችል ነው። ሌሎች ምሳሌዎችን በተጨማሪነት ማንሳትም እንችላለን… ይህን እንግዲህ ጥልቅ ምርመራ የሚጠይቅ ነው፡፡  ይህ በራሱ ከየትኛውም ወገን ቢሆን ልክ ያልሆነ ነገር እንዳለ የሚያሳይ ነገር አለ። ወይ ደግሞ እኛን አልገብቶንም” ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡

ይህንን የታዛቢዎች አስተያየት ይዘን በባህርዳር ከተማ የተካሄዱ የሊዝ ሽያጭ ጤናማነት መመርምረናል፡፡ በዚህም መሰረት በባህርዳር ከተማ ያለውን አሰራር ባደረግነው የሰነድ እና የሰው ምስክር ማጣራት ያገኘናቸው የሊዝ መሬት ማጭበርበሪያ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

በጨረታ አግባብ የተላለፉ የሊዝ ቦታዎች ጨረታ ባሸነፉበት ዋጋ መሰረት ውል አለመያዝ፣ ሊዙን ግለሰቡ ካሸነፈበት ዋጋ ዝቅ አድርጎ መያዝ፣  የመንግሥትን የሊዝ ገቢ ማሳጣት፣ውል አለመያዝ፣የሊዝ ፋይሎችን ወደ ገቢዎች ጽ/ቤት አለማስተላለፍ እና በማዘጋጃ ቤቱ መዝገብ ቤት እንዲቀር ማድረግ፣ምንም አይነት የማኔጅመንት ውሳኔ በሌለበት በአዲስ ውል ከመመሪያ ውጭ የእፎይታ ጊዜ በመስጠት መሬትን ማዘዋወር በ10 ዓመት የተቀመጠውን እስከ 50 ዓመታት የማራዘም ስራዎች በሰነዶች ውስጥ ይገኛሉ።

ሰነዶችን ማሳሳት፣ ያልከፈሉትን ገንዘብ እንደከፈሉ አድርጎ ማስረጃ መስጠት፣ በተመሳሳይ ተወዳዳሪዎች የሊዙን ውድድር በተቀራራቢ ዋጋ በመሙላት ፣ ተሸናፊዎች አሸናፊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ተሸናፊዎች እንዲያሸንፉ አሸናፊዎችን በመደለያ አልያም በሌሎች ምክንያቶች በማስወጣት ፣ ሊዙን በጨረታው ለተሸነፈ እና ዝቅተኛ ዋጋ ላቀረበ አካል ማስተላለፍ፣ ካሸነፈበት ቦታ በላይ የቦታ ስፋት በተጨማሪ አካቶ ካርታ መስጠት፣ የሊዝን ሰነድ መደበቅ፣ የሊዝ ክፍያን ተከታትሎ አለመሰብሰብ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

በእነዚህ እና ከዚህ በታች በማሳያ በምናቀርባቸው ውስብስብ የሊዝ ሸፍጦች ከተማ አስተዳደሩ ከ300 ሚልየን ብር መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ አጥቷል፡፡ በዚህም ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው አውለውታል፡፡

በሊዝ ከተላለፈ ቦታ ስፋት በላይ ጨምሮ መያዝ

በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በጨረታና በምደባ ሊዝ ከተላለፉት በላይ የቦታ ስፋት ተጨምሮ የተሰጣቸው ደንበኞች ላይ የዐማራ ክልል ዋና ኦዲተር ባደረገው አሰሳ በአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የቦታ ኮድ H11R29 የቦታ ስፋት 250 ካ.ሜ፤ ለካ.ሜ በብር 5,125.10 አሸንፎ ካርታ የተዘጋጀለት 320 ካ.ሜ ተብሎ ሲሆን ይኸው ቦታ በባለሙያ ሲለካ 69.11 ካ.ሜ ቦታ ተጨምሮ በመገኘቱ ይህም ባሸነፈበት ዋጋ ሲሰላ ብር 354,195.66 መንግሥትን ማሳጣቱን የ2013 ለክልሉ ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡

