“ሁለቱ ጓደኞቼ ሞቱ እኔ ተርፌ ወጣሁ”
አብዱራህማን ኢብራሂም (በወዳጆቹ አጠራር አብዱ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እንጀራ ከጠራቸው በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች መሀል አንዱ ነው። አብዱራህማን የሁመራ ተወላጅ ሲሆን ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባትም ነው። በዞኑ ጉባ ወረዳ በእርሻ ልማት ስራ ላይ በተሰማራ ድርጅት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር።
አብዱራህማን ከማንኩሽ ከተማ 50 ኪ.ሜ ገደማ በሚርቀው አልምሃል በተባለ ስፍራ መዋዕለ-ነዋይ በፈሰሰበት አዲስ ዓለም እርሻ ልማት ድርጅት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተቀጥሮ ሰርቷል። ድርጅቱ ጥጥ፣ ሰሊጥና ማሽላ አምራች ነው። በድርጅቱ አብዱራህማን ከኬሚካል ረጪነት ጀምሮ ሹፌርና ጸሀፊ በመሆን ሰርቷል።
በአንድ የምርት ዘመን በእሱ አጠራር "መኸር እስከሚሸከፍ" (ከስምንት እስከ ዘጠኝ ወር) ሁሉንም ስራዎች ሰርቶ ሁለት መቶ ሽህ ብር ገቢ ያገኛል። ይህም ማለት በወር ከ22 ሽህ ብር እስከ 25 ሽህ ብር ገቢ ነበረው። አብዱራህማን በገቢው ቤተሰቡን ከማስተዳደር ባለፈ ባለቤቱን ዩኒቨርስቲ ያስተምር እንደነበር ይናገራል።
በየጊዜው በታጣቂዎች የሚሰነሩ ጥቃቶችና ዘረፋዎች ግን ለስራቸው መስተጓጎልን፤ ለደህንነታቸው ደግሞ ስጋት ሆኖ መቆየቱን አብዱራህማን ያስታውሳል።
“ብዙ ቀን ይመጣሉ። ያው እየተደበቅን እናሳልፍ ነበር። ፍየሎች ነበሩን ተዘርፈዋል፤ ከብቶችም ተዘርፈዋል” ይላል። ሆኖም በወርሃ የካቲት 2012 ዓ.ም. በጀርባቸው የለበሱትን ልብስ ብቻ ይዘው እግሬ አውጭኝ ያሉበትን ጊዜ ያስታውሳል። “በዚህ ይሞታል፤ በዚያ ይሞታል። ንብረታችንን ለማውጣት ቆይተን ነበር። 26 የሚሆኑ ሲቪሎች [ንጹሀን] ሞተው እኔም ሬሳ [አሽከሪዬን] ለማምጣት መከላከያዎችን ይዤ ሄጄ ነበር። ሦስት መኪና ሆነን ሄደን ቀብረን ስንመለስ ሁለቱ መኪና የያዙ ጓደኞቼ እነሱ ሞቱ እኔ ተርፌ ወጣሁ። ብዙ መከላከያም ወጣ። ከዛ በኋላ ሁሉን ነገር ጥዬ ወጣሁ [ከመተከል]። የሚያሰራኝን ባለሃብትም ሆነ የእኔን ምንም ንብረት አላወጣንም። የለበስነውን ልብስ ብቻ ነው ይዘን የወጣነው።”
ወደ ትውልድ አገሩ ለመመለስ እንኳን መቸገሩን የሚናገሩው አብዱራህማን እስከ ግልገል በለስ ድረስ (የመተከል ዞን ዋና ከተማ) በጓደኞቹ እርዳታ መምጣት እንደቻለ ይናገራል። ሁመራ ለመድረስ “ድርጅቱን ገንዘብ ብንጠይቅም ንብረቱ ስላልወጣለት ፊት አልሰጠንም” ይላል ሲያስታውስ።
የግጭቱ ዳፋ በአብዱራህማንና ቤተሰቡ ላይ አርፏል። ስራ ከመፍታት ባለፈ ባለቤቱ የሁለተኛ ዓመት ትምህርቷን በክፍያ ምክንያት አቋርጣለች። ከወራት ስራ መፍታት በኋላ ዳግም በትውልድ አካባቢው ማይካድራ ሁመራ ስራ ቢያገኝም ገቢው እንደቀደመው አልሆነለትም። አብዱራህማን ግን አያማርርም። ከእጅ ወደ አፍ መኖርን እንደ እድለኛነትም ይመለከተዋል።
አዲስ ዓለም እርሻ ልማት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በጉባ ወረዳ ስራ የጀመረ ድርጅት ነው። መሀመድ ያሲን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ነው። ድርጅቱ በሁለት ቀበሌዎች አንድ ሺህ የሚጠጋ መሬት ላይ ያለማል። ከ300 በላይ ሰራተኞች (ጊዜያዊ ሰራተኞችን ጨምሮ) ነበሩት። ስራ አስኪያጁ ምን ምን እንደሚያመርቱ ሲጠየቅ “ሁሉም ይመረታል። መሬቱ የሰጠሽውን ሁሉ ይቀበላል” በማለት አካባቢው ምርታማ መሆኑን ይገልጻል። ጥጥ በዚያው በመተከል ዞን ተዳምጦ አዲስ አበባና ባህር ዳር ላሉ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ይሸጣል። አንድ ኩንታል የተዳመጠ ጥጥ 13 ሽህ ብር ይሸጣል። ካልተዳመጠ ደግሞ እስከ ስድስት ሽህ ብር ድረስ ይሸጣል።
