ታህሣሥ 20 ፣ 2015

የባህርዳር እና ጎንደር አካባቢ አስመጪ እና ላኪዎች የወረታ ደረቅ ወደብን እየተጠቀሙ እንዳልሆነ ተገለጸ

City: Bahir Darምጣኔ ሃብትወቅታዊ ጉዳዮችንግድ

የወረታ ደረቅ ወደብ አገልግሎት ምረቃ ስነስርዓት ወቅት የሁለተኛው ዙር ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር በወቅቱ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የሁለተኛው ዙር ግንባታ አለመጀመሩን አዲስ ዘይቤ ተመልክታለች

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የባህርዳር እና ጎንደር አካባቢ አስመጪ እና ላኪዎች የወረታ ደረቅ ወደብን እየተጠቀሙ እንዳልሆነ ተገለጸ

የወረታ ደረቅ ወደብ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ በ2012 ዓ.ም ነበር ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው።

ይህ ወደብ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ከመደረጉ በፊት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ አስመጪና ላኪዎች የሚጠቀሙት የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብን ብቻ ነበር። የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብና ተርሚናል በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ አስመጪና ላኪዎችን ለማስተናገድ በቂ ባለመሆኑ በክልሉ ተጨማሪ አማራጭ እንዲኖር ጥያቄ መነሳቱን ተከትሎም የወረታ ደረቅ ወደብ ሊገነባ ችሏል።

የወረታ ደረቅ ወደብ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ይታይ የነበረውን እንግልት እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ይባክን የነበረውን ጊዜ እና ገንዘብ በእጅጉ እንደሚቀንስም ታምኖበትም ነበር። ይሁን እንጂ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ያልቻለው ይህ ወደብ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ አገልግሎቱ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ቆይቶ አሁን ዳግም ወደ አገልግሎት ተመልሷል።

ከጅቡቲ-ወረታ ያለው የመንገድ ርቀት ወደ ቃሊቲ እና ሞጆ ካለው ርቀት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ቢሆንም የወረታ ደረቅ ወደብ በሚጠበቀው እና በታቀደው ልክ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አዲስ ዘይቤ ባደረገችው ምልከታ አረጋግጣለች።

በባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት የወረታ ደረቅ ወደብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ተስፋዬ አያሌው “የወረታ ደረቅ ወደብ በሰሜኑ ጦርነት አቁሞት የነበረውን አገልግሎት ዳግም ጀምሯል” ብለዋል። የአገልግሎቱ መጀመር ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ አስመጪና ላኪዎች እንዲሁም ለክልሉ መንግሥት ንግድ እና ኢኮኖሚ መሻሻል ጥቅም እንዳለው ስራ አስኪያጁ ይገልፃሉ። 

ደረቅ ወደቡ በአሁኑ ሰዓት በመነቃቃት ላይ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ 200 ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮችን እያስተናገደ እንደሆነ ገልፀው ይህም በደረቅ ወደቡ ከፍተኛው ቁጥር ነው ብለዋል።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ በወደቡ የተሟላ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አሠራሮች ተዘርግተውለታል። ለአብነትም አስመጭና ላኪዎች ሁሉንም አገልግሎት ከደረቅ ወደቡ ሳይወጡ ማጠናቀቅ እንዲችሉ ታሳቢ የተደረጉ የባንክ እና የጤና ተቋማት አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትም በእዛው ይገኛሉ፡፡

ነገር ግን መረጃዎች እንደሚያሳዩት የወረታ ደረቅ ወደብ አሁን ባለው አቅም ተርሚናሉ 973 ኮንቴይነሮችን መሬት ላይ በማሳረፍ፣ ወደላይ በመደርደር ደግሞ 1 ሺህ 950 ኮንቴይነሮችን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ አቅም ቢኖረውም ደረቅ ወደቡ ከአቅም በታች እያስተናገደ መሆኑን ያሳያል ተብሏል።