በሽማቦ ክ/ከተማ የቦታ ኮድ SH-06 የቦታ ስፋት 10,000፣ ለካ.ሜ የተሞላው ዋጋ ብር 1298.00 ተሰጥቶት የቦታው ስፋት በባለሙያ ሲለካ 2,226.94 ካ.ሜ ተጨማሪ ቦታ ተሰጥቶ በመገኘቱ ይህም ባሸነፈበት ዋጋ ሲሰላ 2,890,568.10 መንግሥትን አሳጥቷል፡፡

በህዳር 11 ክ/ከተማ የቦታ ኮድ H11C-54 የካ.ሜ ስፋት 3,000፣ ለካ.ሜ የተሞላው ዋጋ 8,154.99 አሸንፈው የቦታ ስፋቱ በባለሙያ ሲለካ 79.4 ካ.ሜ ተጨማሪ ቦታ ተሰጥቶ በመገኘቱ ይህም ባሸነፈበት ዋጋ ሲሰላ 647,506.20 ብር መንግሥትን አሳጥቷል፡፡ 

ለአንድ የገበያ ማዕከል አ/ማ በህዳር 11 የቦታ ኮድ H11C-53 የቦታ ስፋት 3000፣ ለካ.ሜ የተሞላው ዋጋ 6321.00 አሸንፈው የቦታ ስፋት በመሃንዲስና ባለሙያ ሲለካ 9.58 ካ.ሜ ተጨማሪ ቦታ በመሰጠቱ ይህም ባሸነፉበት ዋጋ ሲሰላ 60,555.18 ብር መንግሥት አጥቷል፡፡

የቦታ ኮድ 611 የቦታ ስፋት 3616፣ ለካ.ሜ የተሞላው ዋጋ ብር 294.00 በምደባ ተሰጥቷቸው የቦታው ስፋት በባለሙያ ሲለካ 1038.87 ካ.ሜ ቦታ ተጨማሪ በመሰጠቱ ይህም ባሸነፉበት ዋጋ ሲሰላ ብር 305,427.78 መንግሥትን ማግኘት የሚገባውን ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

በድምሩ ብር 4,258,252.92 የሊዝ ዋጋ ያልተከፈለበት በጨረታ ካሸነፈበት ወይም በምደባ ከተሰጣቸው መጠን በላይ ቦታ ወስደው እየተጠቀሙበት ተገኝተዋል፡፡ በነዚህ ከላይ በተዘረዘሩት ሁኔታች ምክንያት በተጠቀሱት ከተሞች የሊዝ ገቢው በአግባቡና በወቅቱ አለመሰብሰቡና የመንግሥት መሬትም እየባከነ ይገኛል፡፡ በዚህም የከተማውን የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዳይፈቱ አድርጓል፡፡

የሊዝ ቦታዎች ጨረታ ባሸነፉበት ዋጋ መሰረት ውል አለመያዝ 

በጨረታ አግባብ የተላለፉ የሊዝ ቦታዎች ጨረታ ባሸነፉበት ዋጋ መሰረት ውል አለመያዝ  በዐብክመ ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሊዝ ሂሣብ አስተዳደርን በተመለከተ፤ በጨረታ አግባብ የተላለፉ የሊዝ ቦታዎች ጨረታ ባሸነፉበት ዋጋ መሰረት ውል መያዙን በተመለከተ ኦዲት ሲደረግ ከዚህ በታች የተገለጹት ግኝቶች ተስተውለዋል፡፡ ባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያ ለአንድ ንግድና አፓርታማ አ/ማ አገልግሎት የሚውል ቦታ በሊዝ ጨረታ በባ/ዳር ከተማ በጣና ክፍለ ከተማ የቦታ መለያ ቁጥር TC-01 የቦታ ስፋት 3,816 ለካ.ሜ የሞላው ዋጋ ብር 8,001 ቅድመ ክፍያ ብር 3,053,181.60 ተቀንሶ ቀሪ ክፍያ ብር 27,478,634.40 መሆን ሲገባው ወደ ብር 18,158,422 ዝቅ ተደርጎ የሊዝ ውል የተያዘ በመሆኑ ልዩነት በማነስ ብር 9,320,212.40 ሲሆን ይህ ገንዘብ በቀጣይም እንዳይሰበሰብ ከውል ውጭ ተደርጐ ተገኝቷል፡፡