ሆኖም አዲስ ዓለም እርሻ ልማት መተከልን በናጠው ጥቃት ዶግ አመድ ከሆኑ አሊያም ለቀው ለመውጣት ከተገደዱት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ድርጅቶች (ኢንቨስትመንቶች) አንዱ ነው።
ድርጅቱ በመባቻው ሰሞን ጥጥ በሄክታር እስከ 20 ኩንታል ማምረት ጀምሮ ነበር። አንድ ሺህ 250 ኩንታል ጥጥ እንደሰበሰቡ ጥቃቱ መጀመሩን መሀመድ ያስታውሳል። የተለቀመ አንድ ሺህ ኩንታልና ያልተለቀመ ምርታቸውን ከነ ንብረቱ (ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት) ጥለው ወጥተዋል።
“መንገድ ላይ አምስት ተሳቢ ጭነን እየሄድን፤ አንዱ የእኛ ነበር። ስንሄድ ተጠራቅመን ነው የምንሄደው። ግርግር ስለነበር በተደራጀ መልኩ ነው የምንሄደው። መከላከያም ከእኛ ጋር ይሄዳል። ከዛ መንገድ ላይ [ታጣቂዎች] ጠበቁንና ተኩስ ከፈቱብን። ሰዎች ሲገደሉ እኛ መኪናውን ጥለን አመለጥን። ሲያቃጥሉት እያየን ነበር። ከዛ በኋላ አልተመለስንም” ይላል።
በመተከል በተሰነዘረ ጥቃት አንድ ሰራተኛቸው እንደተገደለ መሀመድ ያሲን ተናግሯል። “እየተተኮሰብን ነው፤ አግዙን ብለን መከላከያ ይዘው እየመጡ እያሉ ነበር ጥቃት የደረሰባቸው” ይላል መሀመድ።
ንብረታቸው ይኑር አይኑር እርግጠኛ ባይሆኑም፤ በተለይ መኪኖቹ እንደሚዘረፉ ጥርጥር ለውም ይላል። “ምን አልባት ጥጡን ካላቃጠሉት እሱ ይኖራል እንጂ፤ ሌላው አይታሰብም” ይላል።
ደርጅቱ በጥቃቱ እስከ 35 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶበታል።
ግጭትና መዋዕለ-ነዋይ፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ
መተከል ዞን በተለይም ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበት ዞን ነው። ዞኑ “ካሽ ክሮፕ” በሚባለው ዘርፍ በቀላሉ ገንዘብ የሚያስገኙ ተክሎች የሚመረቱበት ሲሆን፤ አገር ውስጥም ውጭም የሚሸጡ እንደ ሰሊጥና ጥጥ የመሰሉ ምርቶች ከፍተኛ ገቢ ያስገኛሉ። የመሬቱ ለምነትና ምቹነት (በትናንሽ ማሳዎችም ጭምር) ከፍተኛ ቴክኖሎጂን ሳይጠይቅ የአገር ውስጥ መዋዕለ-ነዋይ አፍሳሾችን መሳብ ችሏል።
ጉባ፣ ዳንጉር፣ ወንበራ፣ ማንዱራና ቡለን ወረዳዎች ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የተጀመሩባቸው የዞኑ አካባቢዎች ናቸው። ሆኖም ከ2010 ዓ.ም. መባቻ ጀምሮ በመተከል ዞን በሁሉም አካባቢ በታጣቂዎች ሚሰነዘሩ ጥቃቶች ከባቢውን አውኮታል። ይህም ካደረሰው ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ ባሻገር ለመዋዕለ-ነዋይ ጠንቅ ሆኗል።
መዋዕለ-ነዋይና ሰላም መሳ ለመሳ የሚሄዱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ባለሞያዎች ይናገራሉ። የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪ የሆኑት ስሜነህ በሴ (ዶ/ር) ግጭት በምጣኔ-ሀብት እድገት፣ መዋዕለ-ነዋይና የዜጎች ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው ይላሉ። ጦርነቶች፣ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሲኖሩ መዋዕለ-ነዋይ አፍሳሾችን ከማባረር ባለፈ አዲስ ባለሀብቶችን መገርገር፣ ምርት ቢመረት እንኳ ሰንሰለቱ ስለሚሰበር ማከፋፈልን ይፈትናልም ይላሉ።