በወረታ ደረቅ ወደብ ጉዳይ የባለሀብቶችን ጉዳይ ሲያስፈጽሙ ያገኘናቸው አቶ ሙሀመድ ያሲን ለአዲስ ዘይቤ በሰጡት አስተያየት የተርሚናሉ ግንባታ አስፓልት አለመሆኑ ሸቀጦች በአቧራ እየተጎዱ መሆኑን ነግረውናል። አቶ ሙሃመድ አክለውም የወረታ ደረቅ ወደብ እንደሌሎች አቻ ወደቦች በኮንክሪት አስፓልት ቢሰራ ብዙ አስመጪዎች እና ላኪዎች ይሄንን ወደብ ወደመጠቀም ሊመለሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የወረታ ደረቅ ወደብ አገልግሎት ምረቃ ስነስርዓት ወቅት የሁለተኛው ዙር ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር በወቅቱ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የሁለተኛው ዙር ግንባታ አለመጀመሩን አዲስ ዘይቤ ተመልክታለች።

አቶ ሰለሞን አትንኩት ከ20 ዓመት በላይ የከባድ መኪና  አሽከርካርዋል። ቤተሰባቸው በባህር ዳር ከተማ ስለሚኖሩ እግረ መንገዳቸውን ቤተሰባቸው ለመጎብኘት የወረታ ደረቅ ወደብን ይጠቀማሉ። እርሳቸው እንደሚሉት በወረታ ደረቅ ወደብ የሚሰጥ አገልግሎት መልካም ነው። “ነገር ግን ከጋሸና ወልድያ ያለው መንገድ ብልሽት ግን እቃዎችን በወቅቱ አጓጉዞ ለማድረስ አስቸጋሪ አድርጎብናል” ሲሉ ነግረውናል።

የመንገዱ አስቸጋሪነት ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ ልክ እንደ ሌሎች ነባር ወደቦች በአሽከርካሪዎች፣ በአስመጭና ላኪዎች ተመራጭ ለማድረግ የመንገድ ጥገናውን ፈጥኖ ማከናወን እንደሚገባም ጠይቀዋል። ከወልድያ ጋሸና ያለው መንገድ በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱ እቃዎች ከጅቡቲ በወቅቱ ተጓጉዘው እንዳይደርሱ ማድረጉን እና አሽከርካሪዎችም የወረታ ደረቅ ወደብን እንዳይጠቀሙ ማድረጉንም አቶ ሰለሞን ነግረውናል።

የወረታ ደረቅ ወደብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አያሌው በሠጡት ምላሽ የደረቅ ወደቡ ተርሚናል አቧራ የሆነው ጊዜያዊ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረው አቧራውን ለመቀነስ ተርሚናሉን በየቀኑ በመኪና ውሃ በመርጨት ጊዜዊ መፍትሄ እየሰጠን ነው ብለዋል።

የደረቅ ወደቡ ሁለተኛው ዙር ማስፋፊያ ግንባታ ዲዛይን እና ጥናቱ መጠናቀቁን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ በቅርቡ ግንባታው እንደሚጀመር ተናግረዋል። ሥራ አስኪያጁ አክለውም “ከወልድያ ጋሸና ያለው መንገድ በደንበኞች ላይ እንግልት ከመፍጠር አልፎ ለኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን እናውቃለን፤ መንገዱ እንዲጠገን ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል” ብለዋል።

በጉምሩክ ኮሚሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አለነ መሐሪ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የወረታ ደረቅ ወደብን እየተጠቀሙ ያሉት የፕሮጀክት፣ የፋብሪካ እና የመንገድ ሥራ እቃ አስመጭዎች ብቻ ናቸው ብለዋል። የንግድ እቃዎች አስመጪዎች ግን ዛሬም ወረታ ደረቅ ወደብን ከመጠቀም ይልቅ ከቃሊቲ፣ ሞጆ እና ሌሎች ወደቦችን እየተጠቀሙ ነው የሚሉት አቶ አለነ ይህ መሆኑ ደግሞ ወደቡ የታሰበውን ያህል ጥቅም እንዳላስገኘ ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር እንዲሁም የመንገድ እና የማጓጓዣ ዋጋ መናር ለወደቡ አለመልማት ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል። 

ከባህር ዳር ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የወረታ ደረቅ ወደብ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድና መፋሰሻ ስርዓት እንዲሁም መጠባበቂያ ጄኔሬተርን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እና ሌሎችም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች አሉት። ከወረታ ደረቅ ወደቡ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ወደቡ ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ 3 ሺህ 66 ሙሉ ገቢ፣ ሙሉ ወጪ፣ ባዶ ገቢና ባዶ ወጪ ኮንቴይነሮችን አስተናግዷል።

አስተያየት