ለመኖሪያ አገልግሎት በጨረታ ቦታ ሲያገኙ የቦታ ስፋት 150 ካ.ሜ፤ ለካሬ ሜትር የተሞላው ዋጋ ብር 5001 የቦታው ጠቅላላ ዋጋ ብር 750,150 አሸንፈው ቅድሚያ ክፍያ ብር 75,015 ተቀንሶ ቀሪ ክፍያ ብር 675,135 ሲሆን ዓመታዊ ክፍያ ብር 13,502.70 በየዓመቱ ለ50 ዓመታት የሚከፈል ውል መያዝ ሲገባው ብር 12,502.70 የሚከፈል ተብሎ ውል ስለተያዘ ልዩነት 1000.00 ከዓመታዊ ክፍያ የሚቀር ሲሆን በ50 ዓመታት ብር 50,000.00 ሳይከፈል እንዲቀር ያደረገ ውል ተይዟል፡፡

ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውል የሊዝ ቦታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በቀድሞ ግንቦት 20 ክፍለ ከተማ ውል ተይዞ የነበረው ስመ ንብረቱ በ18/9/2009 ዓ.ም በሽያጭ ሲተላለፍ የቦታ መለያ ቁጥር G20R-143 የቦታ ስፋት 200 ካ.ሜ  የሊዝ ደንበኛ ጨረታ ያሸነፈበት ዋጋ ብር 4,000 ሆኖ እያለ ስመ ንብረት ዝውውር ሲደረግ ግን ወደ ብር 300 ዝቅ ተደርጎ በመተላለፉ ብር 702,000.00 የመንግሥትን የሊዝ ገቢ ያሳጣና ውል ሳይያዝ እና ፋይሉም ወደ ገቢዎች ጽ/ቤት ሳይተላለፍ ይገኛል፡፡

ለንግድ አገልግሎት የሚውል የሊዝ ቦታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በቀድሞ ግንቦት 20 ክፍለ ከተማ የቦታ መለያ ቁጥር G20C-14 እና G20C-15 የቦታ ስፋት 1010 እና 1020 ካሬ መሬት አሸናፊ ሆና ምንም አይነት የማኔጅመንት ውሳኔ በሌለበት በአዲስ ውል ከመመሪያ ውጭ የእፎይታ ጊዜ በመሰጠቱ ብር 622,508.92 በወቅቱ ሳይሰበስብ ይገኛል፡፡

በሁለተኛ ዙር የመኖሪያ አገልግሎት የሚውል ቦታን በጨረታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በቀድሞ ግንቦት 20 ክፍለ ከተማ የቦታ ኮድ ቁጥር G20R-291 የቦታ ስፋት 200 ካ.ሜ ለካ.ሜ 3,520 አሸናፊ ሆኖ እያለ በሽያጭ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ሲተላለፍ ወደ ብር 300 ዝቅ ተደርጐ ስለተያዘ ልዩነት ብር 579,600.00 በማነስ ውል ተይዞ በመገኘቱ የመንግሥትን ገቢ አሳጥቷል፡፡

የሊዝ ደንበኛ ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል H11R-7 መለያ ቁጥር የተሰጠው 200 ካ.ሜ ቦታ በ10 ዓመት ከፍሎ ለማጠናቀቅ በሊዝ ጨረታ አሸንፎ እያለ 10 ዓመት የሚለውን በመሰረዝና በፍሉድ በማስተካከል ወደ 50 ዓመት ከፍ በማድረግ ከሊዝ ደንበኛው በየዓመቱ ብር 45,090 መሰብሰብ ሲገባው ብር 9,018.00 እንዲከፍል በመድረጉ በልዩነት ብር 360,720.00 በ10 ዓመት ውስጥ እንዳይሰበስብና ባለፋት 7 ዓመታትም ብር 252,504 ገቢ ሆኖ ስራ ላይ እንዳይውል ሁኗል፡፡

ለንግድ አገልግሎት የሚውል የሊዝ ጨረታ ቦታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በቀድሞ ግንቦት 20 ክፍለ ከተማ የቦታ መለያ ቁጥር G20C-43A የቦታ ስፋት 1,470 ለካ.ሜ አንደኛ አሸናፊው የሞላው ዋጋ ብር 2,200 ሆኖ እያለ እሱን በመተው በ2ኛ አሸናፊ ዋጋ ብር 2,025.00 በመሰጠቱ ብር 257, 250.00 መንግሥት እንዲያጣ ተደርጓል፡፡