“ኢንቨስትመንት በአጠቃላይ መተማመንን ይፈልጋል። በተለይ በግለሰብ ደረጃ ኢንቨስት የሚደረጉ፣ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ የዋጋ ንረትን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶች [ሰለም ከሌለ] አይችሉም። ስለዚህ የምርት አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ እጥረት ይገጥማል፣ ቁጠባ አይኖርም፣ በሂደት ደግሞ ኢንቨስትመንት ላይ ጫናውን ያሳርፋል። ኢንመቨስትምነት ደግሞ ተጽዕኖ ገጠመው ማለት የዜጎች ደህንነትና የመንግስት ምጣኔ-ሀብት አደጋ ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው።
ለውጭ ኢንቨስትመንትን ደግሞ አካባቢው ተመራጭ እንዳይሆን ያደርጋል። ሀገራችን ሰላም በነበረችበት ወቅት ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይገባ ነበር። ስለዚህ ጦርነት አለ ማለት የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል። እና [ሰላምና ኢንቨስትመንት] ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው” ሲሉ ይገልጻሉ።
በመተከል ዞን 200 የሚደርሱ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ፕሮጀክቶች ነበሩ። እነዚህ ፕሮጀክቶች 115 ሺህ 552 ሄክታር መሬት የተረከቡና ከሰባቱ የዞኑ ወረዳዎች በአምስቱ የተሰማሩ ናቸው። ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ካፒታልም አስመዝግበዋል። 34 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሰተው “የጸጥታ ችግር” በደረሰባቸው ጉዳት ሰራተኞቻቸውን በትነው እንደ ጉም ተነዋል።
ከዚህ ከፍ ሲልም በቁጥር ይህ ነው ባይባልም ሰራተኞችና ባለሀብቶች ተገድለዋል። “አብዛኞቹ [ፕሮጀክቶች] የሰው ህይወት ያለፈባቸው ናቸው። ሰራተኛ ያለቀባቸው። ባለሀብቶችም የሞቱት ብዙ ናቸው” ይላሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት የድጋፍ ባለሙያ አቶ ደረጄ አበበ።
ከክልሉ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ ባገኘነው መረጃ በግጭቱ ምክንያት 194ቱ የዞኑ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመዋል።
የተመረተ ምርት መቃጠል፣ ዘረፋና ሙሉ በሙሉ መውደም፣ ማሽኖች ማቃጠል፣ መዘረፍና ማውደም፣ የካምፖች ሙሉ በሙሉ ውደመት፣ የተመረተው ምርትም እንደተጫነ ማቃጠልና በአውድማ ላይ እያለ ማቃጠልና መዘረፍ የመሰሉ ከባድ ጉዳቶች ደርሰዋል።
በዚህም ባለሀብቶች የተበደሩትን ብድር መክፈል አለመቻልና እንደ ሊዝ ክፍያና ግብር ያሉ የመንግስት እዳዎችን አለመክፈል እንዲሁም ለሎች ማህበራዊና ምጣኔ-ሀብታዊ ችግር ደርሶባቸዋል።
ሰለባው የመንግስት ካዝና
ባለፉት አራት ዓመታት “የእድገት ኮሪደር” በሚባለው መተከል ዞን የተከሰተው አለመረጋጋት ጫና ከማህበረሰቡ ጀምሮ እስከ መንግስት ድረስ ማረፉ ይነገራል። ለአካባቢው ምጣኔ-ሀብት አበርክቶ የነበራቸው መዋዕለ-ነዋዮች ደጃቸውን መዝጋት ለማህበረሰቡ እንደ የስራ ዕድልና ትምህርት የመሰሉ ግልጋሎቶችን ከማስተጓጎሉ ባለፈ የመንግስትን ገቢ ማስቀረቱን የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪው ያነሳሉ።
በመተከል ዞን የተፈጠረው አለመረጋጋትና ጥቃት የዞኑን ካዝና ባዶ አስቀርቷል። የዞኑ ምጣኔ-ሀብት ላይ ቀላል የማይባል ቀውስ ማሳረፉንም አስተዳደሩ ገልጿል። የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ምንም እንኳ አካባቢው መዋዕለ-ነዋይን ለማፍሰስ የተመቻቸና ምርታማ ቢሆንም ጥቃቱ አላባራ ማለቱ ገቢ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይናገራሉ።
“ይሄ ዞን ገቢ ከእቅድ በላይ በመሰብሰብ ነበር የሚታወቀው። ምክንያቱም የኛ መሬት ለማምረት ማዳበሪያ አይጠይቅም። ይህ ችግር በመፈጠሩ ግን በሙሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች ቆመዋል። ኢንቨስተሮች ወጥተዋል። ኢንቨስተር ካልሰራ ገቢ የለንም። እንዴት ነው ግብር ሊከፍሉ የሚችሉት? ምንስ ላይ ነው የሚገብሩት?” ይላሉ።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በደረሰው የመዋዕለ-ነዋይ ውድመትና ኪሳራ ይስማማል። በተፈጥሮ ሀብት፣ በመሰረተ ልማት፣ በስፋትና በሌሎች ለኢንቨስትመንት በሚያስፈልጉ ግብዓቶች መሟላት ምክንያት ክልሉ ለመተከል ዞን የተለየ ቦታ አለው። ለባለሀብቶች ክልሉ ቅድሚያ የሚያስተዋውቀው አካባቢም ነው። በተለይም ጉባና ዳንጉር ወረዳዎች ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ያሉባቸው ናቸው።
የክልሉ ከፍተኛው የግብርና መዋዕለ-ነዋይ የፈሰሰው በመተከል ዞን ነው። በተለይም ከአንድ ሺህ እስከ 10 ሺህ ሄክታር መሬት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ወደ መተከል ያመራሉ።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬት በፌዴራል መንግስት መተዳደር (እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ) ለሀሰተኛ ባለሀብቶችና ለልማት ባንክ ብድር ብልሽት ቁልፍ ሚና ስለመጫወቱ የክልሉ መንግስት ያምናል። አብዛኞቹም በመተከል ዞን መሬት የወሰዱ ናቸው። ወደ ስራ የገቡ እውነተኛ ባለሀብቶች ደግሞ የጥቃቶች ኢላማና ሰለባ ሆነው ዛሬ መተከልን ያለ አልሚ አስቀርተውታል።
የክልሉ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት የድጋፍ ባለሞያው ደረጄ አበበ የመተከል የጸጥታ ችግር ጦስ ለማህበረሰቡ፣ ለሰራተኛውና ለባለሀብቱ ብቻ የተረፈ አይደለም ይላሉ። ክልሉም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ይላሉ። ወጣቶችን በመቅጠር፣ ከአካባቢው ጥሬ እቃ በመግዛትና ለመንግስት የገቢ ምንጭ በመሆን የአካባቢው ምጣኔ-ሀብት አንቀሳቃሽ ናቸው ይላሉ።
“መንግስት በሁለት መልኩ ተጎድቷል። የመሬት ሊዝ ኪራይ፣ የምርት ገቢ ግብርን የመሰሉ ገቢዎችን ከማግኘት አንጻር ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ስለዚህ ክልሉ በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ማግኘት የነበረበትን ገቢ አላገኘም። የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር የምንላቸውን እንኳ ወደ ጎን አድርገን ማግኘት የነበረበትን ገቢ አላገኘም። ሌላው ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ሲወጡ ከባንክ የተበደሩትን መክፈል አልቻሉም። ስለዚህ ብዙ ጉዳት ደርሷል” በማለት ኪሳራው ዙሪያ መለስ መሆኑን ይናገራሉ።
የክልሉ መንግስት በአጠቃላይ እስካሁን የደረሰበትን ኪሳራ በአሀዝ ለይቶ ይህ ነው ባይልም፤ በመተከል ዞን ከመሬት ሊዝ ኪራይ ግን 70 ሚሊዮን ብር ማጣቱን ተናግሯል።
የደረሰው የመንግስት የገቢ እጦት ላይ የሚስማሙት የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪው ስሜነህ በሴ (ዶ/ር) ፤ ክልሉ ለአገር ካለው አበርክቶ አንጻር ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶታል ብዬ አላምንም ይላሉ።