በሊዝ ጨረታ ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል ቦታን ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በቀድሞው ህዳር 11 ክፍለ ከተማ በቦታ ኮድ ቁጥር H11R -70 የቦታ ስፋት 250 እና የቦታ ኮድ ቁጥር H11R-71 የቦታ ስፋት 250 በ5 ዓመት ከፍሎ ለማጠናቀቅ ጨረታ አሸንፎ እያለ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት ህገ-ወጥ ማህተም እንደህጋዊ አስመስሎ በመጠቀም እና ውሉን እንደገና በአዲስ በመፃፍና የክፍያ ጊዜውን ወደ 50 ዓመት ከፍ በማድረግ ብር 934,668.00 በወቅቱ ሳይሰበሰብ ተገኝቷል፡፡

ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል 1273 መለያ ቁጥር የተሰጠውን 251 ካ.ሜ ቦታ በጥቅል ዋጋ ብር 597,380 ተጫርቶ አሸንፎ በቀን 08/04/2006 ዓ.ም ውል ይዞ የወሰደውን ቦታ የ2007 እና የ2008 ዓ.ም ዓመታዊ ክፍያ ብር 71,685.60 ሳይከፍል እንደከፈለ ተደርጎ ተቀንሶለት በብር 394,270.80 በ27/11/2012 ዓ.ም በሽያጭ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ የስመ ንብረት ዝውውር ተፈጽሞ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በ1ኛ ዙር ጨረታ በጥቅል ዋጋ ብር 732,000 አሸንፈው ቅድመ ክፍያ ብር 73,200 የከፈሉና ቀሪ ክፍያውን በ20 ዓመት ውስጥ በየዓመቱ ብር 32,940 እየከፈሉ ለማጠናቀቅ በቀን፡- 30/03/2006 ዓ.ም ውል ገብተው የያዙትን ኮድ RT-07 የሆነ 200 ካ.ሜ ቦታ በ2012 በጀት ዓመት ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በሽያጭ ስመ ንብረት ዝውውር ሲፈጽሙ የ2007 እና 2008 ዓ.ም የ2 ዓመት ዓመታዊ የሊዝ ክፍያ ብር 65,880 ሳይከፈል እንደተከፈለ ተደርጎ ተቀንሶላት ከተማ ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያው ከ2007-2012 ዓ.ም ያለው የ6 ዓመት ሙሉ ክፍያ ብር 197,640 እንደተከፈለ ተደርጎ በ14 ዓመት ከፍሎ እንዲያጠናቅቅ ብር 461,160 ቀሪ ክፍያ ላይ ብቻ ከገዥው ጋር በቀን 30/4/2012 ዓ.ም ውል ይዞ ተፈራርሟል፡፡

የመኖሪያ አገልግሎት የሚውል ቦታን በጨረታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በቀድሞው የግንቦት 20 ክፍለ ከተማ የቦታ ኮድ ቁጥር G20R-293 የቦታ ስፋት 200 ካ.ሜ አንደኛው አሸናፊ ብር 3600 የሞላውን በመሰረዝ እና ሁለተኛው ተጫራች በብር 3321 የሞላውን እንደ አንደኛ አሸናፊ በማድረግ ውል በመያዙ ብር 55,800.00 መንግሥት አጥቷል፡፡  

ሌላው ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በጣና ክፍለ ከተማ  የቦታ ኮድ 1271 የቦታ ስፋት 251 ካ.ሜ የ2 አመት ክፍያ ሳይከፈል እንደተከፈለ ተደርጐ ተቀንሶለት ስመ ንብረት ዝውውር ሲደረግ ብር 41,610.78 መንግሥት እንዲያጣ ተደርጓል፡፡