ካሳና የወደፊት መፍትሄዎች
አካባቢው ሰላም ከሆነ አብዱራህማንና መሀመድ ወደ መተከል ተመልሰው ስራቸውን መቀጠል ይሻሉ። ባለሀብቶችም ይህን ቢመኙም ለደረሰባቸው ውድመትና ጉዳት ተመጣጣኝ ካሳን ግን አጥብቀው ይፈልጋሉ። አዲስ ዓለም እርሻ ልማት የደረሰበትን ውድመት በምስል አስደግፎ ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ማስገባቱን ተናግሯል።
ጉዳቱን ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዳሳወቀ የሚናገረው የክልል መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ፤ ጉዳት የደረሰባቸውን ድርጅቶች አጣርቶ ካሳ ለመክፈል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቋል።
“የሰላም ሁኔታው ባለመረጋጋቱ ይሄ ነው ማለት አይቻልም” በማለት የወደፊት ውጥኖች አለመኖራቸውን ጠቁሟል።
ከመተከል ቀውስ በኋላ የአካባቢውን መዋዕለ-ነዋይ ለመመለስና የማካካሻ መርሃ-ግብሮች እንዴት ይካሄዱ?
የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪው ስሜነህ (ዶ/ር) በመጀመሪያም አሁንም መሆን ያለበት አካባቢውን ወደ ሰላም መመለስ ነው ይላሉ። በመተከል ከግጭት በኋላ የማገገሚያ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
“ሰላምን በአስተዳደራዊና በፖለቲካዊ በማረጋገጥ፤ መንግስት የተቋም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ አሁን የተፈጠረውን [አንጻራዊ] ሰላም በቀዳሚነት ማስቀጠል አለበት። የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነት ወደ ቀያቸው በመመለስ ማቋቋም። ሁለተኛ ኢንቨስተሮች በሚሊዮኖች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ችግሩ አገራዊ በመሆኑ ለእነዚህ ኢንቨስተሮች ለእያንዳንዳቸው መንግስት ካሳ ይክፈል የሚል እምነት የለኝም። ይደረግ ቢባልም መፍትሄ የሚያስገኝ አይመስለኝም። ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ግን የግድ ነው። አንደኛ ወደ ነበሩበት ቦታ ለመመለስ ድጋፍ ያስፈልጋል። የተበደሩትን ብድር ጊዜ ማራዘም ሊሆን ይችላል፣ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማመቻቸት ሊሆን ይችላል፣ የብድር ምጣኔውን መቀነስ ሊሆን ይችላል፣ ተጨማሪ ብድርን ማመቻቸት ሊሆን ይችላል፣ ግብርን መቀነስ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መንግስት ኢንቨስተሮችን በተገቢው መንገድ ለይቶ እንደ የጉዳት መጠናቸው ድጋፍ ማድረግ ነው። በአጠቃላይ ከግጭት በኋላ የማገገሚያ እርምጃ የምንላቸውን መተግበር። የባለሀብቶችን መተማመንን መመለስ ያስፈልጋል። መተማመን ካለ፤ ሰላሙ ከተረጋገጠ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻም ሳይሆኑ የውጮቹም ይገባሉ። አዋጭ ስለሆነ ለራሳቸው ሲሉ ይመጣሉ” በማለት የመፍትሄ ሀሳቦችን ይጠቁማሉ።
ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎች መኖሪያ የሆነው የመተከል ዞን፤ ለማዕድንና ለእርሻ ልማት እምቅ አቅም አለው። መተከል በመልከዓ-ምድር፣ በተፈጥሮ ጸጋና በአየር ንብረት መታደሏ ተመራጭ አድርጓታል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመተከል ላለፉት አስር ዓመታት እየተገነባ ነው።