በሊዝ ጨረታ ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል  ቦታን ለአንድ የሊዝ ደንበኛ የቀድሞ ግንቦት 20 ክፍለ ከተማ በቦታ ኮድ ቁጥር G20R -367 የቦታ ስፋት 200 ካ.ሜ በ18 ዓመት ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ በጥቅል በብር 500,200 አሸንፈው እያለ ጊዜ ያለፈበት ፎርጅድ ማህተም በመጠቀም እና ውሉን እንደገና በመጻፍ ወደ 50 አመት ከፍ በመደረጉ ብር 256,105.98 መንግሥት በወቅቱ ማግኘት ያለበትን ጥቅም አሳጥቷል፡፡ በድምሩ በባህርዳር ከተማ ብር 13,927,690.88  ከተገቢው መጠን በታች (በማነስ) ውል የተያዘበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡በሊዝ ቦታ ተሽጦ ለገቢዎች ጽ/ቤት ባልተላለፉ የውል ሰነዶች ምክንያት ያልተሰበሰበ የሊዝ ሂሳብ በተመለከተ ኦዲት ሲደረግ ከዚህ በታች የተገለጹት ችግሮች ተስተውለዋል፡፡

በከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት የተፈፀመ የገቢ ስወራ

ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል የሊዝ ጨረታ ቦታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በህዳር 11 ክፍለ ከተማ የቦታ መለያ ቁጥር H11R-24 ስፋት 200 ለካ.ሜ የተሞላው ዋጋ ብር 10,950 ቅድመ ክፍያ ብር 219,000.00 ተከፍሎ ቀሪ ክፍያ ብር 1,971,000.00 የያዘ የደንበኛው የሊዝ ውል ወደ ገቢዎች ጽ/ቤት ከ4 ዓመት በላይ ሳይተላለፍ መገኘቱና መንግሥት በወቅቱ ማግኘት የነበረበትን ገቢ አሳጥቷል፡፡

ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል የቦታ ኮድ G20R-13 ስፋቱ 250 ካ.ሜ ቦታ በጥቅል ዋጋ ብር 1,505,000 በጨረታ አሸንፎና ቅድመ ክፍያ 10% ብር 150,500 በመክፈል ውል ይዞ እያለ ብር 1,354,500.00 የያዘ የውል ሰነድ ከ5 ዓመት በላይ የውሉን አንድ ኮፒ ለገቢዎች ጽ/ቤት ሳይተላለፍና ገቢውም ለመንግሥት ሳይከፈል ባህርዳር ከተማ በድምሩ ብር 3,325,500.00 የያዘ የውል ሰነድ መዝገብ ቤት ተቆልፎበት ይገኛል፡፡

ፋይሎችን መሰወር /ማጥፋት/ ባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያ

2010/2011 በጀት ዓመት ኦዲት በአጠቃላይ ብር 1,383,413,234.77 የያዘ 173 የመኖሪያ ቤትና ብር 3,104,377,478.12 የያዘ 120 የንግድ ድርጅት በጥቅሉ ብር 4,487,790,712.89 ብዛት 293  የሊዝ ደንበኞች የውል ሰነድ ለኦዲት ስራ እንዲቀርብ በኦዲት ቡድኑ እና በዋና ኦዲተሮች ጭምር በተደጋጋሚ ተጠይቆ በኦዲቱ ወቅት ተፈልጎ ሊቀርብ አልቻለም፡፡

በዚህ መነሻ ለኦዲት ስራ ተፈልገው ሊቀርቡ ያልቻሉ የሊዝ ፋይሎችን አስመለክቶ ለሚመለከታቸው የፍትህ አካላት እርምጃ እንዲወስዱበት ሪፖርት ከተላለፈ በኋላ ተጠያቂነቱ ሲመጣ ኦዲተሮች እንደገና መጥተው ይዩልን የሚል አቤቱታ በማቅረባቸው በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ በኩል የጽሁፍ ጥያቄው በመቅረቡ እንደገና በ2012 በጀት ዓመት ድጋሜ ኦዲት ሲደርግ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከ2005-2010 ዓ.ም በሊዝ አግባብ የተላለፉ ቦታዎች የመኖሪያ ብዛት 12 በገንዘብ መጠን ብር 21,519,514.00 የያዘ የደንበኞች የቦታ ሊዝ ፋይል ለኦዲት ስራ ተፈልጎ ሊቀርብ አልቻለም፡፡

በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ከ2005-2010 ዓ.ም በሊዝ አግባብ የተላለፉ ቦታዎችን ለኦዲት ስራ ተፈልገው ሊቀርቡ ያልቻሉ ፋይሎች የመኖሪያ ብዛት 45 ሲሆኑ የያዙት የገንዘብ መጠን ብር 119,224,881.40፤ ሶስት ድርጅቶች  በብር 63,346,413.20 የገንዘብ መጠን እና ስመ-ንብረት ዝውውር በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያ ተፈጸሞላቸው አመታዊ የሊዝ ክፍያ መክፈላቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በባህርዳር ከተማ ገቢዎች መምሪያ ላይ ውላቸው ያልተገኙ የሊዝ ፋይሎች 29 የመኖሪያ ቤት በብር 33,456,895.24 የገንዘብ መጠን በድምሩ በባህርዳር ገቢዎች መምሪያ 77 ፋይሎች በብር 216,028,189.84 የከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ በፍትህ አካላት ጥያቄ ተፈልጎ ሊቀርብ አልቻለም፡፡ በአጠቃላይ 89 ፋይል በብር 237,547,703.84 በገንዘብ መሰወሩ ተረጋግጧል፡፡

የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና/ሲፒኦ/ በሕግ አግባብ አለመውረስ

በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከ2005-2010 በጀት ዓመት በናሙና ለኦዲት ከተመረጡት ውስጥ አንደኛ የሊዝ ጨረታ አሸናፊ ሆነው የሊዝ ውሉን ሳይዋዋሉ ከቀረ የጨረታ አሸናፊ መሆኑ ይሰረዛል፡፡ለጨረታ ማስከበሪያ ተይዞ የነበረው ገንዘብም ለከ/አስ/ፋይ/ጽ/ቤት ገቢ እንደሚሆን የከተማ ቦታን በሊዝ ለመፍቀድ የወጣ የአፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1/2005 አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 4 የሚደነግግ ሲሆን አንደኛ የሊዝ ጨረታ አሸናፊ ከሆኑት ውስጥ የ9 ደንበኞች ብር 41,764.20 የያዘ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ሲፒኦቸው አልተወረሰም፡፡  

ከፍያን ሆነ ብሎ አለማስከፈል

የከተማ ቦታን በሊዝ ስለ መያዝ የወጣ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 6 መሰረት የሊዝ ኪራይ ክፍያውን ለመክፈል በሚገባው የጊዜ ገደብ ውሰጥ በየዓመቱ ክፍያውን ባለመክፈሉ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በየደረጃው የሚሰጥ ሆኖ የ3 ዓመት ውዝፍ ካለበት ከ4ኛው ዓመት ጀምሮ አግባብ ያለው አካል ንብረቱን ይዞ በመሸጥ ለውዝፍ እዳው መክፈያ ያውላል የሚል ቢሆንም ተገቢውን ክፍያ ተከታትሎ አለማስከፈል ችግሮች ተስተውለዋል፡፡

ባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያ ከ1989-2011 ባሉ 22 በጀት ዓመታት በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ላይ ዓመታዊ የሊዝ ክፍያ ያልከፈሉት የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በየደረጃው ሊሰጣቸው የሚገባ ከ1-3 ዓመት የሆናቸው ደንበኞች ብዛት 611 ሲሆኑ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ሂሳብ ብር 51,196,697.61 እንዲሁም ቦታቸውን ሊነጠቁ የሚገባ ከ4 ዓመት በላይ የሆናቸው ደንበኞች ብዛት 381 ሲሆን ያልተሰበሰበ ውዝፍ ሂሳብ ብር 57,609,364.41 በድምሩ 108,806,062.02 በጽ/ቤቱ ውዝፍ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

በእነዚህ ግኝቶች ላይ አሰተያየታቸውን ያቀረቡት የዐማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር የሽመቤት ደምሴ (ዶክተር) የከተማ መሬት ሊዝ አፈፃፀም በርካታ ችግሮች ያሉበት እና የሚመለከታቸው አካላት ያላቸውን መሬት ቆጥረው ባለመያዛቸው መሬት አንዱ የሙስና ምንጭ ነው ብለዋል፡፡ አንዳንድ ተቋማት በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት ፈቃደኛ አለመሆንና መረጃ የመደበቅ ችግር ይታይባቸዋል ሲሉ ያሉትን ችግሮች ቢሯቸው እንደሚገነዘበው እና ይህንን ችግር ለመቅረፍ ችግሩን ከማሳወቅ ያለፈ ስልጣን የለንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አስተያየት